Saturday, 07 September 2024 11:07

Written by  Administrator

በሶዶ ሁለት ወረዳዎች የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎችን ለማስለቀቅ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉ ተገልጿል፡፡


         ላለፉት አምስት ዓመታት ከጉራጌ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር የወጣና በታጣቂዎች የተያዘ አንድ አካባቢ እንዳለ ተነግሯል። ይህ የተነገረው ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣  ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሳኒ በንባብ ባቀረቡት መግለጫ፤ በምስራቅ መስቃን ወረዳ፣ ኢንሴኖ ዙሪያ ያለው የጸጥታ ችግር ከ5 ዓመታት በላይ መፍትሔ ሳያገኝ፣ አሁንም በአሰቃቂ ሁኔታ የንፁሃን ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መነሻው “የ11/9 ቀበሌዎች ጥያቄ” የተሰኘው በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ ወረዳዎች መካከል የተነሳው የ’ይገባኛል’ ጥያቄ እንደሆነ መግለጫው አትቶ፣ “መንግስት ይህንን ጥያቄ በአገራችን በሌሎች አካባቢዎች መሰል የ’ይገባኛል’ ጥያቄዎች በተፈቱበት ሕዝበ ውሳኔ እና ውይይት ከመፍታት ይልቅ በየጊዜው ፖለቲካዊ ፍጆታ በተጫነው ዕርቅ በማተኮሩ ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል።” ሲል ትችቱን ሰንዝሯል፡፡
በኢንሴኖ ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕጻናትን ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች፣ በጠቅላላው 44 ሰዎች መገደላቸውን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። በተጨማሪም  ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና 36 ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡
በጉራጌ ዞን የጸጥታ ችግር የተፈጠረበት “ቆስየ” የተሰኘው ሌላኛው አካባቢ መሆኑን ጎጎት አስታውቆ፣ “አካባቢው ሙሉ ለሙሉ መንግስታዊ መዋቅር ፈርሶ በጎበዝ አለቆች እጅ የገባ ነው።” ብሏል። አያይዞም፣ አካባቢው የጉራጌ ዞን አካል ቢሆንም፣ ላለፉት 5 ዓመታት ከዞኑ ቁጥጥር ውጪ በሌሎች አካላት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው ነዋሪ የነበሩ የጉራጌ ተወላጆች “ከአካባቢው እንዲሰደዱ ተደርገዋል” ያለው ጎጎት፤ “በአካባቢው ሌሎች እንዲሰፍሩበት እየተደረገ ይገኛል።” ሲል ነው የጠቆመው፡፡ በዚህም የተነሳ መንግስታዊ አገልግሎት በመቋረጡ የአካባቢው ነዋሪ ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጋለጡን፣ እንዲሁም ነባር የገበያ ቀኖች ሳይቀሩ መቋረጣቸውን ጠቅሷል።
ፓርቲው በዚሁ አካባቢ ግብር የሚሰበሰበው ይኸው ታጣቂ ሃይል መሆኑን በመግለጫው ቢያመላክትም፣ የታጣቂውን ሃይል ማንነት በይፋ አልገለጸም። ይሁንና ይኸው ታጣቂ ሃይል ቆስየ አካባቢ “የጉራጌ ዞን ሳይሆን የሃዲያ ዞን ነው” የሚል ሃሳብ እንዳለው፣ የጎጎት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሳኒ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፣ ዳርጌ አካባቢ ከዞኑ የፀጥታ ሃይል አቅም ውጪ በመሆኑ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እንዲገባ መደረጉን በዚሁ መግለጫ ሲነገር፣ በአካባቢው መደበኛ የእርሻና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ መታወካቸው ተብራርቷል። በሶዶ ሁለት ወረዳዎች የሃይማኖት አባቶችና ገዳማትን ሳይቀር ኢላማ እንዳደረገ የተነገረለት የዕገታ ተግባር በታጣቂ ሃይሎች “ይፈጸማል” ተብሏል።
ታጋቾችን ለማስለቀቅ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ብር እንደሚጠየቅ አስታውቆ፣ ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎችን ለማስለቀቂያ በድምሩ ከ2 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር በላይ ተከፍሏል  ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው፡፡ በተጨማሪም  ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 10 ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለው፤ ከ23 በላይ የሚሆኑ  ሰዎች ደግሞ ድብደባ ተፈጽሞባቸው፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ አካባቢዎች የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ የመንግስት አመራሮች እጅ “አለበት” የሚል ስሞታ ከነዋሪዎች እንደሚሰማ በመጥቀስ፣ ጎጎት ይህንን ስሞታ እንዴት እንደሚመለከተው ከአዲስ አድማስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሲመልሱ፤ “እየታሰሩና እየተፈቱ ያሉት በታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ናቸው። ችግሩ ከዚያም የዘለቀ ሊሆን እንደሚችል የራሳችን ግንዛቤዎች አሉን። ምናልባት እስከ ክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ድረስ ሊፈተሹ ይገባል። ክልሉ እነዚህን ፈትሾ ከጥቃቶችና ከሴራዎች ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ በቅጡ ለይቶ ለሕዝብ ማሳወቅና ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለን እናስባለን።” ብለዋል፡፡
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ፣ ተከታታይነት ባለው ግጭት አካባቢው እየታመሰ ይገኛል ያለው ፓርቲው፤ በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የ”11/9” ቀበሌዎች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ሕዝቡ በመረጠው ወረዳ እንዲተዳደር እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡን ጠቁሟል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፣ በቆስየ አካባቢ የተፈጠረው “ወረራ” በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መንግስት በወራሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም በአካባቢው የጉራጌ ዞን መንግስታዊ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን እንዲጀምሩም ጠይቋል።
በሶዶ ወረዳዎች፣ ማለትም በሪፌንሶ፣ አማውቴ፣ ጢያ፣ በዱግዳ ቀላ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚፈፀመው ዝርፊያ፣ ዕገታ እና አግቶ ገንዘብ መቀበል ተግባራትን ለማስቆም ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት እንዲደረግ ጎጎት  ጥሪ አስተላልፏል።
“ሕግ ይከበር፣ ሕዝብ ከጥቃት ይጠበቅ” በሚል መንግሥት ሃላፊነቱን እንዲወጣ በመቀስቀስ፣ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣታቸው ምክንያት የታሰሩ የጉራጌ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ፓርቲው በመግለጫው ጥያቄ አቅርቧል።