
ከ 4 ሰአት በፊት
ዓለም ሙሉ በሙሉ ወደ ሜታቨርስ (Metaverse) መቼ ትቀየራለች? ለሚለው ጥያቄ ብዙ መላ ምቶች ይቀመጣሉ። ምናልባትም በቀጣይ አሥርታት ልንደርስበት እንችል ይሆናል ብለው ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
አውሮፕላን ተሳፍሮ ፓሪስ ድረስ ሄዶ አይፍል ታወርን መጎብኘት ላያስፈልግ ይችላል። ከመኝታ ክፍልዎ ሳይወጡ በአንድ ‘ክሊክ’ ፓሪስን በሙሉ ቁመናዋ ያያሉ።
ከቤት ቢሮ ድረስ ሄዶ ኮምፒውተር እስከሚከፈት መጠበቅ ላያስፈልግ ይችላል። ቤት ሆነው ሁሉም ሥራ ያከናውናሉ።
ሌጎስ፣ ሮም፣ አዲስ አበባና ቶኪዮ ያሉ ጓደኛሞች በያሉበት ሆነው፣ አንድ ላይ ቡና ይጠጣሉ።
ይህንን የወደፊት ዓለም በስሱም ቢሆን የሚያሳየን የቨርችዋል ሪያሊቲ (ምናባዊ ዓለም) ጌም ነው። የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያነቡ መሣሪያዎች የተገጠሙለት ቴክኖሎጂ ይጠቀማል።
ተጫዋዎች ያሉበትን እውናዊ ስፍራ ሳይለቁ ወደምናባዊ ዓለም ገብተው ከሌሎች ሰዎች ጋር ጌም ይጫወታሉ።
ይህ በእያንዳንዱ የዕለት ከዕለት ሕይወት እንዲተገበር ተግተው እየሠሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ተቋማትም አሉ።
የእውን ዓለምን ዲጂታል ‘አቻ’ የሚሰጠው ሜታቨርስ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ዓለም ይፈጥራል? መቼስ እንደርስበታለን? የሚሉትን ይህ ዘገባ ይዳስሳል።
ስለ ሜታቨርስ ማብራሪያ የሰጠን ባለሙያ ዳንኤል ጌታቸው ይባላል። ዳንኤል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) እና በሮቦቲክስ ፒኤችዲውን እየሠራ ነው።
በተለይም በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ እና ኤክስቴንድድ ሪያሊቲ (ኤክስአር) የሚታወቀው ተቋም ‘ጉዞ ቴክኖሎጂስ’ መሥራች ነው።
ጉዞ ቴክኖሎጂስ ከሚታወቅበት አንዱ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ታሪካዊ ስፍራዎችን ቦታው የሄዱ ያህል እንዲሰማ ማድረግ የሚያስችል ምናባዊ ዓለም መፍጠር ነው።

ሜታቨርስ ምንድን ነው?
ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ወደ ሜታቨርስ ዓለም በሚደረገው ሽግግር ውስጥ የተሻለ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ፉክክር ላይ ናቸው።
ፌስቡክ መጠሪያውን ወደ ‘ሜታ’ የቀየረው ከማኅበራዊ ሚዲያ ባሻገር ወደ ሜታቨርስ የሚያደርገውን ሽግግር ለመጠቆም ነው።
ኮምፒውተር ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴ በእውን የሆነ እስከሚመስል ድረስ በሦስት አውታር (3ዲ) የሚያስቃኘውን ስፓሻል ኮምፒውቲንግ (Spatial computing) በመጠቀም የተሠራው አፕል ቪዥን ፕሮ የዓለም መነጋገሪያ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም።
ዳንኤል እንደሚለው፣ ሜታቨርስ እስካሁን አልተሠራም፤ ገና በሂደት ላይ ያለ ነው።
ምናባዊ ዓለም ወይም ምናባዊ እውነታን (ቨርችዋል ሪያሊቲ ወይም VR) የሜታቨርስ ‘የጀርባ አጥንት’ ሲል ይጠራዋል።
