ተሟገት ሰላምታና ሰላም ለአዲሱ ዘመን

አንባቢ

ቀን: September 8, 2024

በበሪሁን ተሻለ

በሕፃንነት የትምህርት ዕድሜ ውስጥ እያለሁ እንዘምራቸው ከነበሩት መዝሙሮች መካከል

አበባ ይዘን ተሸልመን

ሰላምታ እንስጠው ለአዲስ ዘመን፣

የሚለውን መዝሙር አዝማች ዛሬም ከእነዜማው አስታውሳለሁ፡፡ መዝሙሩ አዲሱን ዘመን፣ አዲሱን ዓመት ሰላምታ ሰጥቶ፣ ሰላም እያሉ፣ ለአዲሱ ዓመት ሰላምታ እያቀረቡ፣ ዕንቁጣጣሽ እያሉ መቀበል ላይ ይበልጥ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ኅብረተሰብም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ‹‹ባህል›› እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር፣ የብልፅግና ይሁንልን›› እያለ አዲሱን ዓመት ይቀበላል፣ ያከብራል፡፡

እንደ ዕንቁጣጣሽ/የዘመን መለወጫ ባሉና በመሳሰሉ በየቦታውና እንደ ባህሉ ባሉ ክብረ በዓላትና በእነሱም አማካይነት በሚከበሩ ቀኖች አማካይነትና እነሱንም መሠረት አድርጎ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለዴሞክራሲና ለልማት መሳልና መፈጠም፣ ሰላምን መመኘት ተገቢ ነው፡፡ ሰላም ግን ከእኛ ምኞትና መፈጠም በላይ፣ አኗኗራችንን፣ ግንኙነታችንን፣ ማደራጀትና ማበጃጀትን የመሰሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎችን ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ማስፈን፣ በሰላም የመኖር መሠረት የመጣል ተግባር በአስተሳሰብ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት፣ በአገር መንበረ መንግሥት አውታራት ላይ የደረሱ ብልሽቶች ማደስን፣ በተለይም የመንግሥት ዓምዶችን ከየትኛውም ዓይነት ወገናዊነት ገለልተኛ አድርጎ ማዋቀርን፣ መንግሥትን ሥልጣን ከሚይዘው ቡድን፣ ኃይል ወይም ፓርቲ ፖለቲካና እምነት የተለየ እንዲሆን ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሰላማችን እነዚህን በቅድመ ሁኔታነትና በዋስትናነት አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮችንና ድሎችን ይፈልጋል፡፡ ይህ አጣዳፊ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ ደግሞ ይህንን ተቀዳሚ ሥራ የሚሻሙና ሊያድሩ የሚችሉ፣ የሚገባቸውም ሥራዎችን ወይም የማያጣድፉ ጉዳዮችን ከማራገብ መቆጠብን ይጠይቃሉ፡፡ ሕግና ሰላምን የማስከበርና ዴሞክራሲን የመገንባት ቀዳሚ የአገር ግዳጅ የሁሉንም ፓርቲዎች፣ ወገኖች በዚህ የጋራ አደራ ላይ መገናኘትን የግድ ያደርጋል፡፡    

አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ 2017 ዓ.ም. መባቻ ላይ ሆነን ለኢትዮጵያ የምንመኘው ሰላም ከዚህ በፊት የምናውቀው ዓይነት፣ አንዳንዶችም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ሆነው፣ ‹‹እሱስ የት ተገኝቶ›› የሚሉት ዓይነት በአፈናና በጥርነፋ ‹‹ተጠብቆ የኖረውን ዓይነት ሰላም አይደለም፡፡ ‹‹ዛሬ የምናጣጥመው›› እና መረን ለቅቆ የምናየው (ፈረንጆች PERMISSIVENESS የሚሉት ዓይነት) ስድነት ያወጀ ‹‹ዴሞክራሲ››ያችን ምንጭ የገነባነው ዴሞክራሲ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲን ገና አልገነባንም፡፡ የቀድሞው አፈናና ጥርነፋ ለቀቅ በማለቱ፣ በመላላቱ የተገኘ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ግንባታ መንደርደሪያ መሆን የሚገባ የነፃነት አየር ግን ጨካኝ በቀልና መበቃቀል ማካሄጃ መብት፣ ታፍነው የቆዩ፣ ተሰቅዘው የኖሩ ጥያቄዎችን የመዘርገፊያ መሣሪያ ወደ መሆን ተለወጠ፡፡ የአገራችንን ሰላም የበጠበጠው የመብት ጥያቄዎች መቅረባቸው ሳይሆን የጥያቄዎች አቀራረብ ቅደም ተከትል አለማወቁና በባለጥያቄዎች/በፖለቲካ ወገኖች መካከል ያለው ግብግብናና ትግል ከሰላማዊና ሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ ሰላም የነሱን ጥያቄዎች ልዩ ልዩ መሆናቸው፣ ወይም ልዩነታችን አይደለም፡፡ ልዩነቶቻችን ልዩ ልዩ ጥያቄዎቻችን ራሳቸው አብሮ ለመሥራት አያስችሉንም፣ እንዲያውም አያኗኑሩንም ማለታችን ነው፡፡ ልዩነትን በሰላማዊ፣ በሕጋዊ መንገድ በውይይት፣ በንግግር፣ የመፍታት ጨዋነትንና ዴሞክራሲያዊነትን ባህርይውና እስትንፋሱ ያደረገ መንደርደሪያ በማጣታችን ነው፡፡

