እኔ የምለዉ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብር ዋጋ መውረድ (ክፍል ሁለት)   

አንባቢ

ቀን: September 8, 2024

በነጋድራስ ካሳ

መንግሥት የወሰደው የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ተንሳፋፊ (Floating) ማድረጉ  ጠቃሚ ወይስ ጎጂ?

በክፍል አንድ እንደተመለከትነው እስካሁን የሄድንበት መንገድ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ማሟላትና የብርን የምንዛሪ ዋጋ ግሽበት ማስቆም ቀርቶ፣ የውድቀቱን ቁልቁለት በቅጡ ማድረግ አቅቶን ጥቁር ገበያው ሲሄድ፣ የባንኩ ዋጋ ሲከተል ማቆሚያውን መገመት ወደማንችልበት የቀውስ እሽክርክሪት ወስጥ ገብተን እንገኛለን፡፡ ስለሆነም ከዚህ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት አንድ የሆነ መንገድ በማስፈለጉ የምንስማማ ከሆነ፣ ይህ አሁን መንግሥት የወሰደው የፖሊሲ  ዕርምጃ የት ያደርሰናል?

ሀ ለመሆኑ የጥቁር ገበያውን ዋጋ ማንና እንዴት ነው የሚወስነው?

  የአሁኑ የመንግሥት (ብሔራዊ ባንክ) ውሳኔው አስፈላጊነትስ ምን ያህል ነው?

  1. እንደሚታወቀው የባንኩን ምጣኔ የሚወስነው (ሌላ የራሱ ስሌት አለው… እናም የኢኮኖሚው ምጣኔ ብለን ብንወስደው) ራሱ ባንኩ መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህም ማለት ባንኩ እና/ወይም ሌሎች እንደ አይኤምኤፍ ዓይነት የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሊኖረው የሚገባው የምንዛሪ ምጣኔ 76 ብር ነው ሲሉ ከዋነኛው የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመነሳት በሚለኩበት የሞንተሪ ዘዴ ሲሆን፣ የጥቁር ገበያው ደግሞ በዚያ ሳይወሰን ወዲያውኑ የተለየ ዋጋ (በአብዛኛው የበለጠ) መስጠቱ አይቀርም፡፡ ለጊዜው የባንኩን ስሌት እንተወውና የጥቁር ገበያውን የሚወስነውስ ማን ነው? ትናንት 40 ወይም 50 ከነበረና ዛሬ መቶና 120 የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ለምንስ 200 ወይም 300 አልያም 60 እና 70 አልሆነም? መቼም በጥቁር ገበያው ውስጥ ያሉት ሻጮች በስብሰባ ወይም እየተነጋገሩ እየወሰኑት አይደለም፡፡

በቅድሚያ ከባለፈው በክፍል አንድ ዕትም የገለጽናቸው የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የወጪና ገቢ ንግድ አፈጻጸማችን የምንዛሪን መጠንና ጥንካሬ እንዴት እንደሚወስኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ አፈጻጸማችን ዋነኛውና የአገራችን ምንዛሪ ከሌላኛው ጋር ሲነፃፀር የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ሲያሳየን፣ ነገር ግን ደግሞ የየዕለቱን ተለዋዋጭ የገበያ ዋጋ የሚወስነው ማነው? እርግጥ ነው አዎን ዋጋውን የሚወስኑት እነዚሁ ተገባዮቹ ናቸው፡፡ እኮ እንዴት?

