

የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ
ማኅበራዊ የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ወገኖች ታሳቢ ያደረገ የጳጉሜን ነፃ የጤና ምርመራ
ቀን: September 4, 2024
ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል፣ ገንዘብ ከፍለው የጤና ምርመራ ማካሄድ ለተሳናቸው ወገኖች በየዓመቱ ‹‹ጳጉሜን ለጤና!›› በሚል መርህ በነፃ የሚሰጠውን የሕክምና የምርመራ አገልግሎት፣ ዘንድሮም ከሁለት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ምዝገባ ከነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በማከናወን ላይ ነው፡፡
እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየው ይህ ምዝገባ እየተከናወነ ያለው ከፍሬንድሺፕ ፓርክ በስተጀርባ በሚገኘው በዋናው ማዕከልና በተለያዩ አካባቢዎች ባቋቋማቸው ሰባት ቅርንጫፎቹ ነው፡፡
የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ በጳጉሜን ውስጥ የሚካሄዱት ምርመራዎች የሚያተኩሩት የሲቲ ስካን፣ ኤምአርአይ፣ አልትራሳውንድ፣ ኤክስሬይ፣ ኢንዶስኮፒ፣ ክሎሮስኮፒና ጂአይ ሲሆኑ፣ በተጨማሪም ነፃ የዓይን ምርመራና የመንፅር እደላም ይካሄዳል፡፡
እነዚህን ዓይነቶች ምርመራ ለመጠቀም የሚፈልግ ታካሚ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያና ከመንግሥት የሕክምና ተቋም በሐኪም የታዘዘ ማስረጃ ይዞ መቅረብ እንዳለበት ያመለከተው ማዕከሉ፣ የምርመራውም ውጤት በማኅበራዊ ትስስር ገጽ አማካይነት ተመርማሪው እንዲደርሰው ይደረጋል ብሏል፡፡
ዓምና ለ1,500 ነፃ ታካሚዎች አገልግሎት ለመስጠት አልሞ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ወገኖች መስጠቱን፣ ዘንድሮም ከ2,000 በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች ነፃ ምርመራ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ከአቶ ዳዊት ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ማዕከሉ ከነሐሴ 24 ቀን ጀምሮ ሦስት የጤና ፓኬጆችን/ጥቅሎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ሁሉም ፓኬጆች የሐኪም ምክር፣ የላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ አልትራሳውንድና እንደ አስፈላጊነቱ እየታዩ የሚሰጡ ሌሎችም የምርመራ መሣሪያዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡
ከፓኬጆቹም መካከል ‹‹ለጤናዎ ይነሱ›› ፓኬጅ በአንድ ሰው ላይ የሚያም ነገር ባይኖርበትም፣ በራሱ ተነሳሽነት ተብሎ የሚደረግ የምርመራ ዓይነት ነው፡፡ ‹‹ጤናዎን ያረጋግጡ›› ከቤተሰብ ሐረግ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ልዩ ልዩ በሽታዎችን በመመርመርና በመለየት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ‹‹ለጤናዎ ይቅደሙ›› ፓኬጁ ደግሞ አንድ የሆነ የጤና ችግር በትንሹ ሲከሰት ሥር ሰዶ ሳይባባስና የገዘፈ የጤና እክል ከማስከተሉ በፊት ቀድሞ በመንቃት ተገቢውን ምርመራ ለማድረግ የሚረዱ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ውዳሴ ዕንቁ ብርሃን በበኩላቸው ማዕከሉ ከተቋቋመ 15 ዓመታት እንደሞላውና እስካሁንም ድረስ ከ54,000 በላይ ለሚሆኑና ከፍለው ለመመርመር የአቅም ውስንነት ላለባቸው ወገኖች ነፃ የምርመራ አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ጨረር አመንጪ የሆኑ የምርመራ መሣሪያዎች ጥቅም እንዳላቸው ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል የገለጹት የራዲዮሎጂ ሕክምና ስፔሻሊስት ተስፋዬ ከበደ (ዶ/ር)፣ እንደ እነዚህ ዓይነት ምርመራዎች ለማድረግ የሚመጡ ታካሚዎች ከሐኪም ‹‹ያስፈልገዋል›› የሚል ወይም የታዘዘበት ማረጋገጫ ይዘው መምጣት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
በተለይ ሕፃናትና ነፍሰ ጡሮች ጨረር በሚያመነጩ መሣሪያዎች በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ባይጠቀሙ እንደሚመረጥ ከስፔሻሊስቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ምርመራ መርሐ ግብሩ ይፋ ሲደረግ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አስቻለው ወርቁ (ዶ/ር)፣ መሥሪያ ቤታቸው ያስጀመረውና የውጭ አገር ሐኪሞች የተሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊሰጡ የሚችሉ ሕክምናዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከልም ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል መርህ የሚያበረክተው ነፃ የሕክምና ምርመራ የአቅም ማነስ ችግር ላሉባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ዕፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
