ዳዊት ታዬ

September 8, 2024

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ከአራት ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዮሐንስ አያሌው፣ ከጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ለቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዮሐንስ (ዶ/ር)ን ከኃላፊነት መልቀቅ አስመልክቶ እንዳስታወቀው፣ በግል ምክንያትና ከጫና ጋር በተያያዘ በኃላፊነታቸው ለመቀጠል ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህንኑ ምክንያታቸውን በመጥቀስ የሥራ መልቀቂያቸውን ለባንኩ ዳይሬከተሮች ቦርድ ያቀረቡ ሲሆን፣ በጥያቄያቸው መሠረት ቦርዱ መልቀቂያቸውን ተቀብሎ ከጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ አሰናብቷቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን ከ42 በመቶ በላይ የተበላሸ የብድር መጠን በማጻፍ እንዲዘጋ ጭምር ሐሳብ ቀርቦበት የነበረውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ዮሐንስ (ዶ/ር) እንዲመሩት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ባንኩን ከገባበት ችግር እንዳወጡት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡  

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የሥራ መልቀቂያቸውን ከተቀበለ በኋላ፣ ስለእሳቸው ባሠፈረው መረጃ፣ ዮሐንስ (ዶ/ር) ባንኩን ከውድቀት ስለመታደጋቸው ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ስንብት ጋር በተያያዘ በባንኩ አመራሮች ውይይት ስለመደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ መድረክ ላይም ተሰናባቹ ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በበባንኩ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ፣ ባንኩን በተፈለገው ደረጃ መለወጣቸውንና ከችግር እንዲወጣ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ተብሏል፡፡

በሥራ ዘመናቸውም የሚያኮራ ሥራ መሥራታቸውን መግለጻቸውን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በተለይ ለወጣቶች ሥልጠና በመስጠት በመላ ኢትዮጵያ የብድር ተደራሽነት እንዲኖር የቅርንጫፍና የዲስትሪክት ቁጥር በማሳደጉ ረገድ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ባንኩ ከኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ መሆኑ፣ የተበላሸ ብድር ውሳኔውን መቀነስ መቻሉና በአጠቃላይ በተሻለ ለውጥ ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ በማውሳት፣ ከዚህም በኋላ ቢሆን ያላቸውን ዕውቅት ለማካፈል ባንኩ በፈለጋቸው ጊዜ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) የሥራ መልቀቅ እንደተገለጸው፣ በግልና ከጤና ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑ ቢጠቀስም፣ የባንኩ ቀጣይ አቅጣጫ ላይ እየሠሩ ስለነበር ውሳኔው ድንገተኛ ስለመሆኑ የሚገልጹ አሉ፡፡ ባንኩን ከውድቀት ታድጓል የተባለውን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ የዕቅድ ዘመን ባበቃ ማግሥትና ቀጣዩ ዕቅድ ላይ እየሠሩ ስለመሆኑ እየተገለጸ ባለበት ሁኔታ፣ ከሥራ መልቀቃቸው ድንገተኛ ውሳኔ ነው የሚለውን አስተያየት አጠንክሮታል፡፡

እንደ ምንጮች መረጃም ዮሐንስ (ዶ/ር) የባንኩን ቀጣይ የሥራ ዕቅዶችና ክንውኖችን በተመለከተ እየሠሩ ከነበረው አንፃር፣ እንዲህ ባለ ሁኔታ ከሥራ መልቀቃቸው በጤና ምክንያት ብቻ ነው ብሎ ለመግለጽ ያዳግታል፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) የባንኩ ፕሬዚዳንት በመሆን በቆዩባቸው ጊዜያት ባንኩን ከኪሳራ በማውጣት፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ሦስተኛው ከፍተኛ አትራፊ ባንክ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡

የዮሐንስ (ዶ/ር) ከሥራ መልቀቅን ተከትሎ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በተጠባባቂነት የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ባንኩን ረዘም ላሉ ዓመታት ያገለገሉትን አቶ ጌታቸው ዋቄን በጊዜያዊነት መድቧል፡፡

አቶ ጌታቸው፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረዥም ዓመታት በማገልገል ከሚጠቀሱ ባለሙያዎች መካከል ዮሐንስ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት በመሆን ጭምር ያገለገሉ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው ተነስተው የኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንት ሪሰርች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመሆን ሲመሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ አባል ሆነውም  ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