አስተያየት

Byአንባቢ

September 1, 2024

በኑረዲን አብደላ አልሐረሪ፣ ከካናዳ

ርዕስ—የትርክት ዕዳና በረከት

ጸሐፊ—  ዳንኤል ክብረት (ዲያቆን)

ገጽ—-575

ታተመ—በ2016

አስተያየት ሰጭ….. ኑረዲን አብደላ አልሐረሪ ከካናዳ 

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በርካታ መጻሕፍትንና መጣጥፎችን ለኅትመት ያበቁ ሰው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታዋቂ ዲያቆንና ሰባኪ ናቸው። ከ30 በላይ ዓመታት አገልግሎት 35 መጻሕፍትን በመጻፍ ‹ሙሐዘ ጥበብ› የሚል የክብር ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመጋቢት 2010 ያልተጠበቀው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲቀየር፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሆኑ መረጧቸው። እ.ኤ.አ. በ2021 ምርጫ ገለልተኛ ዘመቻ አካሂዶ አዲስ አበባ ላይ አንድን ክልል የሚወክል የፓርላማ መቀመጫ አሸንፈዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። በ2016 ለንባብ ያበቁት መጽሐፍ ‹‹የትርክት ዕዳና በረከት›› በሚል ርዕስ የታተመ ነው፡፡በዚህ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ‹‹ታሪክ የማኅበረሰባዊ ግንኙነት ቅሪት ነው፡፡ ግንኙነቱ ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ትሩፋትንም ያካትታል፡፡ በዚህ ውስጥ በሰዎችና በአገሮች መካከል የሚፈጠረውን ዕድገት፣ ግጭት፣ ውጣ ውረድና ፈተና ይመዘግባል፡፡ ሀብት መፍጠር፣ የግዛት መስፋፋትና መጥበብ፣ ጠላትና ወዳጅ መሆን፣ ወዘተ የጋራ ዝክረ ፀባዮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ትርክት ከዚህ ሥር የሚቀዳና የሚመዘዝ ውርስ ነው፤›› ካሉ በኋላ ‹‹ትርክት ሆን ተብሎም ይሁን በተለምዶ በዓላማ የሚዘጋጅ ንግርት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ታሪክን፣ እምነትን፣ ባህልንና አመለካከትን ይይዛል፡፡ የሚነገርበት ምክንያት አለው፡፡ የሚዘጋጀውም ለዚያ ምክንያት ሲባል ነው፡፡ የሚካተቱት ከተዘጋጀበት ዓላማ ጋር የሚሄዱ ሐሳቦችና ታሪኮች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የትርክቶች በጎነትና እኩይነት በትርክት ቀራፂዎቹ እጅና ፈቃድ ወይም ቁጥጥር ሥር ሲወድቅ ይታያል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በበጎ ዓላማ ከተዘጋጁ በአንድ አገር ሕዝቦች መካከል መግባባትንና አንድነትን እንደሚፈጥሩት ሁሉ፣ በእኩይ ዓላማ ከተዘጋጁ ደግሞ መቃቃር በመፍጠር የግጭት አዙሪት ውስጥ ያስገባሉ፤›› ሲሉ ትርክታቸውን ያስራሉ፡፡

ዲያቆን ዳንኤል በድርበቡም ቢሆን ለአንድ ወገን ዓላማ የተቀረፀ፣ ልዩነትንና ብዝኃነትን ያልተቀበለ፣ ማቀራረብና ማግባባት ዓላማው ያልሆነ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የማይፈጥር ትርክት፣ ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያን ብዙ እንደፈተናት፣ ዋጋም እንዳስከፈላት፣ በተከታታይ የተነሱ የፖለቲካ ኃይሎች የተከተሉት ወይም ሊከተሉት የሚፈልጉት የትርክት መንገድ ምን ያህል ስሁት እንደሆነና አገራችንን ወደ ውስብስብ ችግር እንዴት እንደከተታት፣ የትርክቶቻችን መወላገድ አገራችን የሚያግባባ ትእምርት እንዳይኖራት እንዳደረገ ይተነትናሉ፡፡