ከላይ ከገለጽነው ዋነኛ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የሚመነጩ ሁለት ጉዳዮች አሉ፣ እነሱም በዚያው ሰሞን በገበያው ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦች ዓይነት፣ ብዛትና ዋጋ ማለትም አስመጪ ነጋዴዎቹ ለማስመጣት ያሰቧቸው ሸቀጦች ብዛትና ዋጋ፣ (እዚህ ላይ ሌሎች ዶላርን ለሕገወጥ ጉዳይ የሚፈልጉ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) እንዲሁም ከዚህ በመነሳት የእነዚህ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ የፍላጎት መጠንና በዚሁ ሰሞን በገበያው በሻጮች እጅ ያለው የዶላር አቅርቦት የየዕለቱን የዶላር ዋጋ ይወስኑታል፡፡ ይህም ዶላር እንደማንኛውም ሸቀጥ በግብይቱ የሚሳተፉ ተዋናዮች በየጊዜው በሚያደርጉት የግብይትና መረጃ  ለውውጥ መስተጋብር ይወሰናል ማለት ነው፡፡

ፍልስፍናውና ትንተናው ረዥምና ጥልቅ ቢሆንም፣ በአጭሩ ታላቁ የኢኮኖሚክስ አባት አዳም ስሚዝ ስውሩ እጅ (The invisible hand)  እያለ የሚጠራው ‹ገበያው› ከላይ በተገለጸው መሠረት በገዥዎች ፍላጎትና በሻጮች አቅርቦት መካከል በሚኖረው የማያቋርጥ የግብይት መረጃ ለውውይትና መስተጋብር ይህንን ይሠራል፡፡

ይህም ማለት ለምሳሌ በሆነ ምክንያት በገበያ ውስጥ ዶላር በሻጮች እጅ ባይኖር ወይም ጥቂት ቢሆን ገዥዎች ያቺን ዶላር ለመቀራመት የሚጠየቁትን የሆነ ዋጋ ለመክፈል ይስማማሉ፡፡ በሌላ በኩል ዶላር በሻጮች እጅ ብዙ መጠን ኖሮ፣ ገዥዎች ግን በሆነ ምክንያት ለምሳሌ ቀደም ሲል የገዙት ሸቀጥ ተጣርቶ ባለመሸጡ ወይም ለዚች ሰሞን አትራፊ ነው ያሉት ሸቀጥ የመሸጫ ዋጋ ወይም ፍላጎት ቢቀንስ፣ የዶላር ፍላጎት ይቀንስና የዶላር ዋጋም እንደማንኛውም ሸቀጥ ይወርዳል ማለት ነው፡፡ ማለትም ዶላር በዚያን ሰሞን ሊገዛ በሚችለው ሸቀጥ መጠንና ዓነት እንዲሁም ራሱ ዶላር በዚያን ሰሞን ያለው የአቅርቦትና ፍላጎት መጠን … እናም ይህ የግብይትና የመረጃ ልውውጥ መስተጋብር ነው እንግዲህ  ‹ገበያ› የምንለውና … የአዳም ስሚዝ ስውሩ እጅ!!::

  1. ነገር ግን የእነኚህን ተዋናዮች የመረጃ ልውውጥ የሚወስኑት ሌሎች የመረጃ ግብዓቶችም አሉ፡፡ እነሱም ዛሬ ባይከሰቱም ወደፊት ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ኩነቶች (Speculations) ገዥዎችና ሻጮች በእጃቸው የሚገኘውን ምንዛሪ ወይም ሸቀጥ በሙሉ ወይም በከፊል ማከማቸት ወይም ወደ ገቢው መልቀቅ ሊወስኑና በዚህም ምክንያት ሰሞነኛው የምንዛሪ ወይም የሸቀጥ ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ይህም ሰሞኑን ብሔራዊ ባንኩ ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት በመሬት ላይ ያሉት የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሳይቀዬሩ ሻጮችና ገዥዎች በውሳኔው ምክንያት ሊከሰት ይችላል ብለው ባሰቡት ኩነት ምክንያት እንደተመለከትነው ማለት ነው፡፡
  2. እንግዲህ ይህ አዲሱ የባንኩ ውሳኔ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ለእንደዚህ ዓይነቱ ሊቆጣጠረው ለማይችለው የተገባዮች ባህሪና ግምት ላይ ለተመሠረተና ‹ገበያ› ለተባለው ነገር ትቼዋለሁ ማለቱ ትክክል አይደለም ካልን፣ ለመሆኑ ባንኩ ቀደም ሲል ሲከተለው በነበረው መንገድ የነበረው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና አፈጸጻም ምን ይመስል እንደነበር ለመገንዘብ ለሚከተሉት ተከታታይ ጥያቄዎች መልስ እንስጥ፡፡

