ፅዮን ታደሰ

September 8, 2024

የመንግሥት ግዥ አገልግሎት በ2017 ዓ.ም. ከንብረት ማስወገድ አንድ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ። 

የመንግሥት ግዥ አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትንና የ2017 ዓ.ም. ዕቅዱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር አስተባባሪነት አገር አቀፍ የንብረት ማስወገድ ንቅናቄ ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል። 

ንቅናቄው በሁለት ዙር ተግባራዊ እንደሚደረግና ሁሉንም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች፣ ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በማሳተፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል።

አገልግሎቱ ከግዥ በተጨማሪ የንብረት ማስወገድ ሥራንም በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት አማካይነት በየመሥሪያ ቤቱ ያለ ጥቅም ተከማችተው የሚገኙ የመንግሥት ንብረቶችን በሽያጭ ለማስወገድ መታቀዱን ገልጿል፡፡ 

አገልግሎቱ የንብረት ማስወገድ ሥራውን የሚያከናውነው ተቋማቱ በሚያቀርቡለት ጥያቄ በመነሳት መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የንብረት ማስወገድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሹንቃ አዱኛ በጥያቄው መሠረት ንብረቱ በግልጽ ጨረታ ከተሸጠ በኋላ የተገኘው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በ2017 ዓ.ም. ከንብረት ማስወገድ ለማግኘት የተያዘው የአንድ ቢሊዮን ብር ዕቅድ በመንግሥት ግዥ አገልግሎት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረግ ዘመቻ ለማግኘት የታቀደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየጊዜው የሚከናወነው የንብረት ማስወገድ ሥራ ለመንግሥት የተሻለ ገቢ ለማስገኘት፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል። በመሆኑም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በሽያጭ እንዲወገድ ውሳኔ የተሰጠባቸውን 300 ተሽከርካሪዎችና 215 መደብ ያገለገሉ ልዩ ልዩ ንብረቶችን በግልጽ ጨረታ በሽያጭ በማስወገድ፣ 240 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል ተብሏል። ይህም አገልግሎቱ ብቻውን በሚያከናውነው ሥራ ለማግኘት ያቀደው መሆኑን አቶ ሹንቃ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ለፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚውሉ 823 ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎችን ግዥ ለመፈጸም መታቀዱ በመግለጫው ተመላክቷል። በ2016 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በአዲስ አበባ በሚገኙ 155 የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የንብረት ክምችት መለየት የሚያስችል ንቅናቄ በማካሄድ፣ በሁለት ዙር በሽያጭ ከተወገዱ ተሽከርካሪዎችና ልዩ ልዩ ንብረቶች በአገልግሎቱ ታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለለትን 213.9 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ማስገኘቱ ተገልጿል። ይህም ከ2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ110.9 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።