የማዱሮ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ

ከ 7 ሰአት በፊት

ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የነበሩት ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ከሀገራቸው ሸሽተው ስፔን ጥገኝት እንደጠየቁ የቬንዙዌላ መንግሥት አስታወቀ።

ባለፈው ሐምሌ የተካሄደውን ምርጫ ውጤት በመቃወማቸው ምክንያት የእሥር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የነበሩት ጎንዛሌዝ ተደብቀው ነው የቆዩት።

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ብሔራዊ ምርጫ ምክር ቤት በሐምሌው ምርጫ ኒኮላስ ማዱሮ አሸኛፊ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

የቬንዙዌላው ምክትል ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጉዌዝ በኤክስ ገፃቸው በጻፉት መልዕክት መሠረት ጎንዛሌው ዋና ከተማዋ ካራካስ በሚገኘው የስፔን ኤምባሲ ተጠልለው ከቆዩ በኋላ ነው የስፔን መንግሥትን ፖለቲካዊ ጥገኝነት የጠየቁት።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ አክለው እንዳሉት ጎንዛሌዝ መንግሥት ከሀገር እንዲወጡ በመስማማቱ ምክንያት ወደ ስፔን አቅንተዋል።

የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆዜ ማኑዌል አልባሬዝ ደግሞ ጎንዛሌዝ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በስፔን አየር ኃይል አውሮፕላን ከቬንዙዌላ ወጥተዋል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የስፔን መንግሥት የቬንዙዌላዊያንን ፖለቲካዊ መብት ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን አክለዋል።

የጎንዛሌዝ ጠበቃ የሆኑ ግለሰብ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ከሀገር መውጣታቸውን አረጋግጠው ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፓርቲው መሪ ሀገር ጥለው እየሸሹ ሳለ የቬንዙዌላ የፀጥታ ኃይሎች ካራካስ የሚገኘውን የአርጀንቲና ኤምባሲን ከበው ታይተዋል።

የፕሬዝዳንት ማዱሮ ተቀዋሚ የሆኑ ስድስት ግለሰቦ በአርጀንቲና ኤምባሲ የተጠለሉ ሲሆን የቬንዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤምባሲው የሽብር ተግባር እየተሴረ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሐምሌ የተደረገው ምርጫ በማዱሮ አሸናፊነት መጠናቀቁ ከተነገረ በኋላ ዜንዙዌላ በከባድ አለመረጋጋት ውስጥ ትገኛለች።

ተቃዋሚ ፓርቲው ጎንዛሌዝ በሰፊ ልዩነት ማሸነፋቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለኝ በማለት ዝርዝር መረጃ በይነ-መረባ ላይ የለጠፈ ሲሆን በመረጃው መሠረት ማዱሮ በምርጫው ተሸንፈዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም በርካታ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ለፕሬዝደንት ማዱሮ እውቅና አንሰጥም በማለት መንግሥት የምርጫውን ዝርዝር ውጤት ይፋ እንዲያደርግ እየጠየቁ ነው።

የፕሬዝዳንት ማዱሮ መንግሥት ከምርጫው በኋላ 2400 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት በሀገሪቱ “የፍርሀት አየር ተፈጥሯል” ብሏል።

የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይገባል የሚል መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ጎንዛሌዝ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ተደብቀው ቆይተዋል።

የ75 ዓመቱ ዕጩ ባለፈው መጋቢት በተቃዋሚ ፓርቲው ዋና ዕጩ ሆነው እስኪመዘገቡ ድረስ ብዙም ታዋቂ አልነበሩም።

ከሳቸው በፊት ዕጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብለው የተገመቱት በቅድመ ምርጫው 93 በመቶ ድምፅ በማግኘት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያፈሩት ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ነበሩ።

ነገር ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ የሚነገርላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማሪያ ለምርጫ መወዳደር እንደማይችሉ መግለፃቸውን ተከትሎ ነው ፓርቲው አማራጭ ፍለጋ የገባው።

የማዱሮ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆነው ፓርቲ የጎንዛሌዝን ማንነት ደብቆት የቆየው ስማቸው ይፋ ከሆነ ለምርጫ እንዳይወዳደሩ ይታገዳሉ በሚል ስጋት ነው።

በምርጫው ምሽት ጎንዛሌዝ ከማሪያ ጋር ጎን ለጎን ቆመው ብሔራዊው የምርጫ ምክር ቤት ማዱሮ 52 በመቶ ድምፅ አምጥተው አሸንፈዋል ያለውን እንደማይቀበሉ ተናግረው ነበር።