 – ባንኩ አለኝ የሚለው የውጭ ምንዛሪ ተመናምኖና አልቆ መንግሥት በወሳኝነት (Critically) ከሚፈልጋቸው እንደ ነዳጅ፣ መድኃኒት፣ የጦር መሣሪያ፣ ወዘተ አልፎ ለሌላ ሸቀጥና ግብዓት ምን ያህል ይተርፍና ይዳረስ ነበር?

– እናስ ከዚያ የተረፈ ቢኖርስ ሕጋዊው የምንዛሪ መጠን ይህን ያህል ነው ይበል እንጂ፣ ለመሆኑ ይህንን በሕጋዊ ምጣኔ የሚመነዘር ዶላር የሚያገኙት ስንቶቹና እነማን ናቸው?

– ሲያገኙስ በእርግጥና በትክክል ባንኩ ባወጣው ምንዛሪ ልክ ብቻ ነው ወይ የሚከፍሉት? ማለትም በተለያዩ የቅብብሎሽ ሰንሰለትና ሙስና ከጥቁር ገበያው ባላነሰ መጠን እየተከፈለ አይደለም ወይ?

– እናስ ለመሆኑ የውጭ ምንዛሪ በባንክ በኩል የሚያገኙ አስመጪዎች ከውጭ የሚያስገቡትን ዕቃና ሸቀጥ በጥቁር ገበያ ከሚያስመጡት አስመጪዎች ባነሰ ይሸጣሉ ወይ? ማለትም ከባንኩ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙ ነጋዴዎች ከውጭ የሚያስመጡትን ሸቀጥ ከጥቁር ገበያው ያገኙ ከነበሩት ባነስ ይሸጡልን ነበር? እንግዲያውስ ሀቁ በክፍል አንድ በዝርዝር እንዳየነው ባንኩ ቀደም ሲል ይከተል በነበረው ፖሊሲ ወደ ካዝናው ይገባ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ውስንና የተመናመን ከነበረና የውጭ ምንዛሪን ከባንክ የሚያገኙት አስመጪዎችም ጥቂቶች ከሆኑና እሱንም የሚገዙት በተለያዩ የጥቅም ሰንሰለቶች ከጥቁር ገበያው ባላነሰ ዋጋ በመሆኑ፣ የሚያስመጡትንም ዕቃ ለገበያ የሚያቀርቡት በጥቁር ገበያ ከሚገዙት አስመጪዎች በማይቀንስ ዋጋ ከሆነ፣ ባንኩ በሆነ በተግባር ተፅዕኖ በማያመጣ ቁጥር ላይ ተንጠልጥሎ ከመታየት ባለፈ ከጥቁር ገበያው እየተከተለ የሚለጥፈው የብር ዋጋ ፋይዳው ምንድነው? ይልቁንም ይህንን የይስሙላ ቁጥር እየሰየመ መቀጠሉ ከላይ እንደተመለከትነው በእጁ የምትገኘዋን መጠን ለመቀራመት በሚደረግ ሽኩቻ ለሙስናና ስርቆት ከመዳረግና እነዚህን ጥቂት አስመጪዎችና የጥቅም ተጋሪ የባንክ ሹመኞችን ከመጥቀም ባለፈ ጥቅሙ ምንም እንዳልሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