ጸሐፊው ለንባብ ባቀረቡት መግቢያ ላይ ‹‹ይህ መጽሐፍ የነባር አገራዊ የትርክት ዕዳዎቻችን ወደ ገዥ ትርክት እንዴት መለወጥ እንደሚገባን ማሳየት ቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ ለዚህም መግባባት ያልደረስንባቸውን፣ በተቃርኖነት የሚታወቁትን አገራዊ መግባባት የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ከሥነ ታሪክ ጥናት አንፃር የታሪክና የትርክት አሰነዳድን ይቃኛል፡፡ በተቃርኖ ትርክት ፖለቲካዊ ሥሪታቸው የሚታወቁ ፓርቲዎችና እሳቤዎቻችውን እንዲሁም አገር ለመምራት ባይበቁም የተቃርኖ ትርክት ሙጥኝ ብለው የያዙ ነባርና አዳዲስ ኃይሎችን በዝርዝር እንደሚዳስስ፣ በመደምደሚያውም የአገራችንን ቀደምት ሥልጣኔዎችና የሙሉ ዕይታ ጉድለታችንን ይገመግማል፡፡ ከኋላ ቀርነት ወደፊት አስፈንጥሮ የሚያወጣንን፣ ከተውሶ እሳቤ ነፃ የሆነውን፣ ኢትዮጵያ ገዥ ትርክት ባስፈለጋት ወሳኝ ሁነት ላይ የተከሰተውን የመደመር እሳቤን ያነሳል፡፡ ከኅብረ ብሔራዊነትና ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታችን አንፃር አገራዊ አሰባሳቢ ገዥ ትርክት በመደመር እሳቤ የምናበጅበትን ዘላቂ መንገድ ያሳየናል፡፡›› ይላሉ፡፡

ይህን መግቢያ ከሰጡ በኋላ ግን በትርክት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በርካታ ማስረጃ መረጃ ባለው የሐርላ ኅብረተሰብ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ በአርኬዎሎጂ ምርምር ውጤቶች እንደሚያመለክተው እስልምና ወደ ሐርላ የገባው ከ12ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (መክዘ) አካባቢ ነው (ገጽ 485) ይላሉ፡፡

ሆኖም የሐርላ ማኅበረሰብ እስልምና በመጀመርያ ከተቀበሉት በመቀጠልም  የእስልምናን መንግሥት በ896 ዓመት ከመሠረቱ አንዱ የሐርላ ማኅበረሰብ ነው። ይህንን በተመለከተ የአንትሮፖሎጂ ምሁር ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሚከተለውን በ‹‹ሴረ›› ገጽ 52 ‹‹ከሂጃዝ ዓረቢያ በዓረቡ ሙስሊም አስተማሪዎችና ነጋዴዎች አማካይነት በተለዩ የዜይላ በርና መንገድ የእስልምና ሃይማኖት፣ ባህልና ሥልጣኔ በክፍ ለአገሩ መሀል ደቡብ ወደ ጥንታዊው አጎራባች የሐርላና የሀዲያ ሴማዊና ኩሻዊ አገሮች ለመጀመርያ ጊዜ እንደገቡና ብሎም ከ896 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በሐርላ ሴማዊ ምድር ሸዋ የኢትዮጵያ የመጀመርያው እስላማዊ ሡልጣኔት ወይም  መንግሥት እንደ መሠረቱ ይታወቃል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የታሪክ ፕሮፌሰሩ ላጵሶ ጌ. ድሌቦ (ዶ/ር) ይህንን በተመለከተ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረቶችና መሣሪያዎች›› ገጽ 46  ላይ ‹‹ከ896 ማለት ገና ከአክሱም ዘመን ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ በሐርላ ሴማዊ አገር ሸዋ የተሰኘው የኢትዮጵያ የመጀመርያ እስላማዊ ሡልጣኔት (መንግሥት) እንደተነሳና እስከ 13ኛው  ምዕጽ ዓመት መጨረሻ ድረስ በ400 ዓመታት በሚቆጠር ዘመን ውስጥ የሀዲያ፣ የይፋት፣ የደዋሮ፣ የአርባቢኒና የባሌ  ሡልጣኔቶች ጨምሮ በአካባቢው ሌላም ብዙ እስላም ሕዝቦችና አገሮች እንደነበሩ አሁንም ከታሪክ መረጃና ጥናት ተረጋግጧል፤›› ይላሉ፡፡

