ዜና
በጉራጌ ዞን የተከሰተው ችግር ከፀጥታ ኃይሉ አቅም በላይ መሆኑ ተገለጸ

ፅዮን ታደሰ

ቀን: September 8, 2024

ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ

በወሰን ማስከበርና በሌሎችም ምክንያቶች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን የተከሰተው የፀጥታ ችግር ከዞኑ የፀጥታ ኃይል አቅም በላይ በመሆኑ፣ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት ሥር አንደሚገኙ ተገለጸ።

ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) በዞኑ ያለውን የፀጥታ ችግርና የወሰን ማስከበር ሒደት አስመልክቶ ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የዞኑ የፀጥታ ችግር በአፋጣኝ ዕልባት ሊያገኝ ይገባል ብሏል፡፡ ከአምስት በላይ የሚሆኑ የዞኑ አካባቢዎች ከተከሰተው የፀጥታ ችግር አኳያ ቋሚ የፀጥታ ኃይል ሥምሪት የሚፈልጉ መሆናቸውን ፓርቲ ገልጿል፡፡

በዞኑ የሚገኘው የኢንሴና ዙሪያ የፀጥታ ችግር ከአምስት ዓመታት በላይ መፍትሔ ሳያገኝ የቆየ መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በአሰቃቂ ሁኔታ የንፁኃንን ሕይወት የሚቀጥፍ ምክንያት ሆኖ መቀጠሉን ፓርቲው በመግለጫው ጠቁሟል። መንግሥት በሌሎች አካባቢዎች ያጋጠሙ መሰል ችግሮችን በፈታበት መንገድ በሕዝበ ውሳኔና በውይይት ከመፍታት ይልቅ፣ የፖለቲካ ፍጆታ በተጫነው ዕርቅ ላይ በማተኮሩ ሳይፈታ መቅረቱን የጎጎት መግለጫ ይጠቅሳል። 

ከመጋቢት 21 አስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕፃናትን ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች በጠቅላላው 44 ሰዎች መገደላቸውን፣ 6,000 ሺሕ በላይ የሚሆኑት መፈናቀላቸውንና 36 ሰዎችም በእስር ላይ እንደሚገኙ ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በዞኑ የፀጥታ ችግር ያለበት ‹‹ቆስየ›› የተሰኘው አካባቢም፣ መንግሥታዊ መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ መፍረሱንና በጎበዝ አለቆች አየተዳደረ እንደሚገኝ በመግለጫው ተካቷል፡፡

በአካባቢው በታሪክ የጉራጌ ዞን አካል ቢሆንም ላለፉት አምስት ዓመታት ከዞኑ ቁጥጥር ውጪ በሌሎች አካላት ቁጥጥር ሥር እንደሆነ፣ ሌሎች እንዲሰፍሩ በማድረግ ጉራጌዎች ከአካባቢው አንዲሰደዱ ተደርገዋል ያለው ጎጎት፣ ግብር የሚሰበስበውም ከዞኑ ውጪ ያለ አካል ነው ብሏል፡፡  

ዳርጌ በተሰኘው አካባቢ ያለው የፀጥታ ችግርም ከዞኑ የፀጥታ ኃይል አቅም በላይ በመሆኑ፣ የመከላከያ ሠራዊት እንዲገባ መደረጉንና መደበኛ የእርሻና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ፓርቲው አክሏል፡፡ በሶዶ ወረዳዎች የሚገኘው ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊት ጥበቃ የሚፈልግ ሆኗል የሚለው የጎጎት መግለጫ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ቢደራጁም በተቀናጀ ሁኔታ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቋል። 

በአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና ገዳማውያንን ሳይቀሩ ዒላማ ያደረገ ዕገታ መንሰራፋቱንና ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ነዋሪዎችን ለማስለቀቅ ከ2.9 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉ በመግለጫው ተመላክቷል። በወሰን ማስከበር ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረበት የወልቂጤ ከተማም ሌላው በዞኑ የፀጥታ ችግር ውስጥ የገባ አካባቢ መሆኑን፣ በከተማው የሚፈጸመው የወሰን ጥሰትና ሕገወጥ እንቅስቃሴ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ጎጎት በመግለጫው አስታውቋል። 

ከወልቂጤ የወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ከአሥር በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን የገለጹት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ እንዳለ ንዳ፣ እስከ ስድስት ወራት ታስረው በዋስትና እንደሚለቀቁና አንዳንዶችም በተራዘመ የክስ ሒደት አሁንም በእስር ላይ አንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ወልቂጤ የጉራጌ ዞን መቀመጫነቷ በሕግ የተደነገገ ቢሆንም፣ ይህ ተግባራዊ አይደለም። ከዚህ በፊት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ቆስየ በጉራጌ ዞን ሥር እንዲሆን ቢወሰንም፣ አካባቢው የሃድያ ዞን ነው የሚሉ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ቡድኖች አሁንም አካባቢውን አያስተዳደሩ ነው ያሉት፤›› ብለዋል። 

‹‹ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂ ሲሆኑ የምንመለከታቸው በታችኛው መዋቅር ሥር ያሉ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ እንዳለ፣ ነገር ግን እስከ ክልል ድረስ ያሉ አመራሮች ሊፈተሹ እንደሚገባ አሳስበዋል። ‹‹በቀላሉ በቁጥጥር ሥር መዋል የሚችሉ ግጭቶች ናቸው በቸልተኝነት ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲባባሱ እየተደረገ ያለው። ሆኖም መንግሥት ሲፈልግ መቆጣጠር እንደሚችል ይታወቃል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