በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ

ዜና የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች የሁለት ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ ለማቅረብ ተስማማ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: September 8, 2024

የኮሪያ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ልማት ትብብር ፈንድ አስፈጻሚ ኤጀንሲው በሆነው ኤግዚም ባንክ በኩል፣ ለኢትዮጵያ ስምንት ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ ለማቅረብ መስማማቱ ታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ ግንቦት 21 ቀን 2024 የኢትዮጵያ መንግሥት በኤግዚም ባንክ በኩል ፋይናንስ እንዲደረጉ ቅድሚያ የሰጣቸውን ፕሮጀክቶች ዝርዝር አቅርቧል።

በባንኩና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ተከታታይ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ፣ በሁለቱም አካላት ስምምነት በፈንዱ በኩል በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ስምንት ፕሮጀክቶች መመረጣቸው ታውቋል።

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ እያንዳንዱን ፕሮጀክት ዝርዝር የመግለጽ መብት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሕክምና ተቋማት ግንባታና የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ብድር ለማግኘት የሚፈልግባቸው ፕሮጀክቶችን ዝርዝር አቅርቦልናል። ነገር ግን ከዚህም በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገራችንን በጎበኙበት ወቅት ፋይናንስን የተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን ነበር። ይህ ስምምነት የኮሪያ መንግሥትን በአምስት ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ 10 ቢሊዮን ዶላር ማበደር የሚያስችለው ነው። ነገር ግን ይህ መጠን ሌሎች የምናምንባቸው ፕሮጀክቶች ከሆኑ ጭማሪ ሊደረግበት የሚችል ነው፤›› ብለዋል።

ኮሪያ ለኢትዮጵያ ገንዘብ ማቅረብ እንድትችል በቅድሚያ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ይዘት ላይ ሁለቱ መንግሥታት ከስምምነት መድረስ እንደሚኖርባቸውም ጠቅሰዋል።

ባለፈው ሳምንት ከገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዩች ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ የተገኘው የኮሪያ መንግሥት ልዑካን ቡድን፣ ስለፕሮጀክቶቹ መወያየቱን የተናገሩት አምባሳደሩ፣ በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ ለማቅረብ የተስማሙባቸው ፕሮጀክቶች አዳዲስ የተቀረፁ መሆናቸውንም ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያቀርበው ፋይናንስ የተወሰነው በብድር፣ እንዲሁም በድጋፍ የሚሰጠውንም በጥምረት የያዘ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ካንግ፣ የትኛው ፕሮጀክት ምን ዓይነት የፋይናንስ ሁኔታ ይኖረዋል የሚለውም እንደ ፕሮጀክቱ እንደሚወሰን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ የኮሪያ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ በትራንስፖርትና ኢነርጂ ዘርፎች ላይ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚያደርግ ይጠቁማል።

አምባሳደር ካንግ አውቶቡስን መሠረት ያደረገ የሕዝብ ትራንስፖርት ፕሮጀክት (Bus Rapid Transit/BRT Project) እንደሚደግፍ ገልጸው፣ ይህም ለኢትዮጵያ በሚቀርበው ብድር መርሐ ግብር ውስጥ መካተቱን አሳውቀዋል።