ፊ/ማ ብርሃኑ ጁላ በምስራቅ ዕዝ 47ኛ የምስረታ ክብረ በዓል የመዝጊያ ሥነ ስርዓት ላይ
የምስሉ መግለጫ,ፊ/ማ ብርሃኑ ጁላ በምስራቅ ዕዝ 47ኛ የምስረታ ክብረ በዓል የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ

ከ 4 ሰአት በፊት

የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር በመሆን በቀጠናው ያልተገባ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ሲሉ ወቀሱ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ቅዳሜ ጵጉሜ 2/2016 ዓ.ም. በምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያ መልማት የሚያንገበግባት ታሪካዊ ጠላታችን ከሩቅ መጥታ ለሶማሊያውያን ወዳጅ መስላ ታሪካዊ ዓላማውን ለማሳካት” እየተንቀሳቃሰች ነው ብለዋል።

ምንም እንኳ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ያሏትን ሀገር በስም ባይጠቅሱም፤ ይህን ንግግራቸው የተሰማው በቅርቡ ሶማሊያ እና ግብጽ የደረሱትን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ካይሮ ጦሯን ሞቃዲሾ አስገብታ በቀጠናው ውጥረት ካየለ በኋላ ነው።

የግብጽ ጦር አውሮፕላኖች ሶማሊያ መድረሳቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ባወጣችው መግለጫ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ መደረጉ ለሶማሊያ እና ለአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው ብላለች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት “ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል” ማለቱ ይታወሳል።

ግብጽ በበኩሏ የውሃ ድርሻዬን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ “ሁሉንም እርምጃዎች ከመውሰድ ወደ ኋላ አልልም” ስትል ማሳሰቢያ አዘል ደብዳቤ ለፀጥታው ምክር ቤት ልካለች።

ግብጽ ጦር ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር ሥራ በሶማሊያ ለማሰማራት ያቀረበችው ጥያቄ በአፍሪካ ኅብረት እና በሶማሊያ ተቀባይነት ማግኘቱ ኢትዮጵያ እና ራስ ገዝ የሆነችውን ሶማሊላንድ አላስደሰተም።

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በሃይማኖት፣ በባህል እና በቋንቋ ተመሳሳይ ነች ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “ሶማሊያን የሚያስተዳድሩ መሪዎችን የኢትዮጵያን ጠላቶች ከሩቅ ጎትተው እያመጡ ሁለቱ ወንድማማቾች ሕዝቦች እየተዋጉ እንዲኖሩ” ጥረት ያደርጋሉ ብለዋል።

የኢፌድሪ የጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሶማሊያ “ከአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች የፋይናንስ፣ የስልጠና እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየተቀበለች ከሦስት ጊዜ በላይ አገራችንን ወራለች” በማለት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን አስታውሰዋል።

የሶማሊያ ባለስልጣናት “የተስፋፊነት ፖሊስ ነድፈው” ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረጓቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል ያሉት ብርሃኑ ጁላ፤ አገሪቱን “ችግር ላይ ጥለው ከ30 ዓመታት በላይ አዙሪት ውስጥ ከትተዋት ይገኛሉ” ሲሉ ወቅሰዋል።

ባለፉት 3 አስርት ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥት ለመደገፍ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ አስገብታ አሸባሪ ቡድኖችን ስትዋጋ መቆየቷን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አውስተዋል።

የሶማሊያ መረጋጋት ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ነው ብለን እናምናለን ያሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ሠራዊቱ የአገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ ትልቅ መስዕዋትነት መክፈሉን አስታውሰው፤ “ከአሸባሪ ጋር እየተዋጋ ሕይወቱ ገብሮ ስልጣናቸውን ያረጋጋላቸውን ሠራዊት እንደ ጠላት ሠራዊት ሲያወግዙ መስማት ያሳፍራል” ብለዋል።

ኤታማዦር ሹሙ፤ “ሰሞኑን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በፈጠረው ግርግር የሶማሊያ ገዢ መደብ እና ሕዝቡ የተለያዩ መሆናቸው ታይተዋል” በማለት የግብጽ ጦር በሶማሊያ መሰማራት በሶማሊያ ተቃውሞ እንደገጠመው ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባንዳ ያሏቸው በስም ያልጠቀሷቸው የአገር ውስጥ ኃይሎች፤ “የታሪካዊ ጠላቶችን አጀንዳ እያራገቡ አሳፋሪ የታሪክ ጠባሳ አሳርፎ ለማሳረፍ እየሰሩ ይገኛሉ” ብለዋል።

ፊልድማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ትንኮሳ የሚፈጽምብን እና ቀጠናውን ለማተራመስ የሚሞከር ከሆነ ራሳችን በመረጥነው፤ በራሳችን እቅድ፣ በራሳችን ሜዳ፣ በራሳችን አካሄድ ድል በመንሳት የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዝግጁ መሆናችንን ለአገራችን ሕዝብ ማረጋገጥ አወዳለሁ” ብለዋል።

“በተሳሳተ ስሌት ወደ ትንኮሳ ከገቡ በአጭር ጊዜ ድል ነስተናቸው ሉዓላዊነታችንን ማስከበር በሚያስችል ሁኔታ ዝግጁነታችንን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክረን እንድንቀጥል ላሳስብ እወዳለሁ” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።