ላጵሶ ጌ.ድሌቦ (ዶ/ር) ከላይ ስሙ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ገጽ 97 ውስጥ ‹‹የአርኪኦሎጂ፣ የትውፊትና የታሪክ መረጃዎች መሠረት ከደቡብ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሕዝቦች አንዱ በዘር በቋንቋና በሃይማኖት በደቡብ ምሥራቅ ከዛሬው የሐረሪ (አደሬ) ሕዝብ ጋር የቀረበ ታሪካዊ አንድነት ያለው የሐርላ ሕዝብ ነው፤›› በማለት አስፍረዋል፡፡  

ከይረዲን (ዶ/ር) ብራውካምፐርን ጠቅሰው ባሰፈሩት ጽሑፍ (በገጽ 142) ‹‹የሐረሪ መሰል ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ የሐረሪ አባት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼኽ አባዲር ከውጭ (ሒጃዝ) ሲመጡ የተቀበለ ሕዝብ እንደነበረ ሲገልጽ ‹Harla was a formely existing population on the northern excarpment of Caarcar and  Harar mountains. And when Shek Abadir came from Arab land in 10th century or 11th century and sometimes 13th Century A.D these Harari like speaking Semetic people were there and welcomed him.› ሼክ አባዲር ወደ ሐረር ሐርላ የመጡበትና ሕዝቡ የተቀበላቸው ጊዜ ያለውና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ከገለጹት እጅግ የጎላ ልዩነት አለው፡፡ እስልምና ወደ ሐረር የገባው ከሼክ አባዲር በፊት በሰባት ክፍለ ዘመን ነበር።

ሸክ ጀማሉዲን ኢብራሂም ኸሊል አሻሚና ልጃቸው ሐሺም ጀማሉዲን ኢብራሂም ‹‹የዓፋር/ደናኪል ታሪክና መረጃ አርኪ ምንጭ/አል መንሃል›› በሚል ርዕስ በ2000 ባሳተሙት መጽሐፍ በገጽ 434 እስከ 435 ስለ እስልምና መንግሥት በአፋር አጀማመር ሲተርክ፣ የመኽዙማይት መንግሥት የተቆረቆረው በ283 ዓመተ ሒጅሪያ (ዓ.ሒ.) ወይም በ896/897 አካባቢ ነው ተብሎ ተጠቅሷል፡፡

አህመድ መሐመድ ኢብራሂም ስለ አርጎባ ሕዝብ መነሻ በተመለከተ በገጽ 9 ‹‹ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ ጀምሮ ለምዕት ዓመታት በተከታታይ ልዩ ልዩ የዓረብ ጎሳ ስደተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አስተማሪዎች ቀይ ባህርን በፈለሳ ተሻግረው በአዶሊስና በዘይላ የወደብ በር ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በአቢሲኒያ ሴማዊ ምድር ላይ መጀመርያ በቆላማው ክፍል ከዚያም በሐርላና አጎራባች ሕዝቦች ምድር ላይ በነዋሪነት ሠፈሩ፡፡ በዚህ ረገድ መጀመርያ ከሠፈሩ በር የምሥራቅ ቆላማ ሥፍራ እየለቀቁ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የንግድ፣ የግብርና የዕደ ጥበብ ሥራዎችን እያስተማሩና እያስፋፉ በመጓዝ በመሀል አገር ላይ በቋሚነት በመሥፈር ማዕከላዊ መሠረትና ይዞታቸውን አጠናከሩ፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በርዕሱ በተጠቀሰው ሥራቸው በገጽ 502 ስለ ሐረር ሳንቲም (ገንዘብ) ሲያወሱ ‹‹በኢማም ኑር ጊዜ አሽረፍ የሚባለውን የግብፅ ማምሉኮች ገንዘብ ትጠቀም ነበር፡፡ መሐለቅ የተሰኘው ሳንቲም ደግሞ 1773 እስከ 1883 ዓ.ም. ድረስ በአገልግሎት ላይ ውላል፤›› ይላሉ፡፡

