September 8, 2024 

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ትኩሳት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የፈጠረው ጫና

ባለፈው ሃምሌ ወር የኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ ከመስከረም 20 ጀምሮ እንዲያቆም የሚያዝ አንድ መስመር ደብዳቤ ከላከ በኋላ በአስመራ የሚገኘው የአየር መንገዱ የባንክ ሂሳብ በመታገዱ አየር መንገዱ በረራውን ለማቋረጥ እንደተገደደ አስታውቋል።

በ1990 ዓ/ም ግንቦት ወር የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከፈነዳ በኋላ ለ20 አመት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ- አስመራ በረራ የጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በሁለቱ ሃገሮች መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ አየር መንገዱ ከሃምሌ 2010 ዓ/ም ጀምሮ ኤርትራን ከመላው አለም በአየር ትራንፖርት በማስተሳሰር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

የተቆራረጡ ቤተሰቦችን አገናኝቷል፣ አስመራን ካሉት 140 የአለም አቀፍ መዳረሻዎች እና በስታር አሊያንስ አባልነቱ ከቡድኑ 26 አባል አየር መንገዶች ጋር በመተባበር የኤርትራ መንገደኞች ወደ ተለያዩ ክፍለ አለማት እንዲበሩ ሰፊ አማራጭ ሲያቀርብ ቆይቷል።

ለዚህም እገዳውን ከመጣሉ ሁለት ሳምንት በፊት የኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ምልልሱን እንዲጨምር እና ከፍ ያለ አውሮፕላን አንዲጠቀም መጠየቁ አየር መንገዱ ስለሚሰጠው የአየር ትራንፖርት አገልግሎት ጠቀሜታ አንድ ማስረጃ ነው።

ይሁን እንጂ አየር መንገዱ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል እና ሻንጣ ይጠፋል የሚል ቅሬታ ይደመጣል።

የአየር ትኬት ዋጋ የሚወጣበት የራሱ አሰራር አለ። ከግምት የሚገቡት የነዳጅ ዋጋ፣ የኤርፖርት ማረፊያ ክፍያ፣ የግራውንድ ሃንድሊንግ እና የኤር ናቪጌሽን ክፍያዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

አንድ አየር መንገድ ዋጋው ውድ በመሆኑ አይታገድም፣ ወደ አስመራ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ አይደለም። የግብፅ አየር መንገድ፣ ተርኪሽ፣ ፍላይ ዱባይ እና የሳኡዲው ናስ ኤር ወደ አስመራ ይበራሉ።

አንድ መንገደኛ ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ መብረር ቢፈልግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ በግብፅ ወይም ተርኪሽ አየር መንገዶች ዋጋው በሚቀንስለት አማርጦ መብረር ይችላል።

ከአስመራ- አዲስ አበባ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ በመሆኑ የቲኬት ዋጋው ወደድ ይላል፣ ይህም ያለውን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚሰራ የተለመደ የአየር መንገዶች አሰራር ነው።

ሻንጣን በተመለከተ የኤርትራ መንገደኞች ቤተሰብ ጥየቃ እና በተለይ ለንግድ የሚጎዙ መንገደኞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሻንጣዎች ስለሚይዙ ከአውሮፕላኑ አቅም በላይ እየሆነ ሻንጣዎች ከመንገደኛው ጋር ሳይጫኑ እየቀረ ቅሬታን ሲፈጥር መቆየቱ ይታወቃል። ይህን ችግር ለመፍታት አየር መንገዱ ከፍ ያለ አውሮፕላን መድቦ ነበር፣ በቲኬት ዋጋም ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

እነዚህ የተጠቀሱት ምክኒያቶች ግን አንድ አየር መንገድን ለማገድ አሳማኝ አይደሉም፣ ምክኒያቱም በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ በመሆናቸው ጉዳዩ ከአየር መንገዱ አሰራር ጋር ሳይሆን በሁለቱ መንግስታት መካከል በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቅራኔ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ቀጣዩ ስጋት ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ክልሏን እንዳይጠቀም እንዳትከለክል ነው።

አየር መንገዱ በአብዛኛው የአሜሪካ፣ አውሮፖ እና መካከለኛው ምስራቅ በረራዎች የሚያልፉት በኤርትራ የአየር ክልል ውስጥ ነው። በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት በሱዳን የአየር ክልል ሲጠቀም የቆየ ቢሆንም ሱዳን የምታስከፍለው overflight fee የተጋነነ በመሆኑ ከ2010 ዓ/ም በኋላ አየር መንገዱ የኤርትራን የአየር ክልል ሲጠቀም ቆይቷል።

የጅቡቲን ኮሪደር የሚጠቀመው ደግሞ ለዱባይ፣ ለመስካት፣ ለእስያ እና ለሩቅ ምስራቅ በረራዎች ነው።

የሱዳን የአየር ክልል ውድ ከመሆኑ ባለፈ እየተካሄደው ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክኒያት የአየር ክልሉ ዝግ ነው። በእርግጥ የኤርትራው ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ወደ አስመራ አትብረሩ እንጂ የአየር ክልል እገዳ አልጣለም፣ ነገር ግን በቀጣይ የሚሆነው አይታወቅም እና አማራጭ መንገዶችን ከአሁኑ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

በዚህ በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን አስፈላጊውን ስራ መስራት ይጠበቅበታል።

ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በኢትዮጰያ እና ሶማሊያ መንግስታት መካከል በተፈጠረው የዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ የሞቋዲሾ መንግስት አየር መንገድ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል። የሶማሊያ መንግስትም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ ስለሚችል ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ቢደረግ መልካም ነው።

አየር መንገድ የማንኛውንም ሃገር የአየር ክልል ሲያቋርጥ በውጪ ምንዛሬ ክፍያ ይፈፅማል፣ በአመት ለኤርትራ የሚከፍለው የoverflight እና ኤርናቪጌሽን ክፍያ ቀላል አይደለም። ለሶማሊያም እንደዛው ቢሆንም ፖለቲከኞች ሲጣሉ እልሃቸው ህዝብ እና ሃገር የሚያጣው ነገር አይታያቸውም፣ አንዳች ነገር ይጋርዳቸዋል።

በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ዘርፈ ብዙ የሆነ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ግልፅ ነው፣ ለዚህ ደግሞ በጡረታ የተገለሉ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ማማከር ብልህነት ነው።

*ለፅሁፉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለን ከልብ እናመሰግናለን።