ቡጃኬራ በማካላ እስር ቤት እያለ
የምስሉ መግለጫ,ቡጃኬራ በማካላ እስር ቤት የገጠመውን ማስታወስ አይፈልግም

ከ 3 ሰአት በፊት

በቅርቡ የዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ እስረኞች ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት ማካላ እስር ቤት ለማምለጥ ያደረጉት ጥረት በመቶወች የሚቆጠሩ እስረኞችን ሕይወት ቀጥፏል።

እዚህ እስር ቤት ታስረው የሚያውቁ ሁለት ሰዎች በማካላ ያለውን ሁኔታ ለመግለፅ የተጠቀሙት ተመሳሳይ ቃል ነው። “ገሀነም” የሚል።

“ማካላ ማለት ትክክለኛው ገሀነም ነው” ይላል በዲአር ኮንጎው ትልቁ እስር ቤት ታስሮ የሚያውቀው ጋዜጠኛው ስታኒስ ቡጃኬራ።

ቡጃኬራ ባለፈው ዓመት መስከረም ነው ወደዚህ እስር ቤት የተላከው። የሀገሪቱ ጦር በአንድ ፖለቲከኛ ግድያ እጁ አለበት የሚል ፅሑፍ ፅፏል በሚል ነው ለስድስት ወራት የታሰረው።

“ማካላ እስር ቤት አይደለም። አጉሮ ማቆያ እንጂ። ሰዎች እንዲሞቱ የሚላኩበት ሥፍራ ነው” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የሚገኘው ይህ እስር ቤት 1500 ታራሚዎችን ለማስተናገድ ቢገነባም 10 እጥፍ እስረኞችን እንደያዘ ይነገርለታል።

ጥቃቅን ወንጀል ከሰሩ ወንጀለኞች ጀምሮ የፖለቲካ እስረኞች እና ነብሰ ገዳዮች በዚህ እስር ቤት ታጭቀው ይኖራሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስሩ ቤቱ ከልኩ በላይ ተጫናንቋል፤ በቂ ምግብ የለውም እንዲሁም የንፁህ ውሀ እጥረት አለ ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ከሰሞኑ በርካታ እስረኞች ለማምለጥ ሲሞክሩ መገደላቸውን ተከትሎ ነው ይህ እስር ቤት እንደ አዲስ መነጋገሪያ የሆነው።

ባለፈው ሰኞ ንጋት ግድም ነው በርካታ እስረኞች ከእስር ቤት ለማምለጥ የሞከሩት። በዚህ ሙከራ ሳቢያ 129 እስረኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ጃኪሜን ሻባኒ ተናግረዋል።

ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ሰዎች በጥይት ተመትተው ሲገደሉ በርካቶቹ ደግሞ በተፈጠረው ግርግር ሳቢያ መሞታቸውን ሚኒስትሩ አሳውቀዋል።

ከዚህ አደጋ ካመለጡ እስረኞች መካከል አራት እስረኞች ለማምለጥ ከተደረገው ሙከራ በፊት ለአንድ ቀን ተኩል ውሀም ሆነ አየር ማቀዝቀዣ የሚንቀሳቀስበት መብራት እንዳልነበረ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

አራቱ ሰዎች እንደሚሉት የተወሰኑ እስረኞች አምልጠው የወጡት ሙቀቱን መቋቋም ስላቃታቸው ነው።

ቡጃኬራ ይህ ሁሌም የተለመደ ነው ይላል። ውሀ አንዳንዴ ብቻ እንደሚመጣ የሚናገረው ጋዜጠኛው መብራት ደግሞ ለቀናት ላይመጣ እንደሚችል ያስረዳል።

“እስረኞች ዕጣ ፈንታቸው እንዲያወጣቸው ነው የተተዉት። በጣም ብዙ ሰው አለ፤ ንፅህና የማይታሰብ ነው። በሽታ ሊስፋፋ ይችላል” ይላል።

ቡጃኬራ እንደሚለው በዚህ ምክንያት እስረኞች “በየቀኑ ይሞታሉ።”

ኮንጎ የሚገኝ የሰብዓዊ መብት ቡድን ኃላፊ የሆኑት ሮስቲን ማንኬታ ተመሳሳይ ሐሳብ ያነሳሉ።

ማካላ እስር ቤትን በተደጋጋሚ የጎበኙት ኃላፊው ሰዎች ወደዚህ እስር ቤት ተላኩ ማለት “ወደ ገሀነም ተላኩ ማለት ነው” ይላሉ።

ቡጃኬራ እስር ቤት ሳለ ተደብቆ የቀረፃቸው ቪድዮዎች እና ፎቶዎች በርካታ እስረኞች ተደራርበው ሜዳ ላይ ተኝተው የሚያሳዩ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ የእስር ቤቱን የሚለያዩ ግንቦች ላይ ተኝተው ታይተዋል።

