አትሌት ያየሽ ጌጤ በፓሪስ ፓራሊምፒክ 2024 በቲ11 ምድብ ወቅር ስታሸንፍ
የምስሉ መግለጫ,አትሌት ያየሽ ጌጤ በቲ11 ምድብ የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል ወርቅ አግኝታለች

ከ 6 ሰአት በፊት

የ2024 ፓሪስ ፓራሊምፒክስ ውድድር ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የተባለ ውጤት በማምጣት አጠናቃለች።

በመጨረሻው ቀን ውድድር በአትሌቲክስ በሴቶች እና በወንዶች የማራቶን ውድድሮች ይካሄዳሉ። በማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች አይሳተፉም።

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ፓራሊምፒክስ ውድድር ላይ አራት አትሌቶችን አሰልፋ ሦስት ሜዳልያዎችን ማግኘት ችላለች።

ውድድሩ ዛሬ ፓሪስ ላይ በሚደረግ ኦፊሴላዊ መዝጊያ የሚጠናቀቅ ሲሆን እስካሁን ባለው የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ እና በ1 የብር ሜዳሊያ 43ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በፓሪስ የ2024 ፓራሊምፒክ በ1500 ሜትር በከፊል ማየት በተሳናቸው፣ ሙሉ በሙሉ ማየት በተሳናቸው፣ የእጅ ጉዳት ባለባቸው አትሌቶች ተሳትፋለች።

አትሌት ያየሽ ጌጤ በቲ11 ምድብ፣ ሙሉ በሙሉ ዓይነስውር፣ የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል ወርቅ ስታገኝ፤ ትዕግሥት ገዛኸኝ በበኩሏ በቲ13 ወይንም ‘አይነስውራን ጭላንጭል’ በሚባለው ዘርፍ ተወዳድራ ወርቅ አግኝታለች።

አትሌት ይታያል ስለሺ እንዲሁ በ1500 ሜትር በቲ 11 ምድብ የብር ሜዳልያ አምጥቷል።

አልጄሪያ በ6 ወርቅ እና በጠቅላላው በ11 ሜዳሊያ፣ ቱኒዚያ በ10 ሜዳሊያ እንዲሁም ግብፅ በ4 ሜዳሊያ የአፍሪካን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ይመራሉ። ኢትዮጵያ በ3 ሜዳሊያዎች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ወንድዬ ፍቅሬ በለንደን ፓራሊምፒክ 2012 በቲ46 1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ሲሸለም
የምስሉ መግለጫ,ወንድዬ ፍቅሬ በለንደን ፓራሊምፒክ 2012 በቲ46 1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበር

ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክስ ታሪክ

ኢትጵዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የተሳተፈችው በአውሮፓውያኑ 1968 በቴል-አቪቭ በተደረገው ውድድር ነበር። በወቅቱ በአትሌቲክስ እና በሜዳ ቴኒስ ውድድሮች ተሳትፋ ነበር።

ከዚያ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በፓራሊምፒክስ የተወዳደረችው በአውሮፓውያኑ 1976 ሲሆን ካናዳ በተካሄደው ውድድር የነበረው ብቸኛው ተሳታፊ አብራሀም ሀብቴ ነበር።

አብራሀም ከአራት ዓመታት በኋላ በ1980 ኔዘርላንድስ በተካሄደው ስድስተኛው የፓራሊምፒክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል።

ከዚህ ውድድር በኋላ ለረዥም ዓመታት በፓራሊምፒክስ ውድድር ያልተሳተፈችው ኢትዮጵያ በ2004 አቴንስ የፓራሊምፒክስ ውድድር አንድ ተሳታፊ በመላክ ተመልሳለች።

በ2008 የቤይጂንግ የፓራሊምፒክስ ውድድር ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ተወክላ ነበር።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ ውድድር ሜዳሊያ ያመጣችው በለንደን ፓራሊምፒክ ውድድር ሲሆን ወንድዬ ፍቅሬ በቲ46 1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

ከዚያ ቀጥሎ በተካሄደው የ2016 የሪዮ ፓራሊምፒክስ ውድድር 5 ተሳታፊዎችን የላከችው ኢትዮጵያ በ1500 ሜትር በታምሩ ደምሴ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው በትዕግስት ገዛኸኝ አማካይነት ነው። ትዕግስ በ2021 የቶኪዮ የፓራሊምፒክ ውድድር በቲ13 የ1500 ሜትር ውድድር አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አምጥታለች።

ትዕግስት በዘንድሮው የፓሪስ ፓራሊምፒክስ 2024 ውድድር ወርቅ በመድገም ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ታሪኳ ከፍተኛውን ውጤት እንድታመጣ አስችላለች።