የመጠጥ ጫና

ከ 8 ሰአት በፊት

ከ50 ዓመታት በላይ በእርግዝና ወቅት መጠጥ ጎጂ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ሲመክሩ ቆይተዋል።

እናት አንድ ብርጭቆ በሳምንት ብትጠጣ የልጅ የአእምሮ ዕድገት፣ የፊት ቅርጽ እና ባሕሪ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሳይንስ ይጠቁማል።

እናቶች ምንም ያህል መጠን ያለው መጠጥ ቢጠጡ ጉዳት አለው የሚለው ለዘመናት የተያዘ አቋም ነው።

የአልኮል መጠጥ በጽንስ ላይ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ከዕድገት ጋር የተያያዘ ተጽእኖን እንደሚያሳድር የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ይህም በልጆች ላይ የሚከሰቱ የመማር ችግር፣ በቶሎ መናገር አለመቻል እንዲሁም ሌሎችም የባሕሪ ችግሮች በውስጡ ይዟል።

እናቶች ቢጠጡ በልጆች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ሲጠና አባቶች ቢጠጡ በልጆች ላይ የሚኖረው ጫና እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።

የዕድገት ሥነ ልቦና ባለሙያ ማይክል ጎልዲንግ “ስለ ልጅ መውለድ ሲጠና ትኩረቱ ሴቶች ላይ ሆኖ ቆይቷል። ስለ ወንዶች ብዙም አልተጠናም” ይላል።

ስለ መጠጥ እና ልጆች ጥናቶችን የሚሠራ ሲሆን፣ አንዳንድ እናቶች ነፍሰ ጡር ሳሉ ባይጠጡም ልጃቸው ላይ ከመጠጥ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች እንደሚያዩ መናገራቸውን ያስረዳል።

እነዚህ እናቶች የትዳር አጋሮቻቸው “በጣም ጠጪ” መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሆኖም ግን ወይ እናቶቹ ጠጥተው ነበር ወይም አልጠጣንም ብለው ዋሽተዋል ተብሎ ይታሰብ ነበር።

በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ይህንን ለውጠዋል። እናቶቹ እንዳልዋሹ ያሳያሉ።

የመጠጥ ጫና

ልጆች ከመፀነሳቸው በፊት አባት የሚጠጣው አልኮል መጠን ጉዳት ያደርሳል የሚለው ከዚህ ቀደም አይታሰብም ነበር።

በቅርቡ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው ግን አባቶቻቸው የሚጠጡ ልጆች ለጤና እክል የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2021 የተሠራ ጥናት ግማሽ ሚሊዮን ቻይናውያን ጥንዶችን መነሻ አድርጎ እንደደረሰበት፣ የከንፈር መሰንጠቅ፣ የልብ ሕመም እና ሌሎችም ህመሞች ከአባቶች መጠጣት ጋር ትስስር አላቸው።

እናቶች መጠጥ ባይጠጡም እንኳን የአባቶች መጠጣት ተጽዕኖ ያሳድራል።

በቻይና 5,000 የልብ ሕመም ያላቸው ልጆች ከ5,000 ሕመሙ የሌለባቸው ልጆች ጋር ሲነጻጸሩ፣ አባታቸው የሚጠጣ ልጆች ለልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው በሦስት እጥፍ ጨምሮ ተገኝቷል።

አባቶቹ ከእርግዝና ሦስት ወራት በፊት በቀን ከ50 ሚሊ ሊትር በላይ የሚጠጡ ከሆነ ልጆቹ ለልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ጨምሮ ተገኝቷል።

የከንፈር መሰንጠቅ ከገጠማቸው 164,151 ሕጻናት መካከል 105 ያህሉ አባታቸው መጠጥ ጠጪ ሆነው ተገኝተዋል።

አጥኚዎቹ እንዳሉት፣ ለወደፊት አባት መሆን የሚሹ ወንዶች የሚጠጡትን አልኮል መጠን መቆጣጠር አለባቸው።

የወላጆች መጠጣት ልጆች ከመወለዳቸው ጀምሮ ያለ ህመም እንዲገጥማቸው የ31.0 በመቶ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ዘንድሮ የተሠራ ሌላ ጥናት፣ አባቶች መጠጥ ሲጠጡ የፅንስ ዕድገት ላይ ችግር እንደሚገጥም አሳይቷል።

በልጆች ላይ የተከሰተው ህመም ከአባቶች መጠጣት ጋር ብቻ የሚያያዝ ነው ወይስ ቀድሞውኑም ለህመሙ የመጋለጥ ዕድል ነበራቸው? የሚለው ሌላ አጠያያቂ ጉዳይ ነው።