  1. ታዲያ ትናንትም ወደ አገር ሲገባ የነበረው ሸቀጥም በጥቁር ገበያው ወደ መቶ ምናምን ከነበረና አሁን አዲሱ ፖሊሲ ከተነገረ በኋላ (ስለወደፊቱ የምናየው ሆኖ) ቢያንስ 76 ብር ነው መባሉ ሊያስደነግጠንና ሊያስጮኸን የቻለበት ምክንያቱ ምንድነው? ነገር ግን ደግሞ ባንኩ 76 ብር ነው ባይል ኖሮ፣ በማናቸውም ሁኔታ ከውጭ እየገባ የምንጠቀመውና ለገበያ የሚቀርብልን የሸቀጥ ዋጋ ቀደም ሲል ጥቁር ገበያው ሲሸጥበት ከነበረው ውጭና በታች አይሆንም፣ አልነበረም፡፡

ስለወደፊቱ አብረን እናያለን፣ እናም እንነጋገራለን፡፡ ነገር ግን አሁን ትናንት 61 ብር ላይ የነበረ የባንክ የብር ምንዛሪ ዋጋ፣ ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው ለይስሙላ እንጂ በሙስናና የውስጥ ለውስጥ አሠራር የዶላር ገዥው መጨረሻ ላይ የሚከፍለው ከዚያ በላይ ሆኖ እያለና ያ ቁጥር ደግሞ ከውሳኔው በፊት በጥቁር ገበያው ከምናውቀው  ከብር 120 እና በላይ የቀረበ እንደሚሆን እየታወቀ፣ አሁን ከውሳኔው በኋላ 76 ብር  ወይም ነገ እየጨመረ እንደሚሄድ ነገር ግን ባንኩ አሁን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር የለብኝም እስካለና ማቅረብ እስከቻለ ድረስ፣ ቢያንስ በሆነ አጭር ጊዜ ከጥቁር ገበያው 120 እንደማያልፍና የሆነ ጊዜ እንደሚወስድበት በእርግጠኝነት መገመት ይቻላል፡፡

  1. እናስ ከላይ ከሞላ ጎደል ከጠቀስነውና እየተሽከረከርን ካለንበት የቀውስ አዙሪት እንዴትና መቼ ነው የምንወጣው? አሁን ከተወሰደው አማራጭ ውጪ ሌላ መንገድና አማራጭስ አለ?

እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ባንኩ በየጊዜው ጥቁሩን እየተከተለ የሚለጥፈው ዋጋ በተግባር (Actually) በባንኩ የሚሸጥበት ዋጋ ከጥቁር ገበያው ያላነሰ ወይም የተቀራረበ ከሆነ፣ እንዲሁም ከባንኩ ዶላር ወስደው ሸቀጥ በሚያስመጡና በጥቁር ገበያው በሚያስመጡ ነጋዴዎች የሸቀጥ ዋጋ መካከል ልዩነት ከሌለ፣ እስካሁን በነበረው መንገድ መቀጠሉ አስፈላጊ አይደለም ወይም አይሆንም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም 76 ብር (ወይም በሚቀጥሉት ጊዜያት ጨምሮ እስከ መቶ ምናምን ብር) እንዲያውም ቢያንስ እስከ ትናንት ከነበረው ያነሰ ምጣኔ እንጂ ከፍተኛ ስላልሆነ ነጋዴውም ሆነ እኛ ሸማቾቹ የተለየ ተዓምር እንደተፈጠረና በዚህ ምክንያት የተከሰተ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር አይችልምና አይገባም ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡

  1. በሌላ በኩል ባንኩ በራሱ መንገድ የሚወስነውን የምንዛሪ ምጣኔ ከተወና የጥቁር ገበያውን የሚወስነው ደግሞ ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እንደተመለከትነው ገበያው ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ ምጣኔውን ለገበያው ከመተው በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም:: ስለሆነም ባንኩ የውጭ ምንዛሪን መገበያያ ምጣኔ በገበያው ለመወሰን ያስተላለፈው ውሳኔ ትክክለኛነቱን ላለመቀበል በግሌ ሌላ አሳማኝ ምክንያት አላገኘሁም፡፡
  2. ይሁን እንጂ ይህ ማለት የጉዳዩ መጨረሻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም መንግሥት (ባንኩ) ትናንት መከተልና መፈጸም የነበረባቸውን ትክክለኛ ፖሊሲዎች በጊዜና በተከታታይ ባለመፈጸሙ አገሪቱና ዜጋው የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ከነበረ፣ ዛሬ ከዚያ ለመውጣት የወሰደው ይህ ዕርምጃ ትክክል ሆኖ ቢገኝ፣ የመጀመሪያውና አንዱ አንጂ ከቶም የመጨረሻውና ብቸኛው (ብቻውን) አይደለም፡፡