የውስጥ ጉዳይን የእርስ በርስ ዋነኛ ግንኙነታችን በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት አላውቅበት፣ አልገባው፣ አልፈልግም ያለ ፖለቲካ ደግሞ የውጭ፣ የነበረም ሆነ ያልነበረ የጎረቤት አገር ባላጋራነት ይጠራል፣ ከእሱም ጋር ይሸራረባል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የምትሠጋው ገናና ድንገት አዲስ ባላጋራ/ጠላት ይመጣብኛል ብላ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ልማት ድሮም በቅኝ ግዥዎቻቸው ሥር እያሉና በእነሱ አማካይነት፣ ዛሬም ነፃ ከወጡ በኋላ በበላይ ጠባቂዎቻቸው በኩል የህልውናቸው አደጋ አድርገው አቋም የያዙና ፖሊሲ የቀረፁ ጎረቤቶች አሉብን፡፡ የኢትዮጵያን መጠንከር፣ የገዛ ራሷን የተፈጥሮ ሀብት፣ በተለይም የውኃ ሀብት የመጠቀም መብት ብሔራዊ ሥጋት አድርገው ፖሊሲና ሕግ ያወጡ (እስከ 20ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ድረስ የሃይማኖታዊ አስተዳደራችን ቁንጮ አመራር ላይ ተቀምጠው የኖሩ) የከዚህ ቀደሙን የኤርትራን ትግል ኢትዮጵያን ማዳከሚያ አድርገው የተጠቀሙበት አገሮች እንኳንስ እኛ ችግር ደግሠንላቸው ራሳቸውም ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸውን የመዘንጋት ጉዳይ ራስን የማጥፋት ያህል አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው ክህደትና ፖለቲካ ነው፡፡ ይህንን የአገር የህልውና ጉዳይ በምሳሌነትና በምስክርነት እንዲያሳየን ሮበርት ሜኔንዲዝ የተባሉ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ (ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ) አጭር ታሪክ ምስክር አድርጎ መቁጠር ብቻውን ይበቃል፡፡

ሮበርት (ቦብ) ሜኔንዴዝ 100 (አንድ መቶ) አባላት ያሉት የአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ ነበሩ የምንለው በምንነጋገርበት ቅሌት ምክንያት ከነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የመወሰኛ ምክር ቤት አባልነቱን በ‹ፈቃደ›ኝነት ስለለቀቁ ነው፡፡ የሥልጠናቸው ከፍተኛነት በተራ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነታቸው ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ የዚሁ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ‹‹አድራጊ ፈጣሪ›› ተብሎ የሚጠራው የውጭ ጉዳይ/ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበርም ሆነው ከጥር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሠርተዋል፡፡ እኚህ ሰው ከተከሰሱባቸውና ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙባቸው 16 ክሶች መካከል ግብፅ (የግብፅ መንግሥት) ‹‹የእኛ ሰው በአሜሪካ›› ፖለቲካ ውስጥ የሚሏቸው የባዕድ ወኪል (ፎሬይን ኤጀንት) ሆነው ሠርተዋል፣ ከግብፅ መንግሥትም ጉቦ ተቀብለዋል፣ የዚህንም ክፍያ ምላሽ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታና ጥቅም የግብፅን አቋምና ፖሊሲ በማራመድ ከፍለዋል፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) ይህንን የግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ አቋም እንዲይዝ ጥረዋል የሚለው ክስ ይገኝበታል (ትራምፕ ኢትዮጵያ የሞትገነባውን የህዳሴ ግድብ ታወድመዋለች ብለው ያስፈራሩት/የዛቱት ከዚህ በኋላና በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው)፡፡ ሰውየው በተከሰሱበት 16 ክሶች ሁሉ ጥፋተኛ የተባሉበት መዝገብ ለቅጣት ውሳኔ ለጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡ በአሜሪካ የወንጀል ሕግና የቅጣት አወሳሰን ልምድ መሠረት እስከ 222 ዓመት ድረስ ማስቀጣት በሚችል ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት የሰባ ዓመቱ ፖለቲከኛ ምን ያህል እንደሚፈረድባቸው ገና ባናውቅም፣ የዋሉብንን ደባና ለግብፅም የዋሉለትን ውለታ፣ እንዲሁም በተጠቀሰው ምክንያት የግብፅን ደመኛ ጠላትነት ግን ይህ ብቻውን ይነግረናል፡፡