በመሠረቱ፣ የሐረር አሚሮች ሳንቲም (ገንዘብ) ተሠርቶ ገበያ ላይ የዋለው በ16ኛው መክዘ በአሚር ኑር ዘመነ መንግሥት ነበር፣ ሐረር የራሷን ገንዘብ  መሐለቅ በወቅቱ ትጠቀም እንደነበር በርካታ መረጃና ማስረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የግብፅ ይሁን የሌሎች አገሮች ገንዘብ (እንደ ዛሬው ዶላር) በተጓዥ የሲራራ መንገደኞችና ነጋዴዎች በሐረር፣ በዜይላ፣ በዘቢድና በዛንዚባር ወዘተ የአሸረፍ እንዲሁም የሌሎች ክራውና ማርቴሬዛም በተለያዩ ወቅትና ጊዜያት ግብይት ላይ ውሏል፡፡ ይህ ማለት ጸሐፊው እንደሚሉት የሐረር ሳንቲም መሐልቅ አልተጠቀሙም ማለት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ስለ ሐረር አሚሮች ሳንቲሞች ጥናትና ሙሉ ምርምር ለመጀመርያ ጊዜ የቀረበው ከዛሬ ከ60 ዓመታት በፊት በሐረሪው ሊቅ አው አህመድ ሻሚ ነው። ታላቁ የሐረር ሊቅ አህመድ ሻሚ በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ለዘርፉ ተመራማሪዎች ባቀረቡት ጥናት ምርምር ከ30 በላይ የተለያዩ የሐረር አሚሮች ሳንቲም ናሙናዎች በተለያዩ አሚሮች ንግሥና ዘመን የተጠቀሙባቸው በተለያዩ የብረት ማዕድናት መጠቀማቸው ጥናቱ ያመለክታል [ለተጨማሪ መረጃ The Ethiopian Herald, Thursday June 27,1964 GC ይመልከቱ፡፡]

ጸሐፊ አህመዲን ጀበል ‹‹በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና የጭቆና ትግል›› በሚል ርዕስ በ2003 ዓ.ም. ለንባብ ባበቃው መጽሐፉ ስለሐረር አሚሮች ሳንቲም በገጽ 219 ‹‹በሐረር መሐለቅ የተሰኘ ሳንቲም ከአሽረፍ ጋር ለመገበያየት ውሎ ነበር። በሐረሩ መሐለቅ ሳንቲም ላይ በአርበኛ ‹‹ላ ኢላሃ ኢለላህ›› (ከአላህ በስተቀር በእውነቱ የሚመለክ አምላክ የለም) የሚል ሲጻፍበት በጀርባው ደግሞ የአሚሩ ስም ተጽፎበታል። ነገር ግን ለመገበያያነት ውሎ ያገኘው ሳንቲም በ1504 (በ910 ዓ.ሒ.) እንደተሠራ ይገልጻል። እ.ኤ.አ. በ1495 (በ900 ዓሂ) በ1504 (910 ዓ.ሒ.) እና በ1536 (943 ዓ.ሒ.) በኢማም አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ ዘመን የተሠሩ ሳንቲሞች ተገኝተዋል›› በማለት አስፍሯል፡፡

የሐረር አሚሮች ሳንቲም በጥናት ተመርምሮ ተቀባይነት ያገኘው ከ16ኛው መክዘ አሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ በኋላ የተሠሩ ሳንቲሞች ናቸው። በዚህ መሠረት አሚር ኑር የመጀመርያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሐረር ሳንቲም አምርቶ ገበያ ላይ ያዋለ ድንቅ ተወዳጅ  አሚር ነው።