ቀጣዩ ጥያቄም ይህ ውሳኔ አሁን ከምንገኝበት ውጥንቅጥ ለመውጣት ትክክለኛውና የተሻለው አማራጭ (ለነገሩ ሌሎች ውሳኔውን የሚቃወሙ ሌላ የተሻለ አማራጭ ሲያቀርቡ አልሰማንም) ነው ካልን፣

– ቢያንስ እስካሁን ከነበርንበትና ወደፊት ከሚጠብቀን እንዴትና በምን መልኩ ነው  የሚሻለው?

– ሥጋቶች ካሉትስ ምን ዓይነት ሥጋቶች መቼና እንዴት ነው የሚከሰቱት? እንዴትስ እንለፋቸው?

ለ የውሳኔው ትሩፋቶች/ሥጋቶች ምንድናቸው?

  1. ባንኩ የሆነ የምንዛሬ ምጣኔ ሲያወጣ የጥቁር ገበያው ከባንኩ ማስተካከያ በበለጠ መጠን እየጨመረና ትናንት የጥቁር ገበያ የነበረው የብር ዋጋ ዛሬ የባንኩ ሕጋዊ የምንዛሬ ዋጋ ሆኖ እየቀጠለ፣ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ልዩነታቸው እየሰፋ መቆሚያው የትና ስንት ላይ እንደሆነ መገመት ወደማንችልበት አዘቅት የያዝነውን ጉዞ ለማስቆም የሆነ ዕርምጃ መውሰድና መወሰን እንዳለብን አምነናል፡፡

እንግዲያውስ ከላይ እንደተመለከትነው አንድም ኢኮኖሚው በተሻለ ደረጃ ተንቀሳቅሶና ወደ ውጪ የምንልከው ምርት ከምናስገባው ጋር የተመጣጠነ ሆኖ ሲገኝ፣ ወይም ወደ አገር ውስጥ የሚገባን ሸቀጥ ማስወገድ ወይም የባንኩን የዶላር መጠን በሆነ መንገድ እንዲጨምር በማድረግ ነው፡፡ አሁን ሁለቱንም ማድረግ ባለመቻላችን አስመጪዎች ዶላሩን ከጥቁር ገበያው በውድ ይገዛሉ፣ በሚገዙት ዕቃ ላይም ለዕቃው ትክክለኛ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለዶላሩ ያወጡትን ያህል በዕቃው ዋጋ ላይ በመጨመር  ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ያንን ዕቃም በዚያ ዋጋ መክፈል የሚችሉ እየከፈሉና፣ መክፈል ያልቻሉ እየተነፈጉ የኑሮ ልዩነቱ እየሰፋ ሕይወት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የዶላር ፍላጎት ባይኖሩና አቅርቦቱ ቢበዛ የዶላር ዋጋ ይቀንሳል፣ ነገር ግን የዶላር ፍላጎትን ማጥፋት ስለማይቻል የዶላርን ዋጋ ዝቅ ለማድረግ የመጀመሪያው ጉዳይ አቅርቦቱን ማብዛት ነው፡፡