የግብፅ ምኞት፣ ጥረትና ትጋት ግን በዚህ የሚገታ አልሆነም፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሑድ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ግብፅ ለመከላከል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር የተረጋገጠውን ህልውናዋንና የሕዝቧን ጥቅም ማስከበር፣ ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁና በተጠንቀቅ ላይ ነች ብላ በኢትዮጵያ ላይ ማስፈራሪያዋን አስታውቃለች፡፡ ይህ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በፈጠረው ክፍተት ውስጥ ገብቶ ከቀጥተኛ ጎረቤት አገር ጋር ከምታደርገው ሴራ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚመለከት ዛቻ ነው፡፡  

በተመድ ቻርተር መሠረት ‹‹ህልውናዬንና የሕዝቤን ጥቅም አስከብራሁ›› ማለት በቀጥተኛና  በተራ ቋንቋ የኃይል ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለት ነው፡፡ በግብፅ የተጠቀሰው ቻርተር የሚያረጋግጠው በኃይል /በጉልበት የማስፈራራትና የመጠቀም መብት ሥልጣን ደግሞ የሚታወቀው በዋነኛት በክልክልነቱ ነው፡፡ የቻርተሩ አንቀጽ 2 እና የቻርተሩ ምዕራፍ አምስት መንፈስና ይዘት አባል አገሮችን በሙሉ በእርስ በርስም ሆነ በዓለም አቀፋዊ ግንኙነታቸው ውስጥ ማንኛውም አገር በሌላ አገር የግዛት አንድነትም ሆነ ፖለቲካዊ ነፃነት ላይ በኃይል ማስፈራራትንም በኃይል መጠቀምን (Threat or Use of Force) ክልክል ያደርጋል፡፡ እጅግ በጣም ውስንና ተቆጥረው ከተሰጡ (ብዙ የሚቆጠር ነገር የላቸውም) ሁኔታዎች በስተቀር እነሱም አንድ የፀጥታው ምክር ቤት መፍቀድ አለበት፣ ሁለተኛ ደግሞ በቻርተሩ አንቀጽ 51 በተደነገገው መሠረት ተጠይቆ ፈቃድ ገና ማግኘት ያለበት ነው፡፡ በአንድ አባል አገር ላይ የኃይል ጥቃት/ወረራ ቢደርስ የፀጥታው ምክር ቤት አስፈላጊውን ዕርምጃ እስኪወስድ ድረስ እያንዳነዱ አገር ማለትም ወረራ የደረሰበት አገር ባለው በተናጥልም ሆነ በጋራ ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት መሠረት የሚወስደው የኃይል ዕርምጃ ነው፡፡ ግብፅ ብቻዋንም ሆነ ከሌላ አገርም ሆነ አጋር ጋር አብራ፣ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ወጥታ ኢትዮጵያ ላይ የኃይል ዕርምጃ የምትወስድበት/ወይም እንዲህ ያለ ዕርምጃ እወስዳለሁ ብላ የምታስፈራራበት፣ ተመድንና ቻርተሩን ያንት ያለህ ብላ የምትማፀንበትን ሆነ የምትጠቅሰው የትኛው ዓለም አቀፋዊ ሕግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ራሷ የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ከሕጋዊውና ከሰላማዊው መድረክ ወጥተው፣ ይህንን ሁሉ ሰላም የነሳ፣ ውድመት ያስከተለ፣ በሕይወት፣ በደኅንነትና በነፃነት መብት ላይ ግፍ ያስቆጠረ የዚህን የጦርነት ወጪና በጀት የሚሸፍነው ደግሞ የዳያስፖራ መዋጮ ከጠለፋ/ዕገታ ከዘረፋ፣ በማስገደድ መጠቀም ከሚባል ወንጀል ከሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ግብፅም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አቤቱታችሁን፣ ጥያቄችሁን፣ ፍላጎታችሁን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ አስፈጽሙ ሲባሉ የለም ‹‹ግድ ተዋግቼ›› ብለው ሕገወጥና አውዳሚ ትግል ውስጥ የገቡትን በዓለም ማኅበርና በአገር ዕድር/ትድድር ሕግ ስም ኧረ በጉልበታችሁ አምላክ እያልን የማንማጠነው ይህንን ግጭትና ጦርነት ግድና የማይቀር (Inevitable) የሚያደርግ ምን ምክንያት አላችሁ እያልንም ጭምር ነው፡፡ የዛሬው የዓለማችን ሁኔታ የበረሃ/የዱር ገደል የትጥቅ ትግልን የከተማ አመፅን፣ ወታደራዊ ግልበጣን ዓይነት ሥልቶች ለመጨራረስና ለትርምስ አዙሪት የሚደረግ አደገኛ ጨዋታ አድርጎታል፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤማውያን ግጭት/ጦርነት ውስጥ እንደምናየው በደልን፣ ግፍን፣ ጥቅሜና ‹‹መብቴ››፣ እንዲሁም ህልውናዬ ብሎ የያዘ ፖለቲካን እንኳን በኃይል የመቃወም ተፈጥሯዊ መብትን ኢፍትሐዊው ዓለም እንዴት እየስተናገደው እንዳለ ከግብፅና ከአሜሪካ ‹‹የቀረበ›› እማኝና ባለጉዳይ መጥራት ይከብዳል፡፡

