ሔለን ተስፋዬ

September 8, 2024

ማሽኖችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣ ስምምነት በተደረገበት ወቅት

የሁሉንም የባንክ ካርዶች በመጠቀም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያስችላሉ የተባሉ 10,000 የክፍያ ነቁጥ (Pos) ማሽኖችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣  ስምምነት ተደረገ፡፡

በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተሳለጠ የክፍያ ሥርዓት ለመዘርጋት የመጀመሪያዎቹን አንድ ሺሕ የክፍያ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን፣ የያጉት ፔይ መሥራች አቶ ካሊድ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

የክፍያ ሥርዓቱ በ18 የባንክ ካርዶች በመጠቀም ለያጉት ፔይ ግብይት የሚያስችል መሆኑን፣ ነጋዴዎችም ከተለያዩ ባንኮች የሚቀርቡላቸውን የፖስ ማሽን አገልግሎት በአንድ ለመስጠት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

የፖስ ማሽኖቹን ለማስገባት ከቀረጥ ውጪ 300 ሚሊዮን ብር በላይ ድርጅታቸው ማውጣቱን የገለጹት አቶ ካሊድ፣ በቀጣይም ፔይመንት ኔትዌይ ለመጀመር ሲስተም እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ያጉት የዲጂታል የክፍያ ኢትስዊች ጋር ያደረገው ስምምነት፣ የየትኛውንም የባንክ ካርድ በመጠቀም ግብይት መፈጸም የሚያችል መሆኑን አቶ ካሊድ አስረድተዋል፡፡

የኢትስዊች ቺፍ ኦፕሬተር ኦፊሰር አቶ ነብዩ መንግሥቱ በበኩላቸው፣ ‹‹በዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚነትን ከማበረታቱ ግንባር ቀደም መሆኑን ያጉት ፔይን ከኢትስዊች ጋር ለማሳሰር የተደረገው ትግበራ ውጤታማ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የያጉት ፔይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ ዓለማየሁ፣ ያጉት ፔይ ከብሔራዊ ባንክ የክፍያ ኦፕሬተር ፈቃድ በማግኘት አንድ ሺሕ የክፍያ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ ነብዩ በዲጂታል ፋይናንስ የሚከናወነውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የፈቃድ ክፍያ ጨምሮ 15,000 ዶላር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በያጉት ፔይና በኢትስዊች መካከል ያለው ጥምረት በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታል የክፈያ ሥርዓት በማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው፣ ተጠቃሚዎችም ዘመናዊ ፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

የግብይት አማራጩ የክፍያ ሒደቱን ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚረዳ፣ አነስተኛ የንግድ ተቋማት የገንዘብ ፍሰታቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያስተዳድሩና ቀልጣፋ የንግድ ልውውጦችን እንዲያደርጉ ይረዳል ሲሉም አክለዋል፡፡