ማኅበራዊ ከዓመት ዓመት እያሻቀበ የመጣው የዓውደ ዓመት ገበያ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: September 8, 2024

በኢትዮጵያውያን ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት ክብረ በዓላት መካከል አዲስ ዓመት (ዕንቁጣጣሽ) አንዱ ነው፡፡ አዲስ ዓመት በኢትዮጵያውያን ልዩ ነው፡፡ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚጠነሰስበት፣ መልካም ምኞት የሚያቆጠቁጥበት፣ አዲስ ትልም የሚተለምበትና ርዕይ የሚሰነቅበት ስለመሆኑም አያጠያይቅም፡፡

ከዓመት ዓመት እያሻቀበ የመጣው የዓውደ ዓመት ገበያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዓውደ ዓመቱ የገበያ ድባብ

አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲተካ፣ ፅልመት ተገፎ ብርሃን ሲፈካ፣ ምድር በልምላሜ ስትዋብ፣ መስክና ሸንተረሩ በአደይ ሲያጌጥ፣ ሰማዩ ሲጠራ፣ አዲስ ዓመት ሲብትና መስከረም ሲጠባ ኢትዮጵያውያን ልዩ ስሜት አላቸው፡፡

አዲስ ዓመት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ የሆነ ሥፍራ አለው፡፡ የፍካት፣ የድምቀት፣ የፍሬ፣ የልምላሜ፣ የድልና የስኬት ምልክት ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ በአዲስ ዓመት ሁሉ አዲስ፣ ሁሉ ፀአዳ ነው፡፡ አሮጌ የተባሉ ሐሳቦች፣ ቁሶችና ሸክሞች የሚራገፉበት፣ አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ማንነት የሚነግሡበት መሆኑም  እርግጥ ነው፡፡

በመሆኑም አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚደረገው ሽር ጉዱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዓውደ ዓመት ነውና ሁሉም እንደ አቅሙና እንደ ልኩ ዕለቱን ለመዘከር ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ጠላ፣ ጠጁ፣ ዳቦው፣ ዶሮው፣ ሰንጋው፣ ሙክቱ፣ ቅርጫው… በዓሉን የሚያደምቁና ከወዳጅ፣ ዘመድ፣ ቤተሰብ ጋር ተሰባስበው የሚቋደሱት ነው፡፡ ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን›› በማለት ተመራርቀው የሚሸኛኙበትም ነው፡፡

ከዓመት ዓመት እያሻቀበ የመጣው የዓውደ ዓመት ገበያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የበዓላት ሰሞን ገበያም እንዲሁ ልዩ ነው፡፡ ይደምቃል፣ ይዋባል፡፡ ግርግሩ፣ ወከባው፣ ክርክሩና ዋጋው ይለያል፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ፣ በአዲስ አበባ ካራ አካባቢ በሚገኘው የቁም እንስሳት (ከብት) መሸጫ ሥፍራ የሚታየውም ይኸው ነው፡፡ በዓልን፣ በዓል ከሚያስመስሉት ድባቦች አንዱ የዕርድ ሥነ ሥርዓት የሚከወንበት መሆኑ ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘመናት በተሻገረና በቆየ ልማድ መሠረት በሬ ገዝቶ በጋራ መቀራመት (ቅርጫ) የተለመደ ነው፡፡ ስለሆነም ነጋዴው ያደለበውን ሰንጋ ይዞ፣ ገዥውም ገንዘቡን እንደቋጠረ ካራ ገበያ ላይ ተገናኝተዋል፡፡ የአዲስ ዓመት በዓል የከብት (የበሬ) ገበያ ምን እንደሚመስል ሪፖርተር ቅኝት አድርጓል፡፡

ከ50 ሺሕ ብር እስከ 400 ሺሕ ብር ለገበያ የቀረቡ ከብቶች የሚገኙበት ካራ ገበያ እንደባለፉት ዓመታት በቁጥር የበዙ ከብቶች ያልገቡበትና በዋጋ ደረጃም ከፍተኛና ውድ የሚባሉ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ተሰማ ቢተው ናቸው፡፡

ከበዓሉ ቀናት ቀድመው ከጓደኛቸው ጋር በመሆን ለቅርጫ የሚሆን በሬ ለመግዛት መምጣታቸውን የሚናገሩት አቶ ተሰማ፣ በዓሉ ከመቃረቡ በፊት ለግዢ መምጣታቸው ‹‹ከኋላ ይልቅ አሁን ይረክሳል›› የሚል እምነት በመያዛቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ገበያውን እንዳሰቡት ያህል ሆኖ አላገኙትም፡፡

እንደ አቶ ተሰማ፣ የበሬ ዋጋ ጨምሯል፡፡ አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የከብት መሸጫ ሥፍራዎች ከብቶች እየገቡ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ፣ ሸጎሌና ካራ ገበያዎች ተዟዙረው ማየታቸውንና የአንድ በሬ ዋጋ እስከ አራት መቶ ሺሕ ብር ሲጠራ መስማታቸውን ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት አንድ ግለሰብ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ገዝቶ ቤተሰቡን ሊያስተዳድርበት የሚችል ገንዘብ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አነስተኛ የቅርጫ ከብት ከ70 እስከ 120 ሺሕ ብር ዋጋ እየተሰጣቸው እንዳሉም ግለሰቡ አክለው ይገልጻሉ፡፡

