ዜና ኢዜማ ለሌሎች ፓርቲዎች ጭምር የአመራር ሥልጠና መስጠት የሚያስችል አካዴሚ መገንባቱን ይፋ አደረገ

ዮናስ አማረ

ቀን: September 8, 2024

ለአባላቱ የአመራር ሥልጠና የሚሰጥ አካዳሚ መገንባቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ ለሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትም ቢሆን ሥልጠና እንደሚሰጥ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በዕውቀት፣ በእውነት፣ በስክነትና በምክንያት እንዲመራ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ የተናገረው ኢዜማ፣ የራሱን የማሠልጠኛ አካዴሚ አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃ ላይ መገንባቱን አስታውቋል፡፡

ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ በተዋጣ አሥር ሚሊዮን ብር በጀት ገነባሁት ያለው ማሠልጠኛ አካዴሚ፣ የተማሪዎች መማሪያ፣ ማደሪያና ላይብረሪ እንዳለው ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችም አባሎቻቸው እንዲሠለጥኑ ከፈለጉ፣ የአመራርነት ሥልጠናው በአካዴሚው ለመስጠት ዝግጁና ፈቃደኛ መሆኑንን ገልጿል፡፡

ከፖለቲካ አመራር ማሠልጠኛ አካዴሚ ግንባታ ጎን ለጎን ፓርቲውን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚሰጥ አንድ ወጥ የመረጃ ቋት ወይም ዌብ ሳይት ገንብቶ ማጠናቀቁንም ተናግሯል፡፡ ኢዜማ ገነባሁት ያለው የመረጃ ቋት የድርጅቱ አባላትን በአግባቡ ለመመዝገብ፣ በፆታ፣ በቦታ፣ በትምህርት፣ በሙያና በሌሎችም ዝርዝር መረጃዎች ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ ብቻ ሳይሆን፣ ከድርጅቱ የሚወጣውንና ወደ ድርጅቱ የሚገቡትን ሰዎች በቀላሉ ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ከአባላት ምዝገባና መረጃ አያያዝ በተጨማሪ ከደጋፊዎቹና አጋሮቹ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚረዳ፣ በቀላሉ ጥቅም ላይ የሚውል ድረ ገጽ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የአባላት ሁኔታና ዝርዝር መረጃ የሚከታተለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ ስለፓርቲው መረጃ የሚፈልጉ ሰዎች፣ በዚህ የእጅ ስልክ መተግበሪያ ባለው የመረጃ ቋት ማወቅ እንደሚችሉም አመልክቷል፡፡

የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ ዮሐንስ መኮንን፣ የሥራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሙሉዓለም ተገኝወርቅ (ዶ/ር) በጋራ በመሆን ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ፣ ስለፓርቲው ዓመታዊ ኮንፍረስ በሰፊው ተነስቶ ነበር፡፡ ከሥልጠና አካዴሚና ከመረጃ ቋት ግንባታ በተጨማሪ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሦስቱ የድርጅቱ አመራሮች፣ የፓርቲው አባላት ስለሚለቁበት ሁኔታ፣ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና መረጃ አሰጣጥ፣ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር መሠልጠንና በዕውቀት መመራት ጉዳይ ማብራሪያ ያሉትን በርካታ ሐሳብ አንስተዋል፡፡

የኢዜማ አመራር አካዴሚ የመሠረተ ልማት ግንባታው ተጠናቆ፣ የካሪኩለም ዝግጅት ተገባዶ ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንደሆነ ያብራሩት ምክትል መሪው አቶ ዮሐንስ (አርክቴክት) የተማሪዎች መቀበያ መሥፈርቱ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡ አካዴሚው ለስድስት ወራት ከሚዘልቅ የአጭር ጊዜ ሥልጠና ጀምሮ እስከ ዲፕሎማ ደረጃ ለማሠልጠን እየተዘጋጀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በእልህና ብስጭት ከመመራት ወጥቶ በሰከነ መንገድ በዕውቀት እንዲመራ ለማድረግ ፓርቲው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ የአካዴሚ ግንባታ ተነሳሽነቱን ወስዷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለመረጃ ቋት ግንባታው ሰፊ ገለጻ ያደረጉት አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ ዲጂታይዜሽንና ዘመናዊ አሠራርን መከተል ለኢዜማ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅን ተከትሎ የፓርቲዎችን እንቅስቃሴና መረጃ የመከታተል ሥልጣን እንዳለው የጠቆሙት አቶ ግርማ፣ ነገር ግን ይህን መሰሉ ክትትል ጥብቅ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር በእውነትና በመረጃ ከመመራት ይልቅ በፖለቲካ ሸቃጮች ተሞልቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ አገራዊ ፓርቲዎች ከአሥር ሺሕ ያላነሰ አባል እንዲኖራቸው ሕጉ መሥፈርት ቢያስቀምጥም ይህን በትክክል የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩንና ምርጫ ቦርዱም በትክክል ኃላፊነቱን የሚወጣበት ዕድል አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

