ናርዶስ ዮሴፍ

September 8, 2024

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ ተከልሎ ከቆየበት፣ ወደ አውሮፕላን መለዋወጫዎች አምራችነት እንዲስፋፋ የሚያስችል የዘርፍ የሽግግር ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካዮች፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታዎች፣ ከግል አቪዬሽን ተቋማትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ባካሄደው የግማሽ ቀን የምክክር ወቅት ነው ፕሮግራሙ ይፋ የተደረገው።

ባለሥልጣኑ የፕሮግራሙን አጠቃላይ ይዘትና የሚያካትታቸውን ዘርፎች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም የሚያስችል ጥናት በማድረግ ዝርዝር አካሄዱን የሚወስን ሰነድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰባት ወራት ውስጥ አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ አሳውቋል።

የፕሮግራም አጠቃላይ ይዘት በአሥር ዋና ዋና ጉዳዩች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአየር ትራንስፖርትና የኤርፖርቶች ልማት፣ የአውሮፕላን ክፍሎች ማምረት፣ አጠቃላይ የአቪዬሽን አገልግሎት ሽፋን፣ የአቪዬሽን መመርያዎች መሻሻል፣ ጥገና፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍን ተሳታፊነት ማሳደግን የተመለከቱ ጉዳዩች በሰነድ የተደገፈ ማብራሪያ ከቀረበባቸው ጉዳዮች ተጠቃሾቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይላይት ሆቴል የግማሽ ቀን የምክክር መድረክ ከፍ ያለ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኛው የአውሮፕላን ክፍሎችን ከማምረት ጋር የተያያዘ ነው።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ቀጣዩቹ 15 ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግና ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አመንጪ ዘርፎች መካከል አንዱ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚውሉ አስረድተዋል፡፡

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ በሰጡት ማብራሪያ፣ የአውሮፕላን ክፍሎች በማምረት የመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ገበያ በበላይነት ለመቆጣጠር ዕቅድ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ የአኅጉሪቱ ክፍሎች ምርቱን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች አለመኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ የገበያ ክፍተት ዕድል ከዚህ በኋላ እንዳታጣው በገበያው ውድድሩን መቋቋም እንዳያቅታት ለውጦችን ማድረግ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል። ውድድሩ ያለው ደግሞ በአገሮች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአቪዬሽን ድርጅቶች ደረጃም ከፍተኛ እንደሆነ፣ በዚህ ሒደት በአፍሪካ አኅጉር የመሪነት ሚና መውሰድ አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የአውሮፕላን ክፍሎች አምራችነት ልንጠቀምበት ሲገባን በአግባቡ ያልተጠቀምንበትና የእኛ አያቶች ቅድመ አያቶች በጥሩ ሁኔታ ጀምረው እኛ ማስቀጠል ያልቻልንበት የሚያስቆጭ ነገር ነው፤›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1935 ‹‹ፀሐይ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው አነስተኛ አውሮፕላን ገጣጥሞ እንደነበር፣ በተመሳሳይ በ1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆንና ከአንድ የስዊድን ኩባንያ ጋር በመጣመር ‹እሸት› የተሰኘ አውሮፕላን በአገር ውስጥ ተሠርቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የአውሮፕላን ክፍል ማምረት ጅማሮው ሄዶ ሄዶ በመንግሥት ለውጥ ብቻ የተጨናገፈና አለመቀጠሉን ገልጸው፣ ዕድሎች ነበሩ ብንቀጥልባቸው ኖሮ ዛሬ ሌሎች አገሮች አውሮፕላን ማምረት የደረሱበት ደረጃ በራሳችን ቴክኖሎጂ እንችል ነበረ፤›› ብለዋል።

‹‹የማምረት ዘርፉ አሁን የለም በሚያስብል ደረጃ ነው ያለው፤›› ብለው፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር ከሚመረተው አነስተኛ ዋየር (Wire) እና የአውሮፕላን ብላንኬት (Aircraft Blankets) በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ ስኬታማ መሆን የሚያስችል አቅም መኖሩን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል በአቪዬሽን ድርጅቶችና በዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው አምራቾች ጋር ያለው ግንኙነት መሻሻል እንደሚኖርበት አክለዋል።

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ፣ ከኤርባስና ከሌሎቹ አምራቾች አውሮፕላን ይገዛል። ግን ግንኙነቱ በአንድ መንገድ የሚጓዝ ነው። እነሱ ያመርታሉ እኛ እንገዛለን ያልቃል። ነገር ግን ግንኙነቱ ወደ ሁለቱም መንገድ የሚያቀና መሆን አለበት፡፡ እኛ ስንገዛቸው እነሱም ከእኛ የሚገዙት ነገር መኖር አለበት። ለዚያ የሚሆን ደግሞ አሠራሮች አሉት፡፡ ይህ ትልቅ አቅም ነው፤›› ብለዋል።