ቪአር ምናባዊ ነገሮችን እውን የሆኑ ያህል እንዲሰማን ያደርጋል። የቪአር ሄድሴት ስናደርግ በአካል ያልሄድንባቸው ቦታዎች ይወስደናል። በእውን ያላየናቸውን ስፍራዎች ያሳየናል። የሩቁን ያቀርባል።
ወደ ሜታቨርስ ከሚደረገው ጉዞ ጀርባ ብሎክቼይን እና ኤአይን እንዳሉ ዳንኤል ያስረዳል።
ብሎክቼይንን፣ ማዕከላዊ ያልሆነና አንድ ቦታ ብቻ ቁጥጥር የማይደረግበት በኮምፒውተሮች መካከል የሚደረግ ልውውጥ ቋት ብለን ልንተረጉመው እንችላለን።
ኤአይ፣ ማሽን በቅልጥፍናና የጥራት ደረጃ ሥራ የሚያከናውንበት ሰው ሠራሽ ልኅቀት ነው።
የብሎክቼይን እና ኤአይ ዕድገት እንዲሁም ውህደት ሜታቨርስ ወደሚለው “ትልቅ ሐሳብ” እንደሚወስደን ባለሙያው ያስረዳል።
“ከሩቅ የምናውቃቸው ቴክኖሎጂዎች አንድ እየሆኑ ሲመጡ ሜታቨርስ የሚባለውን ትልቅ ሐሳብ እናገኛለን” ይላል።
የሰው ልጆች ወደፊት የሚኖሩበት “ትልቁ ዲጂታል ሕይወት” ሜታቨርስ እንደሆነ ያስረዳል።
- በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ከኢንተርኔት ጋር ሲተሳሰሩ ዓለም ምን ትመስላለች?11 ግንቦት 2023
- ከተኙ በኋላ ስልክዎን ሳይንቲስቶች እንዲጠቀሙበት ይፈቅዳሉ?10 ጥር 2021
- ከጉግል ውጭ መጠቀም የምንችላቸው ‘የመረጃ ማሰሻዎች’ እንዳሉ ያውቃሉ?6 ሚያዚያ 2023
ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚዛመድ ንድፈ ሐሳብ በሚል የሚጠቅሰው መልቲቨርስ (Multiverse) ነው።
አሁን የምንኖርበትን ሕዋ የሚመስሉ ብዙ ተጨማሪ ሕዋዎች እንዳሉና እንደኛ ሕዋ ዓይነት ፕላኔቶችና ሕይወት ያላቸው እንደሆኑ ንድፈ ሐሳቡ ያትታል።
ሜታቨርስም በተመሳሳይ “የቨርችዋል ዓለሞች ብዛት” እንደሆነ ዳንኤል ይገልጻል።
በእውነታው ዓለም የምናውቃቸው የዕለት ከዕለት ክንውኖች፤ መማር፣ መስራት፣ መገበያየት፣ መዝናናት ወዘተ… ዲጂታል ቅርጽ ይይዛሉ።
“አንዱ ዓለም ብዙም ሊሆን ይችላል። ሌላ አገር ያለ ሰው የራሱ ዓለም ሊኖረው ይችላል። ቨርችዋል ሥራ ሊኖር ይችላል። ሰዎች ሊገናኙና ማኅበራዊ ሕይወት ሊኖር ይችላል።”
ከቨርችዋል ሪያሊቲ በተጨማሪ ኦግመንትድ ሪያሊቲ (Augmented reality)፣ ሚክስድ ሪያሊቲ (Mixed reality) ወይም ተጠቃለው ኤክስቴንድድ ሪያሊቲ (Extended reality) ተናበው የሚሠሩበት ዓለም ነው የሚሆነው።
ከአንድ ድረ ገጽ ወደ ሌላ ድረ ገጽ እንደምንሄደው ወደፊት ከአንድ ቨርችዋል ዓለም ወደ ሌላ ቨርችዋል ዓለም እንደምንሄድ ዳንኤል ያክላል።
አንድ ቀን በሜታቨርስ
ሜታቨርስ በዓለም ላይ እውን ሲሆን አሁን የምናውቀው መደበኛ አኗኗር ምን መልክ ሊኖነው ይችላል? ብለን በምናብ እንጓዝ።
ያኔ የቪአር ሄድሴቶች አሁን ካላቸው አቅም በላቀ ደረጃ ይሠራሉ። የሚያከናውኑት ሥራም እየጨመረ ይሄዳል።
እያንዳንዱን ነገር በእውን እንደምናየው ወይም እንደሚሰማን በቨርችዋል ዓለም እንኖረዋለን። አንድ ቦታ ሆነን ያሻን ቦታ መገኘት (Telepresence) የምንችልበት ይሆናል።
ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ኔትወርክ ያስፈልጋል።
ዳንኤል እንደሚለው፣ 6ጂ ወይም 7ጂ በሚል እየዘመኑ የሚሄዱ የኔትወርክ መሠረተ ልማቶች ለሜታቨርስ እውን መሆን የግድ አስፈላጊ ናቸው።
አሁን ላይ ስልክ፣ ላፕቶፕ ወይም ቴሌቭዥን የምንጠቀመው በሁለት አውታር (2ዲ) ሲሆን ወደ ሜታቨርስ ስንሻገር ሦስት አውታር (3ዲ) ይሆናሉ።
