ትዕግሥት ገዛኸኝ

ከ 8 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ፓራሊምፒክስ ውድድር ላይ አራት አትሌቶችን አሰልፋ ሦስት ሜዳልያዎችን አግኝታለች።

በፈረንሳይ ፓሪስ አዘጋጅነት በተካሄደው የ2024 ፓራሊምፒክ በ1500 ሜትር በከፊል ማየት በተሳናቸው፣ ሙሉ በሙሉ ማየት በተሳናቸው፣ የእጅ ጉዳት ባለባቸው አትሌቶች ነው ኢትዮጵያ ተወክላ የነበረው።

አትሌት ያየሽ ጌጤ በቲ 11 ምድብ፣ ሙሉ በሙሉ ዓይነስውር፣ የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል ወርቅ ስታገኝ፤ ትዕግሥት ገዛኸኝ በበኩሏ በቲ 13 ወይንም ‘አይነስውራን ጭላንጭል’ በሚባለው ዘርፍ ተወዳድራ ወርቅ አግኝታለች።

አትሌት ይታያል ስለሺ እንዲሁ በ1500 ሜትር በቲ 11 ምድብ የብር ሜዳልያ አግኝቷል።

በአጠቃላይ በዓለም የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ 43ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በፈረንሳይ ፓሪስ አዘጋጅነት በተካሄደው የ2024 ፓራሊምፒክ በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክስ ተሳትፎ ታሪክ ትልቁ የተባለለት ሜዳልያ ነው የተገኘው።

ቢቢሲ በፓሪስ ኦሎምፒክ ወርቅ ለአገራቸው ካመጡት አትሌቶች መካከል ትዕግሥት ገዛኸኝን አናግሯታል።

ትዕግሥት ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ በፓራሊምፒክስ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ በማስገኘት ታሪክ ሰርታለች።

ትዕግሥት በቶክዮም ውድድር በ1500 ሜትር T13 ምድብ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆና ነበር።

አሸንፋለሁ ብላ አስባ እንደሆን በቢቢሲ የተጠየቀችው ትዕግሥት “ሩጫ እስከሆነ ድረስ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ግን እኔ የምችለውን ያህል ልምምድ በትክክል ሰርቼ ነበር” ብላለች።

የዛሬ ሦስት ዓመት ቶኪዮ ላይ ዘንድሮ ደግሞ ፓሪስ ላይ ለአገሯ ወርቅ ያመጣችው ትዕግሥት፣ በዚህም የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊት በመሆኗ ምን ዓይነት ስሜት እንደፈጠረባት ስትናገር “በጣም ደስ ነው ያለኝ። ውድድሩ ላይ የቻልኩትን ያህል ለመሄድ እሞክራለሁ ብዬ ነበር የገባሁት። በማሸነፌ በጣም ደስ ብሎኛል” ብላለች።

በሰሜን ሸዋ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ኢላኒ ቀበሌ የተወለደችው አትሌት ትዕግሥት ገዛኸኝ ወደ ሩጫ የገባችው በ2006 ዓ.ም መሆኑን ትናገራለች።

በመሀል አቋርጣ የነበረ ቢሆንም ዳግም በ2007 ወደ ስፖርቱ ተመልሳለች።

ከዚያ በኋላም በ2009 ዓ.ም. ደብረ ብርሀን ከተማ አትሌቲክስ ክለብ በመግባትም ስልጠናዋን አጠናክራቀጠለች።

በዚያው ዓመት በተካሄደ የወረዳ ውድድር በ 6ኪ.ሜ. የፓራሊምፒክ ወረዳዋን አንጎለላና ጠራ ወክላ ተወደድራ 1ኛ በመውጣት ለወረዳዋ ዋንጫ በማስገኘት የአሸናፊነት ድልን ማጣጣም ጀመረች።

ከዚያም ወደ ዞን እንዲሁም ክልል በመሮጥ የአሸናፊነት ዋንጫን አነሳች።

ከዚያ በኋላ ነው በፌደራል ደረጃ በፓራሊምፒክ የተለያዩ ውድድሮች እየተሳተፈችና እየተወዳደረች ጉዞዋን የቀጠለችው

ደብረብርሃን እየሰራች ከቆየች በኋላ በ2011 ኦሜድላ ክለብ ገባች። በ2014 ዓ.ም። ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ልምምዷን መስራት ቀጠለች።

አትሌቷ ከዓመታት በፊት በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር በ1,500 ሜትር ጭላንጭል ለሀገራችን የመጀመሪያ የ ፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችበት ነበር።

ትዕግሥት አሁን ላይ ለ 17ኛ ጊዜ በተካሄደው የ 2024 ፓሪስ ፓራሊምፒክ ውድድር ለአገሯ የወርቅ ሜዳልያ ማሳካት ችላለች።

በዚህም አትሌት ትዕግሥት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ ውድድር ታሪክ ለኢትዮጵያ እና ለራሷ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።

ትዕግሥት ገዛኸኝ በፓሪስ ኦሎምፒክ ካሸነፈች በኋላ

የአካል ጉዳተኛ አትሌቶች ያለባቸው ችግር

አትሌት ትዕግሥት መጀመርያም ልምምድ የምትሰራው ከጉዳት አልባዎች ጋር ነበር።

“ልምምድ የማደርገው ከጉዳት አልባዎች ጋር ነበር። ከጉዳፍ ጋር ነው የምለማመደው።”

