
ስፖርት ዋሊያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን በታንዛኒያ ያከናውናል
ቀን: September 1, 2024
- ዛሬም የጎረቤት አገር ሜዳዎችን መጠቀም ግዴታ ሆኖበታል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በሞሮኮ በ2025 ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በታንዛኒያ፣ ከባለሜዳው ታንዛኒያና ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ይጫወታል። ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ዳሬ ሰላም የሚያመራው ብሔራዊ ቡድኑ ከአራት ዓመታት በፊት የተጣለበት በሜዳው የመጫወት ክልከላ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብን ጨምሮ ድርብ ኃላፊነት በያዙት አሠልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ለሁለት ሳምንታት በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲዘጋጅ ቆይቷል። በቆይታው ከኢትዮጵያ መድን ጋር የአቋም ፍተሻ ተጫውቶጨዋታ 1 ለ0 አሸንፏል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አሠልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ለአንድ ዓመት እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ኃላፊነቱን ወስደው እንዲያሠለጥኑ የአንድ ዓመት ኮንትራት እንደሰጣቸውና የክለቡን ኃላፊነትም መቀጠል እንደሚችሉ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ኮንትራቱ ሲጠናቀቅ አሠልጣኙ በያዙት ኃላፊነት ይቀጥሉ ወይስ አይቀጥሉ? ለሚለው ግን የሥራ አመራር ቦርድ እንደሚወስን የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃም ገብረ ማርያም ተናግረዋል፡፡
ዋሊያዎቹ ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን የታንዛኒያ አቻቸውን ከገጠሙ በኋላ፣ ጳጉሜን 4 ቀን ደግሞ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ማከናወን የነበረበትን ሁለተኛውን ጨዋታ፣ በዕገዳው ምክንያት በታንዛኒያ ስታዲየም እንዲያከናውን ተገዷል፡፡
ኢትዮጵያ ከስታዲየም ስታንዳርድ ጋር ተያይዞ፣ ነባሩን የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ፣ በአገሪቱ የሚገኙት ሁሉም ስታዲየሞች፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባስቀመጠው ዝቅተኛ መሥፈርት መሠረት ማሟላት እንደሚጠበቅባት፣ ካልሆነ ግን ዋናው ብሔራዊ ቡድኗ የሚያደርጋቸው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሚመርጠው አገር ስታዲየሞች እንዲጫወት ከአራት ዓመት መወሰኑ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ፣ ለማስተናገድ ትችል ዘንድ የተጀመሩ ስታዲየሞችን ጨምሮ የአዳዲስ ስታዲየሞች ግንባታ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ስታንዳርድን ጠብቀው መገንባት እንዳለባቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ መናገራቸው ይታወሳል።