በማካለ እስር ቤት እስረኞች የሚኖሩበት ሁኔታ

ማካላ “ቪአይፒ” አለው። በርካቶች ታጭቀው ከሚኖሩበት ወጣ ብሎ ያለው ይህ እስር ቤት በገንዘብ ነው የሚሠራው። ወደ ቪአይፒ የሚመጡ አልጋ እና መንቀሳቀሻ ቦታ ይሰጣቸዋል።

ቡጃኬራ ወደዚህ ክፍል ለመምጣት 3000 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍል ቢጠየቅም በኋላ ግን በድርድር 450 ዶላር ከፍሎ መግባት ችሏል።

ሌላው የዚህ እስር ቤት መለያ የጠባቂዎች እየተዘዋወሩ ሕግ አለማስከበር ነው። በእስር ቤቱ ሕግ የሚያስከብሩት ራሳቸው ታሳሪዎች ናቸው።

“እስረኞች ራሳቸውን ነው የሚያስተዳድሩት” ሲል ከአንድ ዓመት በላይ በዚህ እስር ቤት ያሳለፈው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፍሬድ ባውማ ለቢቢሲ ይናገራል።

ይህ ራስን የማስተዳደር ሥርዓት የማይሆን እንዲሁም “ሰዎች ኃይላቸውን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ፤ በእስረኞች መካከል ግጭት እና አመፅ እንዲፈጠር የሚያበረታታ ነው” ይላል ቡጃኬራ።

በዲአር ኮንጎ ማካላ ብቻ ሳይሆን በርካታ እስር ቤቶች በቂ ፈንድ ባለማግኘታቸው ምክንያት እስረኞች በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይነገራል።

ዎርልድ ፕሪዝን ብሪፍ የተባለው ድርጅት እንደሚለው ዲአር ኮንጎ በዓለማችን ስድስተኛዋ የተጨናነቁ እስር ቤቶች ያሏት ሀገር ናት።

የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይህ ችግር እንዳለ አይክዱም። ሰኞ ዕለት ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ የፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው ሳሙኤል ምቤምባ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ለጥቃቅን ወንጀለኞች ጭምር እስር እየፈረዱ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

በርካቶቹ እስረኞች የተፈረደባቸው ሳይሆኑ ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ለወራት አሊያም ለዓመታት እስር ቤት የሚቆዩ ናቸው።

በማካላ እስር ቤት ምግብ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚቀርብ ሲሆን ይህ ምግብ ጥራቱ እጅግ የወረደ እና ለሰውነት ብዙ ጠቃሚ ያልሆነ ነው።

ቡጃኬራ ያነሳው የምግብ ፎቶ በዲአር ኮንጎ ታዋቂ የሆነው የማሽላ ገንፎ እና የአትልክት ወጥ የሚያሳይ ሲሆን ገንፎው በጣም የደረቀ እንዲሁም የአትክልት ወጡ መልኩን የቀየረ ነው።

የማካላ እስር ቤት ምግብ
የምስሉ መግለጫ,የማካላ እስር ቤት ምግብ

በርካታ እስረኞች በረሀብ ከመቀጣት እንዲሁም ከመቀንጨር ለመዳን በሚል ከቤተሰቦቻቸው ምግብ ያስልካሉ።

ነገር ግን ሁሉም እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው ምግብ ይላክላቸዋል ማለት አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 2017 በማካላ እስር ቤት 17 ታራሚዎች ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ መሞታቸውን አንድ የእርዳታ ድርጅት ተናግሮ ነበር።

ማንኬታ፤ በእስር ቤቱ ባለው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት እስረኖች ለማምለጥ ሞክረው ሊሆን ይችላል ሲሉ የሰሞኑን ክስተት ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት የተፈጠረው አደጋ ደግሞ እንዳይከሰት የሀገሪቱ መንግሥት አዳዲስ እስር ቤቶች መገንባት እና ሁኔታዎችን ማሻሻል ይኖርበታል።

አሁን መኖሪያውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ቡጃኬራ በፍጥነት ለውጥ ሊመጣ ይገባል ሲል ድምፁን ያሰማል።

በጣም “ክፉ” የፍትሕ ሥርዓት ነው የሚለው ጋዜጠኛው እስረኞች መፍትሔ እስኪመጣ ጥበቃ እየሞቱ ነው ይላል።