አቪሻይ ቢን ዶሮር (Avishai Ben-Dror) ለዶክትሬት መመረቂያው “Emirate, Egyptian, Ethiopian; Colonial Experiences in the Nineteenth-Century Harar” በገጽ 17 ‹‹Nur was the first ruler of Harar who coined local currency, the main one being the Mahlak.›› የሐረር አሚር ኑር የመጀመርያው የአገር ውስጥ መሐለቅ እንዳሳተሙ የገለጸ ሲሆን፣ ስለመሐለቅና ስለ መሐለቅ ግብይትም በ206፣ 209፣ 227 አብራርቷል፡፡   

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የግራኝ አሕመድ ወረራ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው በገጽ 46 ስለ ሐረር ሳንቲም የመገበያያ ገንዘብ በተመለከተ ‹‹የሐረርጌ ሡልጣኖች ወይም የነ አሚር ኑር ግዛት የመገበያያ ገንዘብ ሊኖረው የቻለው ይኸው የሐረርጌ በዘይላ ወደብ አማካይነት በቀይ ባህር ማዶ ከአሉት ከዘቢድ ዓረቦችና ቱርኮች ጋር የሥልጣኔ ግንኙነት አድርጎ ሸቀጥ ለሸቀጥ እየተለዋወጠ ንግዱን በማስፋፋቱ ምክንያት ይሆናል፤›› በማለት አስፍረዋል።

በሐረር አብደላ ሸሪፍ የግል  ሙዚየም የቀረቡት የሐረር ሳንቲም ስብስቦች ጥልቁ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሐረር ከ30 በላይ የተለያዩ የሐረር አሚሮች በተለያዩ ዘመናት ባስተዳደሩበት ወቅት የተሠሩ ሳንቲሞች ናቸው። የእነዚህ የ30 አሚሮች (ነገሥታት) የተሰበሰበው ጠቅላላ የሳንቲሞቹ ቁጥር ብዛት በሸሪፍ ሙዚየም ከ2900 እስከ 3000 የተለያዩ ሳንቲሞች ናቸው። የተሠሩት በተለያዩ ብረት ነሐስ፣ ብር፣ ወርቅን ያካተተ ነው፡፡ ምደባቸው የመጀመሪያው በ121 ዓመተ ሒጅሪያ (ዓ.ሒ.) ነው፡፡ ይህ በአማካይ ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜ ጠገብ ሳንቲም ምድብ ይመደባል፡፡ ነገር ግን የጥናቱ ዝርዝር በተገቢው አልቀረበም ተብሎ በሒደት ላይ ያሉ ናቸው። ሁለተኛው የሳንቲም ምድብ በ223 እስከ 931 ዓ.ሒ. የተሠሩ ሳንቲሞች ናቸው፡፡ ይህም በአማካይ ከ720 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ በትክክል ተቀባይነት ቢያገኙም ጥናቱ በዝርዝር ዘገባ ተጠናቅቆ መረጃው ባለመቅረቡ ተንጠልጥለው ‹ሥራው ያልተጠናቀቀ› ተብለው የተሰበሰቡ የሐረር ጥንታዊ ሳንቲሞች ናቸው። ሦስተኛ የሐረር ጥንታዊው ሳንቲም ምድብ የሐረር መሐለቅ በ950 ዓ.ሒ. ወይም እ.ኤ.አ.1560 የተሠሩ የሐረር ሳንቲሞች ናቸው፡፡ እነዚህ የሐረር ሳንቲሞች ስናስብ የሐረር መሐለቅ ሳንቲም ከአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ ከ1560 ወዲህ የተሰበሰቡ ናሙና ሳንቲም ስብስቦች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሳንቲሞች በተገቢ ጥናት መመዘኛ  አልፈው ተቀባይነት አግኝተው ለጥናት፣ ለምርምር፣ ለዕይታ በተለያዩ ሙዚየሞች የቀረቡ ናቸው፡፡ እነዚህ በአማካይ ከ500 ዓመታት በላይ ዕድሜ ጠገብ ሳንቲሞች ናቸው። የተሠሩትም በነሐስ፣ በብር አልፎ አልፎ በወርቅ የተሠሩት ናቸው፡፡