ከግብፅ ማስፈራሪያና ሕገወጥ ዛቻ አንፃር ኢትዮጵያ በሀብቷ (ማንንም ሳትጎዳ) የመጠቀም መብትና ይህንንም መብት የመከላከል መብት ይህንንም የመሰለ ሰናይ ዓላማና ግብ አላት፡፡ ሰናይ ወይም መልካም ጦርነት የሚባል ነገር አለ ብለን ባናምንም ተገድደን የምንገባበት፣ አስቀድመንም የምንዘጋጅበትን ጦርነት ግን ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ በአሸናፊነት ትወጣዋለች ብለን እናምናለን፣ አንጠራጠርምም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ግን ልጇቿ ልዩነታቸውን በሰላማዊና በሕጋዊ መድረክ ውስጥ እንዲታገሉ፣ በመረጃና በዕውቀት መነጋገርን፣ መከራከር፣ መመካከርን፣ አለመግባባትን በውይይት መፍታትን እንዲለማመዱ ትጠይቃለች፣ ጥያቄዋም ዕውን እንዲሆን ፖለቲካዋን ታመቻቻለች፡፡

አገራችን የውኃ ሀብቷን ጨምሮ መላ አገራዊ ሀብቷን (ቁሳቁሷን፣ ገንዘቧን፣ ጥበቧን፣ ዕውቀቷን፣ የሰው ኃይሏን) ከቡዘናና ከብክነት እየተከላከለችና እየቀሰቀሰች፣ የውጭ ካፒታልም እየሳበች ልማቷን የማቀጣጠል፣ እንዲህ ያለም የተፋፋመ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት መብቷም ግዴታዋም ነው፡፡ የህዳሴውም ግድብ የዚሁ አንዱ አካል ነው፡፡ ይህንን ግልጽ ‹‹ፍትፍት›› ማሳወቅና ማስረዳትም ካጋጠመን ጠንቀኛ ጉርብትናና ፍትሐዊ ያልሆነ ዓለም አቀፋዊ ‹‹ግንኙነት›› አንፃር ግዴታችንና ግዳጃችን መሆኑ አልቀረልንም፡፡ በዚህ ዘርፍ አገራችን ከዚህ በፊቱ በተለየ፣ በይዘትም በላቀና የከዚህ ቀደሙን በማያስከነዳ ሁኔታ አዲስና በዓይነቱ ልዩ የሆነ የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና ‹‹የግንባታ ዘመቻ መጀመር አለባት፣ የውጭውን ዓለም ያነጣጠረ፡፡   

ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን (በተለይም ስለዓባይ) የጋራ ፍትሐዊ ጥቅሞቻችን፣ በውስጥና በደጅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ተወላጆች ጋር ተያይዘው የሚሠሩበት የጥናት/የመረጃ ማደራጃና ማለቂያ ማዕከል ተቋቁሞ፣ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች (ቢያንስ ዓረብኛንና እንግሊዝኛን በደንብ በሚያፈሱ አንደበቶችና ብዕሮች) እቅጮችን፣ ቅጥፈቶችንና እውነቶችን በረቺ መከራከሪያ እየፈለቀቁ ለመላው ዓለም (ለአፍሪካ፣ ለግብፅና ለመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካ፣ እንዲሁም ለዋናዎቹ ዓለም ገብ መድረኮች) ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳወቅ የማንዘናጋበት ግዴታችን መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በዚህ ረገድ ከብዙ አቅጣጫ ምክረ ሐሳቦች፣ መረጃዎችና የመከራከሪያ ቢጋሮች፣ ወዘተ. መፍሰሳቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የታዩኝን ጥቂት ነጥቦች ልወራውር፡፡