የሥነ ልቦና ባለሙያው እንደሚያስረዳው፣ ጥናቶች ከግምት ሳያስገቧቸው የሚቀሩ አንዳንድ ነጥቦች አሉ።

“የሰዎች አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ሌሎችም ከግምት ሳይገቡ የሚቀሩ ነገሮች አሉ” ይላል።

የአባቶች መጠጣት ልጆች ላይ ጫና ያሳድራል በሚል መጠጥ የሚቀንሱ ወይም ጉዳቱ ውስን ነው በሚል መጠጥ የሚጨምሩ የጥናት ተሳታፊዎች ላይኖሩም ይችላሉ።

የሥነ ልቦና ባለሙያው በአይጦች ላይ ምርምር አድርጓል።

መጠጥ ልጆች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መጠን መጀመሪያ ላይ መለካት ነበረባቸው።

ከእነዚህ መካከል የዐይን መጥበብ፣ የጭንቅላት መጠን ማነስ ይጠቀሳሉ።

በቀጣይ አይጦቹን ለሁለት ቡድን ከፈሏቸው።

በአንደ ቡድን ነፍሰ ጡሮቹ መጠጥ ተሰጣቸው። በሌላ ቡድን አባቶች መጠጥ ተሰጣቸው። በዚህ ቡድን ውስጥ ነፍሰ ጡሮቹም መጠጥ ይጠጡ ነበር።

እናቶች መጠጥ በጠጡበት ቡድን ውስጥ ለአልኮል ተጽእኖ መጋለጥ ታይቷል። ይህ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጥናቶች በመነሳት የሚጠበቅ ውጤት ነው።

እናትም አባትም እንዲጠጡ በተደረገበት ቡድን ውስጥ የታየው ውጤት ግን የተለየ ነበር።

የፊት ቅርጽ እንዲሁም አጠቃላይ የሰውነት ዕድገት ላይ ችግር ተስተውሏል።

የጥርስ ክፍተት መለያየት፣ የዐይን መጠን መለያየት እና ሌሎችም የተጽእኖው ምልክቶች በልጆቹ ላይ ታይቷል።

የመጠጥ ጫና

የሥነ ልቦና ባለሙያው ማይክል “ተማሪዎቼ ምርምሩን ደግመው እንዲያደርጉ ነገርኳቸው” ይላል።

ሆኖም ግን ያገኙት ውጤት ተመሳሳይ ነው።

በዚህ ዓመት በአይጦች ላይ የሠሩትን ምርምር ተመርኩዘው፣ የአባቶች መጠጥ መጠጣት በልጆች የሚያሳድረውን ጫና የሚዳስሱ ሁለት የጥናት ወረቀቶች አሳትመዋል።

እናታቸውም አባታቸውም መጠጥ የሚጠጡ አይጦች የአእምሮ ሕዋሳቸው እና ጉበታቸው በቶሎ እያረጀ ሲሄድ ተስተውሏል።

በሰውነት ሕዋስ ውስጥ አቅም የሚሰጡ ሕዋሳት መሥራት ሲያቆሙ የሚገጥም ህመም (mitochondrial dysfunction) አይጦቹ ላይ ታይቷል።

እናትም ይሁን አባት መጠጥ የጠጡ አይጦች ላይ ይህ ቢታይም፣ ሁለቱም ወላጆች ሲጠጡ ጉዳቱ የባሰ ሆኗል።

በአልኮል ተጽእኖ የተጎዱ ሰዎች ሆስፒታል አልጋ የሚይዙት እንዲሁም በሕይወት የመኖር ዕድላቸው ከሌሎች ሰዎች አንጻር 42 በመቶ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።

የአይጦች የፊት ቅርጽ በአባት የመጠጥ መጠን የሚወሰንም ሆኖ በጥናቱ ታይቷል።

የሥነ ልቦና ባለሙያው “አባቶች ሲጠጡ ልጆች ላይ ጫና ያሳድራል ለሚለው ጥያቄ መልሱ በቀጥታ አዎ ወይም አያሳድርም አይደለም። ሆኖም የአባቶች የአልኮል መጠን ሲጨምር ጉዳቱም እንደሚጨምር አይተናል” ይላል።

ሌሎች አጥኚዎችም አይጦች ላይ በሠሩት ምርምር የአባቶች መጠጣት በልጆች የሚያሳድረውን የጤና እክል አግኝተዋል።

ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርንያ ሪቨርሳይድ ውስጥ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር ኬሊ ሀፍማን ተመሳሳይ ውጤት አግኝታለች።