የግብይይት አቅምና ዝርዝር በተለያዩ የወቅቱ መረጃ የሚያመለክተው፡- 

1 አሽረፍ = 22 መሐለቅ

2 አሽራፍ = 40 መሐለቅ = 1 ክራውን 

በአሚር ኑር ዘመን በተከሰተው ረሃብ የዋጋ ውድነት ዝርዝር ሲቀርብ፡- 

4 ኡድ ማሽላ = 17 አሽራፍ = 374 መሐለቅ 

1 ላም = 300 አሽራፍ = 6600 መሐለቅ

ምንጭ፣ አብደላ ሸሪፍ የግል ሙዚየም፡፡

‹‹የትርክት ዕዳና በረከት›› ጸሐፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተጠቀሰው መጽሐፋቸው፣ በገጽ 491 በቁፋሮ የተገኙ አርኪዮሎጂ ምርምሮች ሐረር በከተማነት የተቆረቆቀረችበት  ዘመን ከ15 መክዘ እንደማይቀድም አመልክተው በገጽ 491 ደግሞ ‹‹ሁሉም ለማለት በሚቻልበት መልኩ ጥንታዊው መስኪዶቹ የተገነቡት በ15ኛው መክዘ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ግን በጣም የተሳሳተ ትርክት ነው፡፡

በሰነድ የተያዙ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ሐረር የተቆረቆረችው በአሥረኛው  መክዘ አካባቢ ሲሆን፣ ከአሥረኛው ክፍለ ዘመን በፊት የሐረሪ ማኅበረሰብ ይኖር የነበረው በሐርላ ጥንታዊው ሰባት መንዶሮች ቱኹንጌይ፣ እስኻንቲ ጌይ፣ ሐሰንጌይ፣ ፈረቃ ጌይ፣ ሐረዌ ጌይ፣ ሩቂያ ጌይና ሳምቲ ጌይ ተበታትነው በሐርላ ምድርና መንደር ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚያ በመቀጠል የእስልምና ሃይማኖት እንዲሁም የእስልምና መንግሥት ከዓረቢያ በዘይላ ወደ ሐርላ ምድር በመጡ ነጋዴዎችና የሃይማኖት አባቶች እስልምናና የእስልምና መንግሥት ለመመሥረት ቻሉ። 

መፍቱህ ዘከሪያ  በሐረር በተለያዩ ሥፍራ የሚገኙት ዋሻዎችና በውስጡ በያዙት መረጃዎች ዝርዝር በማቅረብ ከእስልምና ወደዚህ ከመምጣቱ በፊት የሐርላ ማኅበረሰብ በአካባቢው ለብዙ ሺሕ ዓመታት መኖሩን በዝርዝር አመልክቷል፡፡ በገጽ 31 ላይም የመጀመርያው የሐረር አሚር፣ አሚር ሐቦባ  ከአባዲር በፊት በ994 በሳምቲ ጌይ አስተዳድረዋል ይላል፡፡

መፍቱሕ ዘከሪያ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ከ940 እስከ 950 የሐረሪ የዘር ግንድ ምንጮች ሐርላ፣ አዋሬ፣ ጋሳ፣ ወርጋር፣ ጋቱሪ፣ አዱስና አቦኝ ከሰባት የሐርላ መንዶሮች አው አባዲር ከዓረቢያ የሃይማኖት መሪ በመሆን በዛሬዪቱ ሐረር አሰባስበው ከተማዋ እንዲያብብ አድርጎታል፤›› በማለት በገጽ 40 ላይ አስፍሯል፡፡

አብዱማሊክ አቡበከር (ዶ/ር) ባቀረቡት የጥናት ጽሑፍ ባስነበቡት መጽሐፍ እስልምና ወደ ሐረር የደረሰው ከአው አባዲር ቀደም ብሎ ከሁለት ሦስት ክፍለ ዘመን ቀድሞ ወደ ሐረር እንደደረሰ በመግለጽ የብራውካምፐር፣ የቲርሚንገሃምና ዋግነር  ከመሳሰሉት አባባል ጋር  ይስማማል። ለዚህም እንደ ማስረጃነት የሚያቀርቡት  አሥር ክፍለ ዘመን ላይ የተገነቡት ሦስቱ የሐረሪ መስጂዶች ማለት አው መንሱር፣ አው መሐመድ አቦኝና  አው መሽሀድ ናቸው። (ዶ/ር አብዱማሊክ አቡበከር፣ የሐረሪ እሴት ራስን በራስ ለማስተዳደርና ባህሪ ገጽ 25 ቀን 2013)