የከብት ዋጋ መወደድና በመገበያያ ሥፍራዎች በብዛት አለመገኘት በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግር የፈጠረው እጥረት ሊሆን እንደሚችልም አቶ ተሰማ ያላቸውን ግምት አክለው ይናገራሉ፡፡

በካራ የቁም እንስሳ መገበያያ ሥፍራ ያገኘነውና በከብት ንግድ የተሰማራው አቶ አሌ ወርቁ እንደሚገልጸው፣ ከብቶችን አደልቦ መሸጥ ከጀመረ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩንና የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሲያደልባቸው የቆዩ ከብቶችን ከጎጃም ‹‹ይልማና ዴንሳ›› አካባቢ ይዞ መምጣቱ ይናገራል፡፡

ለአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ አሥር ከብቶችን ይዞ መምጣቱንና አንዱን በሬ ከ360 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ ብር ለመሸጥ ማቀዱን የሚናገረው አሌ፣ እያንዳንዱን ከብት በ130 ሺሕ ብር ሒሳብ ከገበሬዎች ላይ ገዝቶ ሲያደልባቸው ቆይቷል፡፡

በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ከብቶቹን ለአካባቢው ገበያ ማቅረብ እንዳልቻለና ገዥም የሌለው በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ በመኪና ጭኖ ለማምጣት መገደዱንም ይናገራል፡፡

የፀጥታ ችግር በከብት ንግድ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል የሚለው ነጋዴው፣ ዕውቅናና ሕጋዊነት የሌላቸው ኬላዎች በየቦታው መበራከታቸውና አላግባብ ቀረጥ እየተቀረጡ መሆኑ በንግዳቸው ላይ ተጨማሪ ፈተና እንደሆነባቸው፣ አዲስ አበባ እስኪደርስ ብቻ ለኬላ 30 ሺሕ ብር አካባቢ መክፈሉንም ይገልጻል፡፡

የአረቄ አተላ፣ ፋጉሎ፣ ፉርሽካ፣ ጭድ፣ የአተርና የባቄላ ንፋሽ ከብቶቹን እየመገበ ዓመት ከመንፈቅ ያደለባቸው መሆኑንና ካራ ገበያ ላይ እያንዳንዳቸውን በ200 ሺሕ ብር ሒሳብ ስድስት በሬዎችን የሸጠ መሆኑን ያክላል፡፡

እንደ አሌ፣ ለገበያ ካቀረባቸው ከብቶች መካከል የቀሩት ትልቅ የሚባሉና እስከ 400 ሺሕ ብር የሚሸጡ ናቸው፡፡ እነኚህንም ሸጦ እንደ ጨረሰ ተጨማሪ ለበዓል ገበያ የሚሆኑ ከብቶችን የሚያመጣ መሆኑንም ይገልጻል፡፡

በሸጎሌ የቁም እንስሳ መገበያያ ሥፍራ በከብት ንግድ ተሰማርተው ያገኘናቸው አቶ ባህሩ አወል እንደሚናገሩት፣ የአዲስ ዓመት በዓል በማስመልከት ከ60 ሺሕ እስከ 140 ሺሕ ብር የሚሸጡ ከብቶችን ለገበያ አቅርበዋል፡፡

የሚሸጧቸው ከብቶች በዋጋ ደረጃ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀሩ የዋጋ ልዩነት (ጭማሪ) ያላቸው መሆኑን የሚገልጹት ነጋዴው ይህ ሊሆን የቻለው እንደ ልብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለገበያ የሚሆኑ ከብቶችን መግዛት ያለመቻል፣ የከብቶች ማስጫኛ የመኪና ዋጋ መጨመርና ከመኖ ዋጋ መናር ጋር ተደማምሮ የፈጠረው ተፅዕኖ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ደንበኞቻቸው የሥጋ ቤት ባለቤቶች መሆናቸውን የሚገልጹት ግለሰቡ፣ ለአዲስ ዓመት በዓል ለቅርጫ የሚሆኑ አነስተኛ በሬዎች በአማካይ ከ80 እስከ 100 ሺሕ ብር ሲሸጡ ማየታቸውንም አክለው ተናግረዋል፡፡

በዘመን መለወጫ በዓልና በሌሎችም ዓውደ ዓመቶች ቅርጫ በአገሬው ሕዝብ ዘንድ ማኅበራዊ እሴት ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ነው፡፡ ፍሬሽ ኮርነር የገበያ ማዕከልም ቅርጫ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቱ እንደተጠበቀ ለደንበኞቹ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ፍሬሽ ኮርነር ከሁሉም የሥጋ ዓይነቶችና ብልቶች ሩብ፣ ግማሽና ሙሉ መደብ ‹‹ቅርጫ›› የሚሸጥ ሲሆን ግማሽ ቅርጫ የሚባለው ስድስት ኪሎ፣ ሙሉው ደግሞ 12 ኪሎ መሆኑን የድርጅቱ ሠራተኛ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ነግረውናል፡፡

