Saturday, 07 September 2024 11:15

Written by  Administrator

 “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕዝባዊ ቅቡልነት አንሶታል” - ዓረና

        • ጦርነት እንዳይፈነዳ ስጋት እንዳለው ገልጧል


        የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቃፊና አሳታፊ ባለመሆኑ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዳነሰው ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ ገልጿል። ፓርቲው ባለፈው  ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም  ባወጣው መግለጫ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የህወሓት የበላይነት የነገሰበት መሆኑንም አስታውቋል።
በክልላዊና አገር አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው በዚህ መግለጫው፤ በትግራይ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የተኩስ ድምጽ መቆሙ በአዎንታዊነት የሚወሰድ መሆኑን አመልክቷል። አያይዞም፣ ስምምነቱ በአግባቡ ባይፈጸምም፣ ተኩስ በመቆሙ ብቻ የክልሉ ሕዝብ በተስፋ እየኖረ መቆየቱን አትቷል።
ሆኖም ግን የህወሓት  አመራሮች ለሁለት ተከፍለው፣ አንደኛው ወገን ከኤርትራ መንግስት ጋር “ግንኙነት ፈጥሯል” ሲል የጠቀሰው ዓረና፤ ሌላኛው ደግሞ “ከፌደራል መንግስት ጋር በመሰለፍ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ የሚችል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” በማለት አብራርቷል። አክሎም፣ “ይህ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸው የስልጣን ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉት ነው። ተቀባይነትም የለውም።” ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው።
ለፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ “ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚሰራ ቡድን ‘አለ’ ያላችሁት ከምን ተነስታችሁ ነው?” በሚል ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ  ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ራሱ ይህንን ጉዳይ ገልጾታል። ሁለተኛ፣ የፌደራል መንግስት ከወራት በፊት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። በዚያን ጊዜ አንደኛውን ቡድን በስም ሳይጠቅስ፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙነት እንዳለው መረጃ አጋርቶ ነበር። እኛ ከዲፕሎማቶች፣ ከተለያዩ አካላት መረጃ አጣርተን ነው ያረጋገጥነው። ይህ ግንኙነት በተደጋጋሚና በግልጽ እየተፈጸመ ነው። ‘ሕገ ወጥ’ በተባለው የህወሓት ጉባዔም ላይ በተወሰነ መልኩ ተነስቶ ነበር። ይህ ጉዳይ መልሶ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ስለሆነ፣ እንቅስቃሴው መቆም እንዳለበትና  ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስገነዘብነው።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠንካራ አይደለም” ያሉት  አቶ አምዶም፤ “አስተዳደሩ አቃፊና አሳታፊ ባለመሆኑ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት አንሶታል” ብለዋል። “ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ፣ ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት ባለመቻሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአግባቡ እየሰራ አይደለም” ሲሉም ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።
 የህወሓት የበላይነት የነገሰበት ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን በመጥቀስም፣ “ከ90 በመቶ በላይ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ናቸው አስተዳደሩን የተቆጣጠሩት” ብለዋል።
ትግራይ ክልል ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ከሲቪክ ማሕበራት የተውጣጣ ጠንካራ የሆነ እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር መዘርጋት የሚችል ጊዜያዊ መንግስት ዳግም መዋቀር እንደሚኖርበት አቶ አምዶም ጥሪ አቅርበዋል። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሳታፊና አቃፊ መሆን እንደሚገባው አውስተው፣ “ሁለቱም ቡድኖች ወደ አካባቢያዊነት እንቅስቃሴ ማዘንበላቸው የትግራይን ሕዝብ አንድነት የሚጎዳ ነው። ትልቅ ስሕተት ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “የተፈጠረው ልዩነት ያለ ግጭት እንዲፈታ እንሰራለን” በማለት መናገራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን ያሉት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በማይጨው ከተማ ህዝባዊ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው። አቶ ጌታቸው የሚመሩትና ጄነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ያሉበት የከፍተኛ አመራሮች ቡድን ከሰሞኑ በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከቀናት በፊትም በዓዲግራት ተመሳሳይ ውይይት አድርጎ እንደነበር ተነግሯል። አመራሮቹ ወደ ማይጨው ባደረጉት ጉዞ በየመንገዱ የከተማው ሕዝብ እየወጣ እንደተቀበላቸው የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሕዝቡን እንደሚከፋፍል፣ ይህም በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጥያቄ ቀርቧል። በተጨማሪም፣ በአመራሮች መካከል የተፈጠረው ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ዓይነት አካሄድ እንዲቆምም ጥሪ ተስተጋብቷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የህወሓት ሕጋዊነትን ለሕዝብ በሚመጥንና የፕሪቶሪያን የሰላም ውል በሚያስከብር መልኩ ለመመለስ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። እርሳቸው በሚመሩትና በደብረፀዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) መካከል በሚመራው የህወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ያለግጭት እንዲፈታ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
“ከዚህ ውጭ የፕሪቶሪያን የሰላም ውል ለማፍረስ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ጦርነትን መጥራት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በተጨማሪም፣ “የተፈጠረው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ጎን ለጎን ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን “ በማለት አክለዋል።