  1. ሁላችንም በቀላሉ እንደምንረዳው የኢኮኖሚውን አፈጻጸም በማሻሻልና ወደ ውጭ የምንልከውን መጠንና ጥራት አሳድገን ምንዛሪ ለማግኘት የምንችለው በሆነ ረዥም ጊዜ ውስጥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያና አጣዳፊ ዕርምጃ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ነገር ግን በቋሚነት የውጭ ምንዘሪ ሊያገኙልን የሚችሉ ሌሎች ምንጮችን እንደሚከፍትልን ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ከአገራችን የውጭ ምንዛሪ ምንጮች አንዱና (በሆነ ጊዜም ከፍተኛው) በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ የሚተላለፈው ሐዋላ (Remittance) ሲሆን፣ ይህ የምንዛሪ መጠን አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሕጋዊው የባንክ መስመር ወጥቶ ወደ ጥቁር ገበያ ገብቶ ይገኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው በሕጋዊው ምጣኔና በገበያው መካከል ያለው ከፍተኛ ልዩነት እንደመሆኑ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ዕለት በኋላ ግን ባንኩ በገበያው ዋጋ ስለሚከፍል ዜጎች ገንዘባቸውን በባንክና በባንክ ብቻ እንዲያስተላልፉ በማድረግ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ክስተት ዜጎች ስለጉዳዩ በቂ መረጃ ኖሯቸው እስኪረዱት የራሱ የሆነ ጊዜ ይወሳዳል፣ ምናልባትም በአጠረ ጊዜ፡፡

ስለሆነም የጥቁር ገበያው ዋነኛ ተዋናይ የሆነውና ቡናና ጫትን አስንቆ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የነበረው የዳያስፖራው ሬሚታንስ ለጊዜው ግራ ገብቶት ወዲያውኑ ምላሽ (Reaction) ባያሳይም፣ በቅርቡና በአጭር ጊዜ ወደ ባንክ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህ ይሆን ዘንድም ባንኩ ዶላር አስተላላፊዎች ጊዜና ጉልበታቸውን ሊቆጥብላቸው የሚችል መተግበሪያ (Application) ማዘጋጀትና የመሳሰሉትን የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ከወዲሁ ዝግጅት አድርጎ እንደሚሆን እንገምታለን፡፡

