ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

ከ 7 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ወሰኑ።

ፕሬዝዳንቱ አርብ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ “የኢትዮጵያን ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን አደጋ ላይ ጥሎ የቆየው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሁንም የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጪ ፖሊስ ላይ የማይገመት አደጋ ደቅኗል” ብለዋል።

በዚህም ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የተላለፈው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ቁጥር 14046 ባለበት እንዲቀጥል ወስኛለሁ ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሦስት ዓመታት በፊት መስከረም 7/2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።

ትዕዛዙ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕቀባ እንዲጣል የሚፈቅድ ነው።

ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል አስተዳደር እና በህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ይህ ትዕዛዝ ለአንድ ዓመት የሚጸና በመሆኑ ውሳኔው ከተላለፈበት መስከረም 2014 ጀምሮ በየዓመቱ በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ሲታደስ ቆይቷል።

ይህ ትዕዛዝ መውጣቱን ተከትሎ የትዕዛዙ አስፈጻሚ የሆነው የአሜሪካ ግምዣ ቤት (ዲፓርትመንት ኦፍ ትሬዠሪ) በጦርነቱ ተሳታፊዎች ናቸው ባላቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ባይደን አርብ ጳጉሜ 6/2016 ዓ.ም. ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሴኔቱ ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ልዩ ትዕዛዙ ከማብቂያው መስከረም 7/2017 ዓ.ም. በኋላ ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት አንድ “ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ” ድንጋጌ የተቀመጠለት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት 90 ቀናት ውስጥ ባለበት እንዲጸና የሚያደርግ ጥያቄ ካልቀረበበት በስተቀር ተግባራዊነቱ ስለሚያበቃ ነው ፕሬዝዳንት ባይደን ደብዳቤውን የጻፉት።

መስከረም ወር መጀመሪያ 2014 ዓ.ም. ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የሚመለከት ሲሆን፣ የተለያዩ ጥሰቶችን የፈጸሙ እና ሰላም እንዳይወርድ እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ ወገኖችን ተጠያቂ ለማድረግ ፕሬዝዳንቱ ለአሜሪካ ግምጃ ቤት አስፈላጊውን ሥልጣን መስጠታቸው ተገልጾ ነበር።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአገሪቱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል።
የምስሉ መግለጫ,ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአገሪቱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል

ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት በአገሪቱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል። በኢትዮጵያም በቀጠናውም ላይ ከፍተኛ አደጋም ደቅኖ ነበር።

በዚህ ጦርነት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነው ቆይተዋል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት ኃይሎች ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ነበር።

ፕሬዝዳንት ባይደን ከሦስት ዓመታት በፊት በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ ኢትዮጵያ አሜሪካ በያዘችው አቋም የተሰማትን ቅሬታ ገልጻ ነበር።

የባይደን ትዕዛዝ መውጣን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ ነች ያሏት አሜሪካ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምትከተለው ፖሊሲ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሰብዓዊነት ከመቆርቆር የዘለለ ነው” ሲሉ ተችተው ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ፕሪቶሪያ ላይ በፈረሙት የሰላም ስምምነት ቢያበቃም አሜሪካ አሁንም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ትላለች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸውን ተከትሎ እስካሁን ከኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት አዎንታዊ እንዲሆነ የሚሰራው የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (ዘ አሜሪካን-ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ-ኮሚቴ) ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔው ለአንድ ዓመት መራዘሙን እደግፈዋለሁ ብሏል።

ቡድኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ዜጎችን ከመግደል እንዲቆጠብ ኃላፊነታቸውን መውጣት አለባቸው ብሏል።