እኛ እንደ ኢዜማ ፖለቲካ፣ በፖለቲካ ሸቃጮች ሳይሆን በፍላጎትና ወደው በሚሳተፉ ሰዎች የተሞላ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ወደ 15 ሚሊዮን አባላት አሉኝ የሚለው ብልፅግናም ሆነ ክልላዊና አገራዊ ነን የሚሉ ሌሎች ፓርቲዎች በተጨባጭ መረጋገጥ የሚችል መረጃ አቅርበው የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ስለሆነም የኢዜማ አባላትን ሁኔታና ሌሎችም ዝርዝር መረጃዎች የሚያቀርብ የመረጃ ድኅረ ገጽ ገንብተን ሥራ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነን በማለት አቶ ግርማ ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡  

በእነዚህና በሌሎችም ፓርቲውን በተመለከቱ ጉዳዮች ጥያቄ ለሚያቀርቡ ጋዜጠኞች ዕድል የሰጡት የኢዜማ አመራሮች፣ የተለያዩ ሐሳቦችን አስተናግደዋል፡፡ ኢዜማ ዋና ሥራውን ፖለቲካን ትቶ ወደ ትምህርት ገባ ወይ እንዲሁም አገሪቱ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ቀውሶች ውስጥ ተዘፍቃ ሳለ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታውን ገምግሞ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚሰጥ ሥራ ላይ ለምን አያተኩርም የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአግባቡ መመዝገብ፣ አባላትን የተመለከቱና ሌሎች የፓርቲ መረጃዎችን ማቅረብ የሚከታተል በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድን የመሰለ ተቋም እያለ፣ ኢዜማ በዚህ ጉዳይ ለምን ይጠበባል የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸው ነበር፡፡ የኢዜማ አባሎችና አመራሮች በየጊዜው እየለቀቁ እየታየ ፓርቲው ለምን ዝም ይላል ተብለውም ነበር፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የመስጠቱን ቅድሚያ የወሰዱት የሕዝብ ግንኙነቱ ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ በቅርቡ ፓርቲው ያካሄደውን ዓመታዊ ኮንፍረንስ አንስተዋል፡፡ በኮንፍረንሱ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ የተመለከቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው፣ ፓርቲው በእነዚህ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊከተላቸው የሚገቡ አቅጣጫዎች ተመላክተዋል፡፡ የፓርቲ መሪዎቻችንን ገለጻና ውይይቱን የተመለከቱ ቪዲዮዎች ከሰሞኑ ስላጋራን ይህን የተመለከተ ምላሽ ከዚያ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ አካዴሚ መገንባትም ሆነ የመረጃ ቋት መሥራት ፓርቲው ፖለቲካን በዕውቀት እንዲመራ ለማድረግ ከሚከተለው አቋም ጋር አብሮ የሚሄድ ሥራ እንጂ ፖለቲካን መተው አይደለም በማለትም ተከራክረዋል፡፡

ሦስቱ የኢዜማ አመራሮች በአባላት ከፓርቲው መልቀቅና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየተቀባበሉ በሰጡት ምላሽ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመዘወር ይሞክራሉ ባሏቸው በዩቲዩበሮች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች ላይ ጭምር ወቀሳቸውን አያይዘው አቅርበዋል፡፡ የኢዜማ ጉዳይ ሲሆን ተጋኖ ይወራል፣ የገዢው ፓርቲ ብልፅግና ጉዳይ እንኳ እንደ ኢዜማ መነጋገሪያ አይሆንም፣ ከመንግሥት ጋር በመሥራት ጉዳይ፣ በአባላት መልቀቅ ጉዳይና በሌሎችም ጉዳዮች ሆን ተብሎ አጀንዳ ለመፍጠር በሚመስል ሁኔታ ፓርቲው ላይ ዘመቻ ይካሄዳል ሲሉ ሚዲያዎችን በስም እየጠሩ ጭምር ተችተዋል፡፡

የኢዜማ አመራሮች ይህን ቢሉም ነገር ግን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተገኙ መገናኛ ብዙኃን መካከል አንዳንዶቹ የፓርቲው ጉድለት ያሏቸውን ጠንካራ አስተያየቶች ወርውረዋል፡፡ ኢዜማ ሚዲያዎችን ይፈራል፣ ፓርቲው የሚፈልገው ጉዳይና ሚዲያ ሲሆን ብቻ ነው መግለጫና መረጃ የሚሰጠው፣ ሚዲያ የምትፈሩት ለምንድነው የሚል ሐሳብ ተነስቶላቸዋል፡፡ መንግሥት በግልጽ ሐሳብ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የሕዝብ ቅሬታዎችን በተመለከተ ምንም ስትሉ አትታዩም፡፡ አገራዊና እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮች ተበራክተው ሳለ እናንተ የምትፈልጉትን አጀንዳ ብቻ መርጣችሁ ነው ሐሳብ ለማስተጋባት የምትሞክሩት የሚል ወቀሳም ቀርቦላቸዋል፡፡ መረጃና ሐሳብ ስትጠየቁ ቢሮክራሲ ታበዛላችሁ የሚል ትችትም ለፓርቲው አመራሮች በዕለቱ ከሚዲያ ሰዎች ቀርቦ ነበር፡፡

ሦስቱ የኢዜማ አመራሮችም ምላሽ ያሉትን ከመስጠት በተጨማሪ ፓርቲው ራሱን ለማሻሻል ውስጣዊ ግምገማ እንደሚያደርግና ችግር ካለ እንደሚያርም ተናግረዋል፡፡