  1. ላኪዎች ድሮ ወደ ውጭ የምትልኩትን ሽያጭ ገቢ መጠቀም የምትችሉት 40 በመቶ ብቻ ነው በመባላቸውና እሱንም የምትመነዝሩት በባንኩ ምጣኔ ነው በመባላቸው ሽያጫቸውን በዝቅተኛ ዋጋ (Underinvoice) በማከናወን የገቢያቸውን የተወሰነ (Most Significant) መጠን በውጭ እንደሚያስቀምጡ የነበረው ጥርጣሬና ሥጋት አሁን ይህንን የሚፈጽሙበት ምክንያት ስለሌለ ሙሉ በሙሉ ወደ ሕጋዊው የባንኩ መስመር እንደሚመጡ ይጠበቃል። በዚህም መሠረት የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ቀደም ሲል ከነበረው ከፍ እንደሚል ግልጽ ነው፡፡
  2. መንግሥት ቀደም ሲል ይህንን ተንሳፋፊ ፖሊሲ እንዲከተል እየተመከረ ባለመቀበሉ ከዓለም አቀፉ አበዳሪና ለጋሽ አካላት ይጠበቅ የነበረውን የዕርዳታና ብድር እንዲለቀቅለት መደረጉ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን የሚያሳድግ ምንጭ ከመሆኑም በላይ፣ አገሪቱ አሁን ካለችበት የቀውስ አዙሪት ትወጣ ዘንድ ትክክለኛውን ጊዜ በማምጣቱ ከፍተኛ አስተዋኦ ያደርጋል፡፡
  3. ስለሆነም አሁን ማንም የውጭ ምንዛሪ የሚፈልገውን መጠን መጠየቅና መውሰድ ይችል ዘንድ ይጋበዛል፡፡ በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል የነበረው የውስጥ ለውስጥ ግብይትና የሙስና አሠራርን በማስቀረት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
  4. የፍራንኮ ቫሉታ ማለትም ዜጎች የውጭ ምንዛሪያቸውን በቀጥታ ወደ አገር ውስጥ ባንክ ሳያስገቡ የትም አገር ከሚገኝ አካውንታቸው ወይም ምንጭ በመጠቀም ዕቃ ማስገባት እንዲችሉ በመፈቀዱ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፍራንኮ ቫሉታ ጋር በተያያዘ አንድ ግልጽ ችግር አለ፡፡ ይኸውም የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ባዘቀዘቀና ባጠረ ጊዜ በባንኩ ያልተስተናገዱ ጥያቄዎች ፊታቸውን ወደ ሌላ ምንጭ በማዞር ፍራንኮ ቫሉታ ሌላ የጥቁር መገበያያ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ አንዱ መፍትሔ በፍራንኮ ቫሉታ የሚመጡ ዕቃዎችን በዝርዝር ወስኖ ማስቀመጥ ሊሆን ይችላል፡፡
  5. ቀደም ሲል ምርትና ሸቀጣቸውን በድንበር እያሻገሩ በኮንትሮባንድ ይሸጡ የነበሩ ሁሉ አሁን ያንን ማድረግ ሳያስፈልጋቸው ኮንትሮባንዱ የሚሰጣቸውን ገንዘብ እዚሁ በቀላሉ፣ በሕግና በአስተማማኝ ደረጃ ሊያገኙ ከመቻላቸውም በላይ፣ ከሕገወጥነት ጋር የተያያዙ ድብብቆሽና ሥጋት በሌለው መንገድ መሥራትን ይመርጣሉ፣ ይህም ሌላ የውጭ ምንዛሪ ምንጭና ምክንያት ይሆናል፡፡
  6. በዚህም ምክንያት በውጭ ምንዛሪው ብቻ ሳይሆን፣ ያንን በመሸሽ ከሕጋዊው መስመር ወጥተው የነበሩ የንግድ ሥራዎች ሁሉ ወደ መስመር በመግባታቸው ቀደም ሲል ከእነዚህ ስውር ንግዶች ይታጣ የነበረው የታክስና ቀረጥ ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ ይሆናል።
  7. መንግሥት ያላግባብ እየተፈራገጠ የማይችለውንና ሁሉንም እቆጣጠራለሁ በሚል በሚያወጣቸው መሠረታዊ የሰውን ልጅ ሠርቶ የመኖርና የላቡን ዋጋ በነፃነት የመጠቀም መብት እየተጋፋ ሲንደፋደፍባቸውና ከዜጎቹና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም ከወዳጅ አገር ለጋሾችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር እያተላተመ ያጣ የነበረውን አግባብ ያልሆነ የፖለቲካ አተካሮና ተቃርኖ (በተወሰነ መልኩም ቢሆን) ማስታገስና አንፃራዊ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ማግኘት ያስችለዋል።
  8. በተመሳሳይ ግብይታቸው በቀጥታ በብሔራዊ ባንኩ በኩል እንደሚሆን የሚጠበቁት ወርቅና የመሳሰሉ ማዕድናት፣ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ወደ ሕጋዊው መስመር እንደሚገቡ መጠበቅ ስለሚቻል ሌላ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

አሁን ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ይቀሩናል

አንደኛው ይህ ውሳኔ ውጤቱ እንዲህ ዓይነት ከሆነ ለምንድነው ብዙዎቻችን በተቃራኒው ሥጋት ላይ የወደቅነውና በተለይም በዚህ ሽግግር ወቅት የማይቀሩ ሥጋቶች ካሉ፣ እንዴትና እንዴት ተረጋግተን ማለፍ እንችላለን የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛውና መሠረታዊው ደግሞ ይህ ውሳኔ ከአስቸኳይ ጊዜ መደህንነት አውጥቶን በተደላደለና በተረጋጋ መሠረት ላይ መቆም እንችል ዘንድ ሌሎች የማይቀሩና ተጓዳኘ (Complementary) ፖሊሲዎችና ዕርምጃዎች ምንድናቸው? የሚሉትን በመጨረሻው ክፍል ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው negadraskassa48@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