ከጉዳት አልባዎች ጋር መሰልጠኗ እንደጠቀማት የምትናገረው ትዕግሥት

“የእኔ ጉዳት በከፊል ስለሆነ፣ በከፊል ማየት ስለምችል፣ ከአጠገቤ ሰው ካልራቀ ለእይታ አልቸገረም። አብሬያቸው እያለሁ ምንም አልልም። አንዳንዴ መደነቃቀፍ ቢኖርም፣ ጓደኞቼም ስለሚያውቁ ይጠብቁኛል። ያበረታቱኛል። ስለዚህ ያለምንም ችግር ልምምዴን እየሰራሁ ነው። ውድድርም ሲኖር በጉዳት አልባ እወዳደራለሁ” ትላለች።

ከአትሌት ጉዳፍ እንዲሁም ሌሎች ጉዳት አልባዎች ጋር መስራት የሰጣትን ጥቅም ስታስረዳ

“ከተሻለ ሰው ጋር ስትሰራ የተሻለ ሞራል፣ የተሻለ መነቃቃትም ይኖራል። እኔ ከእነርሱ ጋር እየሰራሁ ባለሁበት ብዙ ነገር ነው ያገኘሁት። ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝ፣ መሰልቸት እንደሌለብኝ፣ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብኝ ሁሉ ተምሬበታለሁ፤ ከእነርሱ ጋር በመስራቴ”

ትዕግሥት በክለብ ታቅፋ ትስራ እንጂ ይህ ዕድል የሁሉም አካል ጉዳተኛ አትሌቶች አለመሆኑን ታዝባለች።

“የአካል ጉዳተኛው ስፖርት በርካታ ችግሮች ነው ያሉበት። ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ ማየት የማይችሉ፣ የእግር የእጅ ጉዳት ያለባቸው አሉ። በስፖርቱ ውስጥ ብዙ ዓይነት የአካል ጉዳተኛ ነው ያለው። እነዚያ ሁሉ አንደኔ እድል አግኝተው ለመስራት ትንሽ ከባድ ነው። አሁን ሙሉ በሙሉ የአካል ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች እንደኔ ጫካ ውስጥ ከጉዳት አልባዎች ኣገር ለመስራት ይቸግራቸዋል”

በ2012 የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክስ አትሌቶችን አሰልጣኝ በመሆን በለንደን ኦሎምፒክ ላይ የተሳተፈው ወንድሙ ቀኖ በአትሌት ትዕግሥት ሀሳብ ይስማማል።

በኢትዮፕያ ውስጥ ለአካል ጉዳተኛ አትሌቶች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የሚናገረው አሰልጣኝ ወንድሙ፣ የመሰልጠኛ ስፍራ፣ ትጥቅ፣ እንዲሁም በጀት ችግር እንዳለባቸው ይናገራል።

ለዚህም ምክንያቱ በቅድሚያ የአመለካከት መሆኑን በማንሳት “ለአካል ጉተኞች የሚሰጠው ግምት አነስተኛ በመሆኑ ስፖርቱ በኢትዮጵያ ሊስፋፋ አልቻለም” እላሉ።

የዘንድሮው ውጤት የተገኘው በፕሮጀክቶች፣ በአንዳንድ ክለቦች ድጎማ እና በዩኒቨርስቲዎች ድጋፍ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

መንግሥት ለአካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች “ተገቢውን ትኩርት ቢሰጥ” ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አሰልጣኝ ወንድሙ ቀኖ ይናገራሉ።

አትሌት ትዕግሥት በበኩሏ “የአካል ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች ይዞ የሚያሯሩጣቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ከጉዳት አልባም ጋር ለመስራት አይችሉም። ብቻቸውንም ለመስራት አሰልጣኝም፣ ከጎናቸው ሆኖ የሚያግዛቸው፣ ክለብም ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ክለቦች ለጉዳት አልባ ተብለው የተቋቋሙ እንጂ ለአካል ጉዳተኞች የለም።” ትላለች።

አክላም “አሁን ያሉት የአካል ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች የታቀፉት ከጉዳት አልባዎች ጋር ተቀይጠው ነው። ጥሩነሽ፣ ወጣት ስፖርት አካዳሚ፣ ሱሉልታ ነው ትንሽ ትንሽ ልጆች ይዘው ያሉት። እዚያ ያለቸውን ቆይታ ጨርሰው ሲወጡ ግን የሚቀበላቸው፣ የሚያግዛቸው፣ የሚያሰራቸው፣ የሚያበረታታቸው ሰውም ሆነ ክለብ ስለሌለ አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠው አቋርጠው የወጡ አሉ። እናም የአካል ጉዳተኛ ስፖርት ላይ ችግር አለ” ትለላች።

“የአጭር እና መካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ወንድሙ ቀኖ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ዘንድሮ የተገኘው ውጤት “አስደሳች” እንደነበር ጠቅሰው የፓራሊምፒክ ‘የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች፣ ማሰልጠኛዎች፣ አካዳሚዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ይመክራሉ።

የዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክስ ኮሚቴ እንደሚለው ከሆነ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በፓራሊምፒክስ መሳተፍ የጀመረችው በ1968ቱ የቴላቪቭ ፓራሊምፒክስ ውድእድር ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው በ2012ቱ ለንደን ኦሎምፒክ በአትሌት ወንድዬ ፍቅሬ ነበር።

ከዚህ በኋላእኤአ በ2016 በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ ታምሩ ከፍያለው በ1500 ሜትር ሁለተኛ ሆኖ በመጨረስ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

ከዚያ በኋላ ትዕግሥት ገዛኸኝ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመጀመርያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ወርቅ አስገኝታለች።

ትዕግሥት ዘንድሮ በፓሪስ ኦሎምፒክ ያገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ ለራሷ ሁለተኛው ነው።