በሐርላና በሐረር የሚገኙት መስጂዶች ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ ስለመሆናቸው በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከታች የቀረበው የፊሊፕና ሰርጌ ጽሑፍ የሙስሊም ከተማ በኢትዮጵያ በሚለው ዝርዝር መረጃ በገጽ 39 ‹‹በሐረር የመጀመርያዎቹ መስጂዶች የተገነቡት በ10ኛው እና በ12ኛው ክፍለ ዘመን መካከል ነው ተብሎ ሲጠቀስ በገጽ 41 ደግሞ  ዲን አጎበራ፣ ኢማም አርዲን፣ አው መንሱር፣ አው መሻድ በ10ኛው እና 12ኛው ክፍለ ዘመን መካከል መገንባታቸው ተመልክቷል፡፡ 

በሌላ በኩል ይህንን መረጃ የሚያጠናክሩ በርካታ ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡ ለአብነት የሚከተለውን እንመልከት፡፡ 

የጀርመኑ Ulrich Braukmper፡ The Islamization and The Muslim Shrines of Harar plateau በተባለው ማስታወሻ  ጽሑፍ፣ ሼኽ አባድር ወደ ሐረር በመጡበት ወቅት ማኅበረሰቡ  እስልምናን ሃይማኖት ቀድሞ የተቀበለ መሆኑን ዩሪች [When Abadir reached Harar his company of 405 shaykhs the native peoples he met there , Harala , Gaturi and Argoba were all Islamized  በማለት ጽፎታል፡፡ 

በተጨማሪም ሼኽ አባዲር ቡድናቸው የነበረውን እስልም ሃይማኖትን ማጠናከራቸውን ኡልሪች ብራውከምፐር ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ‹‹አባድር የእስልምና ፈር ቀዳጅ የሃይማኖት አባት አልነበረም፣ ነገር ግን እሱና ቡድኑ የሃይማኖትን ሁኔታዊ ማዕቀፍ ለማጠናከር የወሰዱት ዕርምጃ እንደሆነ ግልጽ ነው፤›› በማለት ያስነብበናል፡፡ 

ዳንኤል ክብረት በሥነ ቁፋሮም የተገኙ መስጂዶች  ከ15 መክዘ በኋላ ነው የሚል ክርክር የሚያነሱ ይመስላል፡፡ ይህ ከሆነ ለክርክሩ መልስ የሚከተለው መረጃ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ቢቢሲ (BBC News Africa) በጁን 16 ቀን 2017 (ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም.) ስለ ሐርላ ምርምር  ባቀረበው በሥዕል የተደገፈ ሰፊ ዘገባው ‹‹በኢትዮጵያ የሚገኙ አርኪኦሎጂስቶች በሐርላ፣ በጁን 16 ቀን 2017 ጥንታዊ ከተማን አገኙ፤›› ካለ በኋላ በሥዕሉ ሥር ‹‹እነዚህ የ12ኛው ክፍለ ዘመን መስጊድ ቅሪቶች ናቸው። በምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ አሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን (መክዘ) ድረስ የተረሳች ከተማ በአርኪኦሎጂስቶች ቡድን ተገኝቷል። በሐርላ ክልል ከግብፅ፣ ከህንድና ከቻይና የተገኙ ቅርሶች በከተማው ውስጥ ተገኝተዋል። አርኪኦሎጂስቶች በታንዛኒያና በሶማሊላንድ ከሚገኙት መስጊዶች ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የ12ኛው ክፍለ ዘመን መስጊድ አግኝተዋል፡፡ ይህ በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ እስላማዊ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ያረጋግጣል ይላሉ አርኪኦሎጂስቶች፤›› በማለት ቢቢሲ ዜናውን ዘግቧል፡፡ ይህንን የመሰሉ መስጂዶች በሐረር፣ በኮሮሚ፣ በቡርቃ፣ በጉርሱም ወዘተ ዕድሜ ጠገብ መስጂዶች ይገኛሉ፡፡ ይህንን ቅርስና ታሪክ ነው ዳንኤል ክብረት ሁሉም መስጂዶች በ15 መክዘ ተገንብተዋል በማለት ታሪካችንን ለማደብዘዝ የሚጥረው፡፡ 

