September 8, 2024

ናታን ዳዊት

አዲስ ብለን የጀመርነው 2016 ዓ.ም. አሮጌ ሆኖ አዲስ ብለን ለምንጠራው 2017 ዓ.ም. ቦታውን የሚያስረክብበት የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ እንገኛለን፡፡ ዓመቱ መልካም የሚባሉ ተግባራትን የተመለከትንበት የዚያኑ ያህል ደግሞ በርካታ የሚባሉ ተግባራትን ያስተናገድንበት ነው፡፡ በተለይ ለተከታታይ ዓመታት በአገር ደረጃ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሰላም ዕጦትና አለመረጋጋት በ2016 በጀት ዓመትም አብሮን ዘልቋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀለቀሉ እሳቶችን ማጥፋት አልተቻለም፡፡

ሰላምን ለማስፈን የተደረጉ ጥረቶች ውጤት አላመጡም፡፡ አሁንም የሰላም ዕጦትና አለመረጋጋትን ወደ አዲሱ ዓመት እየተሸጋገርን ነው፡፡ በመሆኑም አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲስ ዓመት ስንረከብ ይህ ችግራችን ይቀረፍ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ የሰላም ዕጦቶችን ብዙ ወገኖችን አሳጥቶታል፡፡ ብዙ ንብረት አውድሞብናል፡፡ ኢኮኖሚያችንን ተፈታትኖታል፡፡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት እንቅፋት ሆኗል፡፡ እጃችን ላይ ያሉ መልካም ዕድሎችን እንኳን እንዳንጠቀም ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አቅዶ ለመሥራት እያሳረፈብን ያለው ብትር በጊዜ ሒደት በቀላሉ የማናስተካክለው እንዳይሆን ሁሉ ያሰጋናል፡፡ አዲሱ ዓመት ለሰላም መስፈን የምንጥርበት ይሁንልን፡፡   

ከዚህ ባሻገር ግን በ2016 ከሌሎች ዓመታት በተለየ በርካታ አዎንታዊ የሚባሉ አገራዊ ተግባራት የተከናወኑበት ነው፡፡ በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሥር ነቀል ለውጦች የተደረጉበት ዓመት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለአገራችን እንግዳ የሆኑ አዳዲስ ሕግጋት ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን፣ ታሪካዊ ሊባሉ የሚችሉ የፖሊሲ ለውጦችና ውሳኔዎች የተላለፉበት ዓመት ነው፡፡ 

ከእነዚህ ሕግጋቶች ውስጥ እንደ ሸማችና እንደተገልጋይ በቀዳሚነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል የቤት ኪራይ አስተዳደር አዋጅና የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅዱት ሕጎች መውጣት ነው፡፡ 

ሁለቱም ድንጋጌዎች በቀጥታ ከሸማቾችና ከተገልጋዮች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሕጎች መውጣት በዋናነት ሸማቾች በአማራጭ የሚገበያዩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና የዋጋ ንረትን ለመከላከል ያግዛሉ ተብሎ ጭምር ነው፡፡ 

የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ለውጭ ኩባንያዎች ይፈቀድ ሲባል ዝም ብሎ ገበያውን ለመክፈት በሚል አይደለም፡፡ ገበያውን በመክፈት ሊገኙ የሚችሉ ጠቀሜታዎች ሥሌት ውስጥ ገብተው ነው፡፡ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ በአገሬው ሰው ብቻ ቢሠራና የራስ ወገን ተጠቃሚ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይሁንና አሁን በዘርፉ ላይ ያሉ ተዋንያኖችን ይዞ በየጊዜው እያደገ ያለውን የገበያ ፍላጎት ማሟላት አይቻልም፡፡ በእስካሁኑ የግብይት ሥርዓት ገበያውን ማዘመን ባለመቻሉ የተወሰደው ዕርምጃ እንዲህ ያሉ ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ 

የጅምላና ችርቻሮ ንግድ በአገሬው ሰው ብቻ እየተሠራ መቀጠሉ እያደገ ካለው የገበያ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚያስጉዝ አይደለም፡፡ በጥቅል ሲታይ የዚህ ድንጋጌ ጠቀሜታዎች በርካታ ቢሆኑም ቁጥር አንድ ተጠቃሚ ግን ሸማችና ተገልጋይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በሕግና በሥርዓት የሚሠሩ ኩባንያዎች ከተፈጠሩ የተበለሻሸው የግብይት ሥርዓት ይስተካከላል፡፡ በጤናማ ውድድር መሀል ሸማች በምርጫ እንዲገበያይ የሚፈቅድ ዕድል ስለሚኖረው በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ውስጥ የውጭዎችም ይግቡበት የሚለው ድንጋጌ በሸማች ዓይን ከታየ እጅግ የሚወደስ ነው፡፡ ለዘመናት ሲፈራ የነበረውን ይህንን አይነኬ የተባለ ቢዝነስ ዘርፍ ደፍሮ ለመለወጥ መነሳቱ በራሱ መንግሥትን ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡

ነገር ግን ይህ ብዙ የተባለበት ድንጋጌ ወደ ተግባር እንዲሸሸጋገር ምን እየተደረገ ነው? የሚለው ጥያቄ በፍጥነት መልስ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ አንፃር እስካሁን በተጨባጭ ያየነው ነገር የለም፡፡ ይህም ጠቀሜታውና አስፈላጊነቱ ታምኖ የወጣው ሕግ በተግባር ካልታየ ሕጉ አለን ብቻ የዋህ መሆን የለበትም፡፡ በዓለም ላይ የግብይት ሥርዓትን ማቀላጠፍና የሸማቾችን ፍላጎት እንደየአቅማቸው በማስተናገድ የሚታወቁ ትላልቅ ኩባንያዎች ሕጉን  ተከትለው እንዲገቡ ጠንከር ተብሎ ካልተሠራ ትርጉም የለውም፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ኩባንያዎች በአንዴ መጥተው ቲማቲሙንም በርገሩንም የቤትና የቢሮ ዕቃውንም በቅናሽ ዋጋ ይዘረግፉልናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከሕጉ ባሻገር የሚፈልጓቸው ሌሎች መሥፈርቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተለይ ትልቅ ችግር ይሆንባቸዋል ተብሎ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ ያለመገበያቱና ትርፋቸውን ያለ ችግር ወደ ውጭ ማውጣት ይቻል አይቻል እንደሆነ ማረጋገጥ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ይህ ችግር ግን አሁን ተፈቷል፡፡ ሌሎች ሊያቀርቧቸው ይችላሉ የተባሉ ጥያቄዎቻቸውንም ሊመልሱ የሚችሉ ሕግጋት ወጥተዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ ለመቀላቀል ሊያሠጋቸው የሚችል ነገር ከሌለ ችግሩ ኩባንያዎቹን ለማምጣት ለየት ያለ ጥረት አልተደረገም ማለት ነው፡፡ በእርግጠኝነት ከብዙ የዓለም አገሮች አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ያለበት አገር  እንደመሆኗ ተጠቃሚና የምትመረጥ መሆኗ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ ከዚህ በኋላ ለምንስ ይዘገያሉ? ብለን አጥብቀን መጠየቅና እንዲመጡ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎችን መሥራት አለብን ማለት ነው፡፡

ኩባንያዎቹን ለማስመጣት የሚያስፈልገው ቀሪ ሥራ በእኛው እጅ ያለ ነው፡፡ የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማት እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች የበለጠ ደግሞ በየአገሩ በውጭ ምንዛሪ የምንከፍላቸው ዲፕሎማቶቻችን ኃላፊነት ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በተደጋጋሚ ለንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች አዘውትረው ወደ ተለያዩ አገሮች የሚመላለሱ የንግድ ምክር ቤት አመራሮች እንዲህ ያለው ሥራ ቀዳሚ ሥራቸው ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?

ስለዚህ ኢትዮጵያ ያለውን ዕድል በሚገባ በማስተዋወቅ እነዚህ ኩባንያዎች በሌላው ዓለም ላይ ያላቸውን ልምድና አገልግሎት እንዲያቀርቡ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት በማድረግ የሕጉ መውጣት ይሰጣል የተባለውን ጠቀሜታ ቢያንስ በአዲሱ ዓመት ማየት እንሻለን፡፡ 

በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ የጅምላና የችርቻሮ ቢዝነሶች አዋጭ መሆናቸው የማይጠረጠር በመሆኑ ይህ ሕግ የአገር ውስጥ ነጋዴዎችንም ተጠናከሩ የሚል መልዕክት ያለውጭ ምር ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ዓለም ላይ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ የሚታወቁ ኩባንያዎች ልምድ ይዞ ሞዴል የአገር ውስጥ ግለሰቦችና ኩባንያዎችም ትላልቅ ኩባንያዎች መፍጠር የሚችሉበት ዕድል ያልተዘጋ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ 

የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የሚሹ ጨዋ ነጋዴዎች ያሉ በመሆኑ አቅም ያላቸው የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ልምድና ስም ካላቸው ጋር በሽርክና መሥራት የሚቻልም ከሆነ ሌላ ጥሩ አማራጭ ሆኖ መታየት ይኖርበታል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የግብይት ሥርዓታችንን ለማዘመንና የተሻለ ድባብ ለመፍጠር አድንም ይሁን ሁለት የውጭ ኩባንያዎች እዚህ ከመጠበቅ ወጣ ብሎ በማፈላለግ እንዲገቡ ማድረግ የ2017 ዓ.ም. አንዱ ሥራ ይሁን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!