በደቡብና በሰሜን አፍሪካ ያሉ አገሮች የገበያ ፍላጎት በሞሮኮ፣ በቱኒዝያና በደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች መሸፈናቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ሞሮኮ ብቻ ከዘርፉ በዓመት በአማካይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ ተናግረዋል። ‹‹ፈጥነን በዘርፉ ካልተሰማራን ዕድሉ እንዳያመልጠን እሠጋለሁ፤›› ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የተገኙ የኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፣ የሲቪል አቪዬሽን የትራንስፖርት ፕሮግራም የዘርፉን የቴክኖሎጂ ዕድገትና የተወዳዳሪዎችን አቅም ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበው የመመርያዎች መሻሻል ሊቀድሙት እንደሚገባ፣ እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል መኖር የፕሮግራሙን ስኬታማነት እንደሚወስነው አብራርተዋል።

በአቪዬሽን ዘርፍ ጉምቱ ባለሙያ የሆኑ አንድ የጉባዔው ተሳታፊ፣ ‹‹ፕሮግራሙን ማስፈጸም የሚያስችል የሰው ኃይል አቅም አለን ወይ ስል እጠይቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል ዘርፉን የምንቆጣጠርበት መመርያም ለኢንቨስተሮች ሳቢ መሆን ይገባዋል፤›› ብለዋል።

እንደ ባለሙያዎች ትንታኔ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአቪዬሽን ደኅንነት ከፍተኛ ደረጃ ስኬት ካስመዘገቡት መካከል እንደሚመደብ ቢገለጽም፣ ዘርፉን የሚቆጣጠረው መመርያ ግን ወቅታዊ የኢንዱስትሪውን ዕድገት ያላማከለ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያላካተተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

መመርያ ሲወጣ ችግር የሚያተኩረው አድርግ፣ አታድርግ ላይ የሚወሰን መሆኑን፣ ደኅንነት የሚያስጠብቁና የሚያረጋግጡ ደረጃዎችን ተግባር ላይ ማዋል የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ስለሆነ አስፈላጊ ስለሆነ፣ ሌሎች ሁኔታዎችም ታሳቢ መደረግ አለባቸው ብለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዴሄንጌ ቦሩ በበኩላቸው፣ ‹‹የግል የአቪዬሽን ዘርፍ ‘የአየር ትራንስፖርት’ ዘርፍ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ የግሉ ዘርፍ ወደ ሌሎች የኢንዱስትሪው ዘርፎችም መሰማራት አለበት፤›› ብለዋል።

‹‹የአውሮፕላን ክፍሎች የማምረት ዘርፉም ሆነ አጠቃላይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ማበረታቻ የለውም፡፡ የተለያዩ መቃለል ያለባቸው የግብር ዓይነቶች ተጥለውበታል፡፡ የሰው ኃይል ልማት ዕድገቱ የተቀዛቀዘና ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው፡፡ የፋይናንስ ተደራሽነቱም ሊረጋገጥለት ይገባል፤›› ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸውም በሥራ ላይ ያሉት መመርያዎች ከመፍቀድና ከመከልከል ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን ማካተት፣ አላስፈላጊ የሆኑ ተደራራቢ ጫናዎችን ማቃለልና ድርጅቶች በማምረት ዘርፉ ውስጥ መግባት የሚችሉበት አቅም የሚገነባ መሆን አለበት ሲሉ አብራርተዋል። አያይዘውም በአኅጉራዊ የደኅንነት ማዕከሎች ኢትዮጵያ መካተት እንደሚገባትም ጠቅሰዋል።

‹‹የአቪዬሽን ደኅንነትን ከራሳችን ጋር ብቻ አያይዘን ማየት ስህተት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት። ይህ ማለት በሚበርባቸው አገሮች በሙሉ ያለው የደኅንነት ደረጃ ይመለከተዋል፡፡ አኅጉራዊ ማዕቀፍ ባለው የደኅንነት ማዕከል ውስጥም መግባት አለብን፤›› ብለዋል።

በአፍሪካ የአቪዬሽን ደኅንነት ማዕከል ያልተካተቱት አገሮች ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኤርትራ ብቻ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

አቶ ዴሄንጌ በበኩላቸው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መመርያ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይነት ለሚመራው የኢንቨስትመንት ቦርድ መቅረቡንና በቅርቡም ይፀድቃል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ለሚመራው የመንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚክ ቡድንም፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን የሚመለከት የመመርያ ሰነድ እንደሚቀርብም ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴር ደኤታው፣ ‹‹ሁለቱ መመርያዎች ፀድቀው በሥራ ላይ ሲውሉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ገበያ ይከፈታል፡፡ የአገር ውስጥም የሆነ የውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች እንደ ፍላጎታቸው መሰማራት የሚያስችላቸውን መንገዶች ሁሉ ይዘረጋል። ከእነዚህ ዋነኛው ተጠቃሚ ደግሞ የአውሮፕላን ክፍሎች ማምረት ዘርፉ ይሆናል፤›› ብለዋል።