  1. ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትጋራቸውን ውኃዎች በሰላምና በፍትሐዊነት ለመጠቀም የምታደርገው ትግል ለመግባቢያነት በቅቶ በተግባር እንዲዘልቅ፣ እንቅስቃሴዋና ገጽታዋ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቀዳዳ የሌለውና በቀላሉ የማይበገር የጥቃት መከላከያ (ኢንሱሌሽን) ማበጀቱ መሠረታዊ ነው፡፡ ለመጠቃቀስ ያህል በአዋሳኝ ጎረቤቶቿ ዘንድ ከአንዳቸውም ጋር ቢሆን በወዳጅነት ረገድ አለመራቆቷ፣ የመከላከያና የመረጃ ኃይሏን ከማዘመንና ሸርን አነፍንፎ ከማምከን ባሻገር ሸርን በሸር አለመመለሷ፣ የራሷን ልማት ስታይ የሌላውን ጥቅም ላለመጉዳት መጠንቀቋ፣ ከዓባይ ውኃና ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ለፍትሐዊ የጋራ ጥቅም ያላትን ራስ ወዳድ ያልሆነ አቋም፣ ከሌሎች ጎረቤቶቿም ጋር የምትተቃቀፍበት መርህ መሆኑን ማሳወቋና በዚሁ መሠረት የማይዋዥቅ ትስስር መፍጠሯ፣ ከሁሉም በላይ የአገር ውስጥ ጠንካራ ሰላም ማበጀቷና ግስጋሴዋ መቀጠሉ አንድ ላይ ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
  2. የልዕለ ኃያላንና የኃያላን አድሏዊ ጣልቃ ገብነት በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ ቀጣናዎች ሰላምንና ፍትሐዊ ጥቅምን ሲጎዳ፣ ጠንቅ ሲተክልና ሲያባላ ኖሯል፣ በተለይ ከቅኝ ግዛት መስፋፋት አንስቶ፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አካባቢም እንዲሁ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያና የሌሎች የናይል/የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ትግል መምጣትና ዛሬ የደረሰበት ደረጃ መድረስ፣ የተተከለ ጠንቅንና አድሏዊነትን የማስተካከል ነው፡፡ እናም አሮጌ አድሎኛ ‹‹ባለድርሻነትን›› ታሪካዊ መብት አድርጎ በኃይል፣ በልዕለ ኃያላዊ ጫናና በቀጣፊ መከራከሪያ ለማስቀጠል መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ያነሱት የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ በምንም መንገድ ወደ ኋላ ሊመለስና ሊታነቅ የማይችል፣ መቀበልን ግድ የሚል ነው ዛሬ፡፡ ምክንያቱም በፍትሐዊነት ተሳስቦና ተባብሮ በሰላም ለማደግ መታገል፣ የምሥራቅ አፍሪካና የመላ አፍሪካ የዘመኑ ጥያቄ ስለሆነ፡፡ ይህ ሁላችንን አቀፍ ጥያቄ ፈክቶ መውጣቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
  3. የኢትዮጵያን ከድህነት የመውጣት (የመልማት) ጥረት ለማፈን መሞከር፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም መበጥበጥና ጦርነት መክፈት (ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ የመቀነስ አንዳችም ተንኮል ውስጥ ሳትገባ)፣ የግርጌ አገሮችን በዓባይ ውኃ የመጠቀም ዕድል ላይ ክፉኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በየትኞቹም የደባና የኃይል ሥልቶች የኢትዮጵያን ድህነት የማስቀጠል ተግባር፣ በራሱ በረሃማነትንና የዓባይ ውኃ መበከልን በማስፋፋት የውኃውን መመናመን ማስከተሉ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡ በረሃማነትን ያለ አረንጓዴ ልማት መታገል እንደማይቻል እኛ ለጎረቤቶቻችንም ሆነ ለዓለም አስታዋሽ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ የዓባይን ወንዝ መበከል በተመለከተ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችም ሆኑ ዓለም ሊያውቀው የሚገባ እውነት አለ፡፡ ዛሬ የዓባይ ውኃ ከጣና ሐይቅ አንስቶ እንቦጭ በሚባል አደገኛ አረም እየተወረረና በመድረቅ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን አረም ለማጥፋትና ጣናንና ዓባይን ከመድረቅ ለማትረፍ ብቻዋን እየተፍጨረጨረች ነው፡፡ ይህ ትግል ኢትዮጵያ ለራሷ ህልውናና ልማት የምታካሂደው ቢሆንም፣ በተዘዋዋሪ አይደለም በቀጥታ የዓባይ ውኃ ለሱዳንና ለግብፅ ያለው አለኝታነት እንዳይቀንስ የመዋደቅም ትግል ነው፡፡