እናቶች ካረገዙ በኋላ መጠጥ ሲሰጣቸው የተገኘው ውጤት ላይ የጉዳት መጠኑ የከፋ ሆኖ አልተገኘም።

“ልጆቹ በቀጥታ ለመጠጥ ስላልተጋለጡ ነው ይህ የሆነው። ቤተሰቦቻቸው መጠጥ ያልተሰጣቸው አይጦችን አንጎል ስንመለከት ግን የደረሰውን ጉዳት ማየት እንችላለን” ትላለች።

አባታቸው ብቻ መጠጥ የተሰጣቸው አይጦች መልዕክት አስተላላፊ የአንጎላቸው ክፍል ላይ የተለየ ሁኔታ ተስተውሏል።

የአይጦቹ ባሕሪ እና የሰውነት እንቅስቃሴ ብቃታቸውም የተለያየ ሆኖ ተገኝቷል።

አባታቸው መጠጥ የተሰጠው አይጦች ለመጓዝ ሲቸገሩ ወይም እንቅስቃሴን ለመማር ረዥም ጊዜ ሲወስድባቸው ታይተዋል።

“የሚማሩት በእኩል ደረጃ አይደለም። እነዚህኞቹ ዝግ ያሉ ናቸው። መንቀሳቀስን የሚያዘው የአንጎላቸው ክፍልም ዘገም ይላል” ስትል ባለሙያዋ ታስረዳለች።

ከዚህ ጀርባ ያለው ሳይንሳዊ ማብራሪያ ‘epigenetics’ የተባለ የዘረ መል ለውጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ዘረ መል ላይ የሚታይ አካላዊ ለውጥ ሳይኖር አንዳች የሕዋስ ክፍል ላይ የሚደረግ ለውጥ ነው።

መጠጥ የወንድ የዘር ፍሬ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር መደበኛው የዘረ መል እንቅስቃሴ ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህም ወደ ፅንስ ይተላለፋል ማለት ነው።

የሥነ ልቦና ባለሙያው ማይክል፣ አባቶች ሲጠጡ በወንድ የዘር ፍሬ ላይ ለውጥ ይኖራል።

ወደ ልጅ የሚተላለፈው ዘረ መል ላይም ለውጥ እንዲኖር ያደርጋል።

ሲጋራ ማጨስን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በልጆች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ጥናቶች ያሳያሉ።

የሚያጨሱ አባቶች የሚወልዷቸው ልጆች ሉኪሚያ፣ ከፍተኛ የስብ መጠን ወይም ሌላም ችግር ይገጥማቸዋል።

ወደ መጠጥ ስንመጣ፣ አባቶች ሲጠጡ ካለው ተጽዕኖ አንጻር እናቶች ሲጠጡ የሚፈጠረው ጉዳት ያመዝናል።

የልጆች ሐኪም እና የልጆች ጤና ፕሮፌሰር ኤልዛቤት ኤልየት “በእናት ሰውነት ውስጥ ያለው አልኮል በቀጥታ በደም ወደ ልጅ ይተላለፋል” ትላለች።

የሰውነት ቅርጽ እና እንደ ሳንባ፣ ልብ፣ ዐይን እና ጆሮ አሠራርን የሚወስኑ የአንጎል ክፍሎች ላይ ጫና እንደሚፈጥር ታስረዳለች።

አይጦች ላይ የሚሠሩ ምርምሮች በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሰውነት አሠራር የሚተገበሩ ስላልሆኑ፣ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ።

ሆኖም አባቶች ሲጠጡ ልጆች ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ችላ ማለት አይቻልም።

የልጆች ሐኪሟ እንደምትለው የጤና ባለሙያዎች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው።

እናቶች መጠጥ ካልወሰዱ ለልጆች ያለውን ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ አባቶችም አልኮል ቢቀንሱ እንደሚመከር ታስረዳለች። በምን ያህል መጠጥ ይቀንሱ? የሚለው ገና አልታወቀም።

የሥነ ልቦና ባለሙያው ማይክል፣ አዘውትራችሁ አትጠጡ ሲል ይመክራል።

“እኔ ወንድ ልጆቼ ከነጭራሹ ባይጠጡ ነው የምመክራቸው” ሲልም ያክላል።

ሴቶች ላይ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግ በመግለጽ “የወንዶች ጤናም ዋጋ አለው። የልጅን ጤና የመጠበቅ ኃላፊነቱ የእናትም የአባትም ነው” ይላል።