ፅዮን ታደሰ

September 8, 2024

ሽፈራው ተሊላ (ኢንጂነር)

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመሆን ለሚያከናውናቸው የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሻሻያ ሥራዎች የሚውል 545 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ መገኘቱን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህንን ያስታወቀው የ2016 ዓ.ም. አፈጻጸምንና በ2017 ዓ.ም. የትኩረት መስኮች፣ እንዲሁም አዲሱን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ አስመልክቶ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ነው፡፡  

መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ (ኢንጂነር)፣ በ72 ከተሞች ቀደም ሲል የተጀመሩ የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሻሻያ ሥራዎችን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ለመሥራት የሚያስችል የ545 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንና የአቅም ውስንነት ያለባቸውን የማከፋፈያ ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም አገልግሎቱ በከተሞች ውስጥ ያለውን መሠረተ ልማት እንደሚገነባ አስታውቀው፣ የተገኘው ብድር ሁለቱ ተቋማት ለሚያከናውኑት ሥራ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት የሚውል የግዥና የኮንትራክተሮች መረጣም በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ 

የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ታሪፍ ማሻሻያውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው፣ ተቋሙ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሥራት አቅም አንዲኖረው ለማስቻልና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ከግንዛቤ ማስገባት የሚሉ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የተደረገ ማሻሻያ መሆኑን አስታውቀዋል። 

የመኖሪያ ቤት፣ የንግድ፣ የአነስተኛ ኢንዱስትሪ፣ መካከለኛ ኢንዱስትሪና የመንገድ መብራት በሚል የተከፈሉ አምስት ዓይነት የኃይል ተጠቃሚ የታሪፍ ዓይነቶች እንዳሉ፣ በመኖሪያ ቤት ታሪፍ ላይ አስከ 50 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቀሙ ደንበኞች የተደረገውን ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ እንደማይከፍሉ፣ ከዚህ ቀደም ሲከፍሉ በነበረው ዋጋና በማሻሻያው መካከል ያለውን ጭማሪ 75 በመቶ ድጎማ አንደሚደረግበትና 25 በመቶውን ብቻ እንዲከፍሉ ይደረጋ ብለዋል። 

ከ51 አስከ 100 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቀሙም በማሻሻያው የተጨመረው ዋጋ ላይ 40 በመቶ ድጎማ አንደሚደረግላቸው ገልጸው፣ ከ101 አስከ 200 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቅሙት ደግሞ አራት በመቶ ድጎማ አንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል። የኃይል ማመንጫ ዋጋ በመጨመሩ ብቻ የተጨመረው ታሪፍ (Cost Reflection Tariff) በአንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ከአራት ዓመታት በኋላ 6.01 እንደሚሆን ሽፈራው (ኢንጂነር) ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ከ12 ዓመታት በኋላ በ2010 ዓ.ም. ማሻሻያ እንደተደረገበትና ይህም አስከ 2014 ዓ.ም. ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ማሻሻያ ባለመደረጉ ተቋሙ የፋይናንስ ጫና ውስጥ መውደቁን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሠረተ ልማቶችን በብድር የሚገነቡ መሆናቸውን የገለትጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ተቋማቱ ጤናማ የፋይናንስ ቁመና ላይ አንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንና ከእነዚህ ውስጥም የኃይል ፍጆታ ታሪፍ ማሻሻያው አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይዞት የሚመጣው ጫና ቢኖርም ለተቋማቱ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅም እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል። ከማሻሻያው በፊት ውል የወሰዱ ኮንትራክተሮች የዋጋ ማሻሻያ መጠየቃቸውን ጠቁመው፣ ‹‹የውል ስምምነቱ ላይ የዋጋ ማሻሻያ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲፈጠር ማሻሻያውን ለማድረግ የሚፈቅድ ከሆነ ይደረጋል። እስካሁንም ሁለት ሦስት የሚሆኑ ትልልቅ ኮንትራክተሮች ጠይቀዋል፤›› ብለዋል።