በአጭሩ ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብፅን የጥቅም ቀንበር ብቻዋን ተሸክማለች፡፡ እናም የኢትዮጵያና የተፋሰሱ አገሮች አረንጓዴ ልማት፣ ለሱዳንና ለግብፅ የዓባይ ጥቅም ዋስትና እንጂ ጉዳት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ሰላምና የልማት ተፍጨርጫሪነት በማገዝ ፈንታ ለማሰናከል መሥራት፣ የዓባይን ውኃ ከምንጩ ለማድረቅ ከሚተጋው ከእንቦጭ አረም ጎን መቆም ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ዓባይ እንዲደርቅ የሱዳንና የግብፅ ግድቦች ላንቃቸው ተራቁቶ ሲሰነጣጠቅ ለማየት ከመሥራት አይለይም፡፡ ይህንን ዓብይ ሀቅ የሱዳንና የግብፅ ሕዝቦችና ዓለም ሊያውቁት ይገባል፡፡

  1. የህዳሴ ግድብ ባመጣው የፊት ለፊት ጥቅም ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ አንዳችም ቅናሽ ሳታስከትል፣ ውኃው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ውልብልቢቶችን እየመታ እንዲያልፍ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች፡፡ አዲሱ ነገር ውኃው በግድብ ውስጥ በረዥም የጊዜ ሒደት ተጠራቅሞ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ማለፉ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረውም፣ ውኃው በመገደቡ የግብፅንም ሆነ የሱዳንን ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ ይጎዳል የሚል ክርክር ፈጽሞ ሐሰት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፊት ያልነበረ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ጥቅም እንዳገኘች ሁሉ፣ እነ ግብፅም በግድቡ ምክንያት በፊት ያልነበረ (አዲስ) ጥቅም ያገኛሉ ሲባል እንደነበረው ከጎርፍ ጥቃት ይጠበቃሉ፡፡ ግድቦቻቸው በደለል ከመሞላትና ከብክለት ይጠበቃሉ (በህዳሴ ግድብ ሲጠራቀም ያየነው ውኃ አፈርማ እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የአፈር መታጠብና የጎርፍ ጭቃ ጣጣን መቆጣጣር ካልቻለች የግርጌ አገሮች ግድቦች በጭቃ እንዳይሞሉ ከማገልገል እጅግም ያለፈ ጥቅም አይኖራትም)፡፡ በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብ ከሞላ ጎደል ፈረሰኛ ውኃና ድርቅ የሚፈጥሩትን ዝባት ስለሚያቻችል ሱዳንና ግብፅ ከዓመት ዓመት የተቀራረበ የውኃ መጠን የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፋል፡፡ ይህንን ስናስተውል ነው በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ስለውኃ አለቃቀቅ “ዋስትና ያለው” ስምምነት ለመፍጠር የሚደረግ ዓይን ያወጣ ጮካነት የሚጋለጠው፡፡
  2. የህዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ተልዕኮ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪነት ከሞላ ጎደል ሙሉ ዓመት (በድርቅ ጊዜም) የሚካሄድ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዝናብ እጥረት በደረሰ ጊዜ ግድብ ከመኖሩ በፊት፣ ዓባይ ከኢትዮጵያ ድንበር ይዞት ከሚያልፈው የበለጠ ውኃ ግድቡ የሚያስገኝ መሆኑም አያከራክርም፡፡ ስለዚህ አንድ ከግድቡ በታች ያለ የዓባይ ውኃ ተጠቃሚ፣ ኢትዮጵያ በድርቅ በተመቻች ጊዜ ዓባይ የሚኖረው የውኃ መጠን ሳይነካ ይምጣልኝ እንጂ፣ ከዚያ ያለፈ ውኃ አይምጣልኝ ቢል ጥቅሜ አልገባኝም የማለት አላዋቂነት ይሆንበታል፡፡ በተቃራኒው ድርቅን ምርኩዝ አድርጎ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን ሳትጠቀም ለእኔ ልትለቅ ቃል ትሰርልኝ ከሆነ ደግሞ፣ አንቺ በድርቅ ተንጨፍረሪ እኔ ግን ልጠቀም ባይነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታች ወቅት፣ ድርቅ ዓባይ ውኃ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሁሉም የዓባይ ተጋሪ አገሮች የሚጋሩት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የህዳሴ ግድብ መኖር በዓባይ ውኃ ተጋሪዎች ላይ ድርቅ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚያለዝብ ትሩፋት እንዳለው አጉልቶ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ፣ ኢትዮጵያ በሚኖራት ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ መሠረት ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ውኃ ከማሳለፍ የዘለለ ግብርና ነክ ልማት ብታካሄድ እንኳ፣ በግብርና ልማት መጠቀምን እንደምትሻ ሁሉ፣ የኑሮና የልማቷ ሞተር የሆነው የኃይል ምንጭ የጎላ ቀውስ በማይደርስበት አኳኋን ውኃ የሚቀንስ ልማቷን የውኃ ስንቅ ከሚሻው የኤሌክትሪክ አመንጭነት ጋር ማቻቻል አይቀርላትም፡፡ እናም የህዳሴ ግድብ ለግርጌ ትሩፋት የማስገኘት ባህርይው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን በምትጠቀምበት ጊዜም ቢሆን፣ ከፋም ለማም ይቀጥላል እንጂ አይመክንም፡፡ ይህም በአግባቡ ሊጤን ይገባል፡፡