አንድ ኪሎ በ777 ብር ሒሳብ እየተሸጠ እንደሚገኝ የሚገልጹት ግለሰቡ በየትኛውም የቅርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙ ሁሉም ዓይነት የሥጋ ክፍሎች ድርጅቱ በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ የሚገኙ ስለመሆናቸውም አክለዋል፡፡

በሥሌቱ መሠረት ሙሉ መደብ 9,324 ብር ሲሆን፣ ብማሽ መደብ ደግሞ 4,662 ብር ይሆናል፡፡

የቅርጫ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቱ ሳይሸራረፍ የቅርጫ ሥጋን ለደምበኞቹ እያቀረበ እንደሚገኝ የሚገልጸው ሌላው ድርጅት ደግሞ አጋፔ ኦንላይን ቅርጫ ነው፡፡

የአጋፔ ኦንላይን ቅርጫ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ናትናኤል እንደሚገልጹት፣ የቅርጫ ባህል በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚያጠናክር፣ ወዳጅነትን የሚያስተሳስርና ሰዎችን በማቀራረብ የበዓል ድባብን ከሚያደምቁ እሴቶች አንዱ ነው፡፡

‹‹አንድ ሰው ሥጋ ቤት ሄዶ የሚገዛው ሥጋ በሥጋ ቆራጩ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደሆነና ቅርጫ ግን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም እኩል የሚከፋፈልበት ነው፤›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ አሁን እየተፈጠረና እየታየ ያለው አዲስ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ሰዎች ቅርጫ ማድረግ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ፣ ሰዎች ከሚኖሩበት የቀደመ ሥፍራ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ፣ ግላዊነት እየገዘፈ መምጣትና ከተለያዩ የሥራ ባህሪያት አንፃር ቅርጫ ማከናወን እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ለምሳሌ በኮንዶሚኒየም (የጋራ መኖሪያ ቤቶች) አካባቢ ያለው የአኗኗር ዘይቤ ሰዎችን እስካልተግባቡና በደንብ እስካልተዋወቁ ድረስ ቅርጫ የማድረግ ዕድላቸው የጠበበ ያደርገዋል፡፡

‹‹ቅርጫ በባህሪው የሰዎችን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ዕርድ ለማከናወን ሌሊት መነሳት ይኖራል፡፡ በሬ መጣል፣ እግር መያዝ ወዘተ ያካትታል፡፡ በመሆኑም ቤት ተቀምጠው ቅርጫዬ ይላክልኝ የሚባል ዓይነት አይደለም፤›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ሰዎች ቅርጫ የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ድርጅታቸው ይህን ክፍተት ለመሙላት አማራጭ ሆኖ የመጣ ነው ይላሉ፡፡

አቶ አሸናፊ እንደሚናገሩት፣ ዘመኑ የሩጫ በመሆኑ ሰዎች ቅርጫ እንዳይገቡ ‹‹ጊዜ›› በተጨማሪ እያገዳቸው ይገኛል፡፡ ስለሆነም ድርጅታቸው ለእነዚህ ዓይነት ግለሰቦች ሁሉም ዓይነት ብልት የተካተተበት ቅርጫ ሥጋ ቤታቸው ድረስ በማቅረብ ላይ ነው፡፡

በተመጣጣኝ ዋጋ ሁሉንም ዓይነት ሥጋ በቅርጫ መልክ ለተጠቃሚ ማድረስ ከጀመሩ አንድ ዓመት ማስቆጠራቸውን የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፣ የሙሉ ዋጋ ቅርጫ ሒሳብ በበሬው ዓይነትና ትልቅነት ላይ የተወሰነ ሆኖ ከ10 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ብር ድረስ ይሆናል፡፡ የቅርጫ ዋጋው እስከ መኖሪያ ቤት የሚዘልቅ የትራንስፖርት አገልግሎትን ያካተተ መሆኑንና ይህንንም አገልግሎት ድርጅታቸው ባሉት ስድስት መኪኖች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ድርጅታችን በጥራት ላይ አይደራደርም›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ጥራቱን የጠበቀ የቅርጫ አገልግሎት በመስጠታቸው አገልግሎታቸው ተቀባይነትን እያገኘና የደንበኞቻቸውም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የበግና ፍየል ንግድ በሚካሄድባቸው ሸጎሌ፣ ሳሪስና በቦሌ ሃያአራት እየተባለ በሚታወቀው አካባቢ ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው አንድ በግ ከአራት ሺሕ እስከ 18 ሺሕ ብር፣ ፍየል ደግሞ ከአምስት ሺሕ እስከ 16 ሺሕ ብር ዋጋ እየተጠራባቸው ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