“ሜታቨርስ አሁን ያለንበት እውነተኛ ዓለም ቅጂ ስለሚሆን 3ዲ ነው የሚሆነው” ይላል ባለሙያው።
እናም በሜታቨርስ ውስጥ መንቀሳቀስ፣ ላይ ታች ማለት፣ ሰዎች መጨበጥ፣ የሰዎችን ስሜት ማንበብም ይቻላል።
“ለወደፊት አብዛኛውን ነገር ለማድረግ ከቤት መውጣት የሚያስፈልግ አይመስለኝም” ይላል ባለሙያው።
አሁን ካለው የቪአር ሄድሴት ባነሰ መነጽር ወይም ዓይን ብሌን ላይ በሚቀመጥ ኮንታክት ሌንስ አማካይነት ሐሳቡን እውን ለማድረግ እየተሞከረ ነው።
“አሁን የከበቡንና ያጣበቡን ስክሪንኖች ተወግደው የምናየው ቨርችዋል ወይም ዲጂታል ዓለም ይኖራል ማለት ነው።“
አሁን ብሔራዊ መታወቂያዎች ወይም የዜግነት ቁጥሮች እንዳሉት ሁሉ የሜታቨርስ አድራሻም ይኖረናል።
ዳንኤል እንደሚለው፣ የሜታቨርስ ግብ ያልተማከተ ሥርዓት መፍጠር ስለሆነ ሁሉም ነገር በኔትወርኩ ላይ እንዲሠራና ራሱን በራሱ እንዲያሳድግ ይደረጋል።
“ሜታቨርስ የወደፊቱ ትልቅ የኢንተርኔት ውጤት ነው” ሲል ይገልጸዋል።

ከስንት ዓመት በኋላ ሜታቨርስ ላይ ይደረሳል?
የተለያዩ ባለሙያዎች ጥቂት አሥርታት ይቀሩታል ብለው የጊዜ ገደብ በግምት ያስቀምጡለታል።
ዳንኤል “በዚህ ዓመት ውስጥ ይመጣል ብሎ መገመት ይከብዳል” ቢልም፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ “ብዙ ለውጦችን እናያለን ብዬ እገምታለሁ” ሲል ግምቱን ያስቀምጣል።
ይሄንን የሚለው የቴክኖሎጂ ተቋማት በዘርፉ እያፈሰሱ ያሉትን ገንዘብና አቅም እንዲሁም ትኩረት ከግምት በማስገባት ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ሜታ ኩዌስት3 ያሉ ዘመነኛ የቪአር ሄድሴቶች በሚሊዮኖች መሸጣቸውም ለዳንኤል አንድ ምልክት ነው።
“ሰዎች በጌም ለምደውታል። በቀጣይ ለትምህርት ወይም ለቱሪዝም ይውላል። ቀዶ ሕክምናን በአካል ከማድረግ በፊት የተማሩትን በዲጂታል መንገድ (Simulation) መሞከር የግድ ይሆናል። እናም ከአሥር ዓመት ወዲህ ብዙ ለውጥ እናያለን ብዬ አምናለሁ።”
ማይክሮሶፍት፣ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ አፕልና ሌሎችም ተቋማት የገበያ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።
ዋነኛ ትኩረታቸው የመገልገያ ቴክኖሎጂዎቹ ዲዛይን ላይ እንደሆነ የሚናገረው ባለሙያው፣ ከዚህ ጎን ለጎን የኔትወርክ መሠረተ ልማት መሻሻል እንደሚኖርበት ያስረዳል።
“አሁን የምናውቀው ኢንተርኔት እውነተኛውን ሜታቨርስ ለመሸከም በቂ አይደለም። ብዙ ሥራ ይቀረዋል” ሲል ይገልጻል።
አሁን የተዘረጋው ሥርዓት በአንድ ሰርቨር ላይ ያለን መረጃ ሰዎች ማግኘት የሚችሉበት የኢንተርኔት አሠራር ሲሆን፣ በቀጣይ የሚኖረውን ያልተማከለ የመረጃ ሥርዓት መሸከም የሚችል ፈጣን ኔትወርክ ያስፈልጋል።
ዳንኤል እንደሚለው፣ አሁን ዳውንሎድ ወይም አፕሎድ የምናደርግበት የዳታ ፍጥነት አሁን ላለው ፍላጎት በቂ ነው።
ወደፊት ግን ማዕከላዊ ባልሆነ ሥርዓት ዳውንሎድ ወይም አፕሎድ የምናደርጋቸው መረጃዎች በጣም ትልቅ ስለሚሆኑ ፈጣን ኔትወርክ ይፈልጋሉ።
ስለዚህም “6ጂ ወይም 7ጂን ልንጠብቅ ነው” ይላል።
ከዛ በኋላ፣ ሜታቨርስ ውስጥ ስንገባ፣ ዓለምን ከቨርችዋል ሕይወት ውጭ ማሰብ የሚከብድበት ደረጃ እንደርሳለን።
ሜታቨርስ “ልክ እንደ ስልካችን” ይሆናል ሲል ባለሙያው ይገልጸዋል።