የህዳሴ ግድብን በጋራ ሱዳን፣ ግብፅና ኢትዮጵያ በሦስትዮሽ እናስተዳድር የሚል ሐሳብን ኢትዮጵያ የምትቃወመው ድብቅ ዓላማ ስላላት ሳይሆን፣ ሉዓላዊ የውስጥ መብቷን እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ አገር ከማስከበር አኳያ መሆኑን አጠንክሮ ለአፍሪካም ለዓለም ከማሳወቅ ባሻገር፣ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ውኃዎችን ተጋሪ የሆኑ አገሮች ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ስምምነት ፈጥረው በስምምነቱ መሠረት ፍትሐዊ ድርሻቸውን አክብረው መኖራቸውን፣ በጋራ ያስተዳድሩ የሚል ፖሊሲና ድንጋጌ የአፍሪካ ኅብረት ካበጀና ሥራ ላይ ካዋለ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የጋራ ጥቅምን ለማስተዳደር የቅን ፍላጎት ችግር እንደማይኖርባት መግለጥም የሚጠቅም ነጥብ ይመስለኛል፡፡

  1. ከዚህ ቀደም ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ ክፍፍል ሲነሳ ግብፆች ይህንን ለማምለጥና የእኛን የመብት ጥያቄ ሰይጣናዊና ግፈኛ አድርጎ ለማቅረብ የሚጠቀሙበት መከራከሪያ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ውኃዎች እያሏት ዓባይን ልትገደብ የተነሳችው ለአንድ ናይል ሌላ አማራጭ የሌላትን ግብፅ ለማስጠማትና ለማስራብ ነው በሚል አቅጣጫ ማጭበርበር ነበር፡፡ ዛሬም ይኸው ዘዴ ቀጥሏል፡፡ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻን የማስከበር ትግል የግብፅን ህልውና ከማሳጣት ጥቃት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ የማድረግ ብልጣብጥነትን ለማክሸፍ፣ ግብፆች በዓባይ ውኃ አጠቃቀማቸው የሚታየውን አድፋፊነት፣ ከመጠቀም አልፈው ግዙፍ የከርስ ምድር ውኃ ማጠራቀማቸውን፣ ለሌላም የሚሸጡ መሆናቸውን፣ ወዘተ በደንብ በተጠናቀረ መረጃ መግለጽ (አሁን እንደተያዘው) አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ግን የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ያመጣው ግብፅን የመሻማት ስስትና የማጥቃት ፍላጎት ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ከድርቅ ጋር በሚያያዝ የመጠቃት ረዥም ታሪካችንን ከሰሜን እስከ ምሥራቅ ደቡብ ድረስ ለመቀየር የተነሳሳ ትግል መሆኑን፣ ከኩራዝና ወደ ሰማይ አንጋጦ ውኃ ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ሰፊ የድህነት ገጽታችንን ከረዥም የድርቅና የረሃብ ታሪካችን ጋር ሰድሮ ማሳየት ያዋጣል፡፡
  2. እነዚህ የመሳሰሉ ነጥቦች ከምሁራኑና ከሊቃውንቱ ተዋጥተው የአዋጭነታቸው ጥንካሬ ተገምግሞና በመረጃና በትንታኔ ጉልበት አግኝተው በኢትዮጵያ የዓባይ ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ጥያቄ ላይ የሚነዙ አሉታዊ ሥዕሎችን ለማስተካከል መሥራት አንድ ነገር ነው፡፡ በጉዳዩ የበሰሉ፣ ሐሳብን በማስረዳትና በቋንቋ አቅማቸው የተቡ መልዕክተኞችን ልኮ ለአፍሪካ ለዓረቡና ለምዕራቡ ዓለም ማስረዳት ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ አፄ ምኒሊክ በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የአውሮፓ አቋም ኢትዮጵያንም የሚያይ አንጀት እንዲኖረው አውሮፓዊውን አልፍሬድ ኢልግ የተባለ መልዕክተኛ ልከው ሠርቶ ነበር፡፡ ከዚህ መማር ይገባናል፡፡

ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዳቷንና ፍላጎቷ በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት የተለካ መሆኑን ለዓለም ማስረዳት ከቻለች፣ ተሳስቦ ከመኖርና ከማደግ ፍላጎታችን ጎን የሚቆሙ ለዚህም የሚናገሩ የቅርብና የሩቅ መልዕክተኞች/ወዳጆች ከዓረቡም ከምዕራቡም ዓለም ማፍራታችን ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ፍሬያማ ውጤት አልማ መሥራት አለባት፡፡ ስኬቷንም ብዙ “ባዕድ” ደጋፊ በማግኘት ፍሬ መመዘን ይገባታል፡፡ ይህ ፍሬ ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በውስጥና በውጭ ላለነው ዜጎች በሚያጠጡን ዝተት የፕሮፓጋንዳ ዘይቤ የመገኘቱ ነገር ሱሚ ነው፡፡

  1. ይህም ሁሉ ተደርጎ በህዳሴ ግድብ ላይ የተያዘው ድርድር ቢጠናቀቅም፣ ከዓባይ ውኃ ጋር የተያያዙ ጣጣዎች ይዘጋሉ ማለት አደለም፡፡ ዓባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ግንኙነቶች ጠንቃቃ እንክብካቤ መፈለጋቸው የሚቀጥል ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ ይህን ሥራ ለመወጣት የማይዋዥቅ የውስጥ ሰላም በኢትዮጵያ መገንባቱ ወሳኝ ነው፡፡ የውስጥ ሰላምን ይዞ ከተዋሳኝ ጎረቤቶቻችን ጋር ሁሉም የሚሳሳለት የጋራ ልማት ውስጥ መግባት ደግሞ ዋና መተማመኛችን ነው፡፡

በመጨረሻም ሁሌም የሚከነክነኝንና ሲያጋጥመኝ የማነሳውን አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ወረራ ጋር ባደረገችው ነፃነትን ያለ ማስደፈር ተጋድሎ የብዙ ተቆርቋሪ ወገኖች ባለውለታ ነች፡፡ በዚህ ውስጥ አፍሪካውያን፣ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ የካሪቢያንና የአሜሪካ ጥቁሮች እንዲሁም ፈረንጆች ነበሩበት፡፡ ዛሬም እንዲህ ያለ ተቆርቋሪነት እየታየ ነው፡፡ የአዛውንቱ ቄስ ጄሲ ጃክሰን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለአሜሪካ በአምባሳደርነት የሠሩ ወዳጆችና የአሜሪካ ኮንግረስ ውስን አባላት ያሳዩት፣ የአሜሪካን ለሰላም የማይበጅ አድሏዊነት የተቃወመና ለኢትዮጵያ የፍትሕ ድምፅ ጀርባ ያልሰጠ ድጋፍም ሌላ ውለታ ነው፡፡

በዓረቡም ዓለም የኢትዮጵያ ትውልድ ካላቸው ተቆርቋሪዎች ውጪ ለእውነት የቆሙ ባይተዋሮች አይታጡም፡፡ ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ከሃቋ ጎን የቆሙላትን ባለውለታዎች በአግባቡ ማመሥገን ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ምሥጋና በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የምሥጋና መድረክ ከማዘጋጀት ማለፍ አለበት፡፡ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የታሪክ ዘመዶቻችንና የውጭ ጎብኚዎችን የሚያዩት የታሪክ ባለውለታነታችንን ከእነ ምሥጋናችን በአገራዊና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ያሰፈረ ቋሚ መታሰቢያ፣ ይህ ቢዘገይ መታወሻ ዕለተ ቀን መሰየም  ተገቢ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