በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ የተጠቃ ታማሚ ሕክምና አግኝቷል

ዓለም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የከፋ የዓለም ሥጋት እንዳይሆን የቀረበው ጥሪ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: September 4, 2024

በሁለት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት መሆኑን አውጇል። የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ማሳሰቢያ እንደሚያመለክተው ወረርሽኙ እንደገና ለዓለም ጤና አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

ከዚህ ቀደም ከታዩት የባሰ አደገኛ ነው የተባለው ‹‹ክላድ 1 ቢ›› የሚባለው አዲሱ ዝርያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎችን ኅልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ ወደ አጎራባች የመካከለኛውና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም እየዘለቀ ይገኛል። እንደ ቡሩንዲ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ባሉ አገሮችም በሽታው እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት ወቅታዊ መረጃ ያሳያል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የከፋ የዓለም ሥጋት እንዳይሆን የቀረበው ጥሪ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በኤምፖክስ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ነርሱ ጓንቱን እያስተካከለ

የቀውሱ ማዕከል በሆነችው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 629 ሰዎችን የሞቱ ሲሆን ከ18,000 በላይ በቫይረሱ መያዛቸው ተዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 በተከሰተው ወረርሽኝ ወቅት ያገለገሉት የተላላፊ በሽታ ሐኪሙ  ክሩቲካ ኩፓሊ (ዶ/ር)፣ አሁን ያለው ወረርሽኝ ዓለም ከሁለት ዓመት በፊት ካጋጠመው የበለጠ የተወሳሰበ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡን ከወረርሽኙ ለመታደግ ዩኒሴፍ ከአምስት ቀናት በፊት ለኤምፖክስ ክትባቶች ግዥ አስቸኳይ ጨረታ ማውጣቱን አስታውቋል። በሁለቱም ተቋማት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) እና የዓለም ጤና ድርጅት የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ተብሎ የታወጀውን የኤምፖክስ ወረርሽኝ ለመያዝ ክትባቶች ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

የዩኒሴፍ ጨረታ ከአፍሪካ ሲዲሲ፣ ጋቪ፣ ከክትባት አሊያንስ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከፓን አሜሪካን የጤና ድርጅትና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር የኤምፖክስ ክትባቶችን በከፋ ሁኔታ ለተጎዱ አገሮች ለማዳረስ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት በአምራቾች የቀረበውን መረጃ እየገመገመ ሲሆን ግምገማውን በመስከረም የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታይም ዘግቧል፡፡

‹‹አሁን ያለውን የኤምፖክስ ​​ክትባት እጥረት መፍታትና ክትባቶችን አሁን ለሚያስፈልጋቸው ማኅበረሰቦች ማድረስ በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲሁም የክትባቶችን ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊና ግልጽ የምደባ ዘዴ በጣም አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል የዩኒሴፍ የአቅርቦት ክፍል ዳይሬክተር ለይላ ፓካላ።

‹‹የኤምፖክስ ወረርሽኝ ስንጋፈጥ፣ የክትባት ግዥና ሥርጭቱ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን በተለይም በስፋት የተጠቁ አካባቢዎችን ለመታደግ ወሳኝ ነው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ ጨረታ የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር በምናደርገው ጥረት ወሳኝ ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

አፍሪካ ሲዲሲ ክትባቶች በአኅጉሪቱ በፍጥነትና በፍትሐዊነት እንዲሠራጩ ከዩኒሴፍ፣ ጋቪ፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎች ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት የአፍሪካ ሲዲሲ ጄኔራል ዳይሬክተር ዣን ካሴያ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ‹‹የሕዝብ ጤና ላይ ድንገተኛ አደጋ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመግታትና የማኅበረሰቡን ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅ የእኛ የተዋሃደ ምላሽ ወሳኝ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ፈጣን፣ የተቀናጀና ፍትሐዊ ምላሽ የአሁኑን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ድንገተኛ አደጋ ለመቆጣጠርና ወደፊት የሚመጡትንም ለመከላከል ወሳኝ ነው፤›› ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የኤምፖክስ ምላሽ ጉዳይ ሥራ አስኪያጅና የወረርሽኞች መከላከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት  ማሪያ ቫን ከርሆቭ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

‹‹ሁላችንም አሁኑኑ ቆራጥ ዕርምጃ መውሰድ አለብን አሊያም የዝንጀሮ ፈንጣጣ የበለጠ እንዲሠራጭና የበለጠ ዓለም አቀፍ ሥጋት እንዲሆን መፍቀድ አለብን። እርስ በርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ፣ ከወረርሽኙ ጋር የሚደረገውን ትግል ልክ እንደ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችና የጤና ሥጋቶች ብቻውን ማካሄድ አይቻልም፡፡››

የአስቸኳይ ጊዜ ጨረታው የተነደፈው የኤምፖክስ ክትባቶችን ወዲያውኑ ለማግኘትና ምርትን ለማስፋት ነው። ከሚኖረው ፍላጎት በመነሳትም የአምራቾች የማምረት አቅምና ከሚኖረው የገንዘብ ድጋፍ አንፃር እስከ 2025 እስከ 12 ሚሊዮን ዶዝ ለማምረት ስምምነቶችን መተግበር ይቻላል ብሏል ዘገባው፡፡

በብራዛቪል ኮንጎ ሰሞኑን በተካሄደው በ74ኛው የአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ፣ በአኅጉሩ በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞችና ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎች እየተከሰቱ የማኅበረሰቡ ጤና ሥጋት መሆናቸው አሳሳቢነቱ ተገልጿል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ኢቦላ፣ ኮቪድ-19 እና ሌሎች ወረርሽኞች በአፍሪካ ያደረሱት ከፍተኛ ጉዳት ሳይረሳ አሁን ላይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ሌላኛው በጤና ላይ የደቀነው አደጋ ነው፡፡ በተለይ ለአፍሪካ አሳሳቢ መሆኑ በመድረኩ ተወስቷል።

ወረርሽኙን ለመግታት የመከላከያ ክትባት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ቢወሳም በአፍሪካ ግን በበቂ እየተሠራጨ አይደለምም ተብሏል፡፡

ለተፈጠረው ችግር መንግሥታዊም ሆኑ ያልሆኑ የጤና ዘርፍ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው፡፡ በተለይ የመድኃኒት አምራቾችና አቅራቢ ተቋማት የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ክትባትን በብዛት በማቅረብ እንዲተባበሩ የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አማካሪ ሔለን ሪስ (ፕሮፌሰር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) በሽታ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ አማካይነት የሚመጣ ሲሆን፣ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው፡፡ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ ዕብጠት፣ የጡንቻና የጀርባ ሕመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ከበሽታው ምልክቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ልቅ ግብረ ሥጋ ግንኙነትን ጨምሮ ንክኪ የበሽታው መተላለፊያዎች ናቸው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚሳየው፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ለመጀመርያ ጊዜ በዴንማርክ እ.ኤ.አ. በ1958 የተገኘው ለምርምር በተቀመጡ ዝንጀሮዎች ውስጥ ሲሆን፣ በሰው ልጅ ላይ የተገኘው ደግሞ በ1970 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዘጠኝ ወር ሕፃን ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠረጠረም ሆነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለ የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ በብራዛቪሉ የአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