የዩኔስኮ መረጃ ደግሞ እስልምና በሐረር አካባቢ ምን ያህል ዕድሜ ጠገብ መሆኑን ‹‹እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጥንት ሙስሊም ደቀ መዛሙርት በመካ የደረሰባቸውን ስደት ሲሸሹ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የእስልምና ትምህርት ዋና መቀመጫ ሐረር ነበር፣ ዊች በሐርላ አቅራቢያ ትገኛለች። ሐረር እጅግ ቅዱሳን ከሆኑት እስላማዊ ከተሞች ተርታ ትመደብና 82 መስጊዶች ያሏት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአሥረኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠሩ ሦስቱ መስጊዶችና 102 መስጊዶች አሏት፤›› በማለት አስገንዝቧል፡፡

በሐረርና አካባቢው እስልምናን ያስተዋወቁና ሃይማኖቱን ከመካ ዓረቢያ በ615 ወደ ሐረር [ዲን አጎበራ የተባበው ሥፍራ] ይዘው የመጡት የነቢዩ መሐመድ (ዐሰወ) ባልደረቦች ሰሃባዋች መሆናቸውን ጥንታዊው ትውፊትና የድርሳናት ሰነድ ያመለክታል፡፡ በዚህ ረገድ ይህንን ጥናት ምርምር ካደረጉት ታላቁ የሐረር ታሪክ ሙሁር ኡስታዝ ዩሱፍ አብዱረህማን ሼኽ፣ አላህ ይርሃማቸውና  በዓረቢኛ በጻፉት ርዕሱ ‹‹ታሪኽ መመለከቱል ሐረር ኢስላሚያ›› ወይንም  በአማርኛው ሲተረጐም – እስላማዊ ግዛት የሆነችው የሐረር ከተማ ታሪክ አጭር ዳሰሳ- ብለው የጻፉትና ለኅትመት ያልዋለ ጽሑፍ በእጄ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ እስልምና ወደ ሐረር እንዴት እንደደረሰ ኡስታዝ ዩሱፍ የሚከተለውን ‹እስልምናና ሐረር› በሚለው ሥር ያስነብባል፡፡ 

የእስልምና ሃይማኖት ወደ ዘይላና ሐረር የገባው በሰይደና ኡስማን ኢብኑ አፋን እጅ ነበር፡፡ ከሳቸው ጋር ሚስታቸው ሩቅያህ የረሱላችን ልጅ የሆነችው፣ እንደዚሁም አብዱረህማን ኢብኑ አውፍና ሌሎች 14 ሙሀጂሮች (ስደተኞች) አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ይሄም የሆነው በ615 የመጀመርያ ሒጅራቸው  ላይ ሲሆን፣ ይህም ረሱል መሐመድ (ሰዐወ) ወደ መዲና ሒጅራ ከማድረጋቸው ስምንት ዓመት በፊት ነው::

 እነኚህ ወደ ሩቂያ ጌይና  ዘይላ ሂጅራ  ያደረጉ ሰዎች (ስደተኞች) አራት ወራት ረጀብ: ሽዐባን፣ ረመዳንና ሹዋል ቆይተው ወደ መካ አገራቸው ተመለሱ] በማለት ኡስታዝ ዩሱፍ አብዱረህማን ሼኽ እስልምና ሐረር እንዴት በማን እንደረሰና ሐረር እስልምናን በመቀበልም ሆነ በማሠራጨት ቀዳሚ ሥፍራ እንደነበራት ጽሑፉ በስፋት ያብራራል፡፡  ለዛሬ በዚሁ ላብቃ  ሠናይ ጊዜ እንመኛለን! 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው <nur_man77@yahoo.com> ማግኘት ይቻላል፡፡