እኔ የምለዉ የአዲሱ ዓመት የሰላም መልዕክቴ ለፖለቲካ መሪዎቻችን

አንባቢ

ቀን: September 8, 2024

በንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር)

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እመኛለሁ፡፡ በሰላም ዕጦትና ባስከተላቸው መዘዞች ሳቢያ ይህንን በዓል እንደምትፈልጉትና ቀድሞ እንደለመዳችሁት ማክበር ላልቻላችሁ ወገኖቼ የሚሰማኝን ልባዊ ሐዘን እየገለጥኩ፣ መጪው ጊዜ ግን ብሩህና ሰላማዊ እንዲሆን እንደምፀልይና የበኩሌንም እንደምሠራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

ይህንን በአል አስታክኬ ሰላም ብለን ስለምንጠራው ጽንሰ ሐሳብ በአንድ መንገድ ለመግለጽ ወደድሁ። በዓል ሲመጣ በግ፣ ፍየል ወይም ከብት በቤትም በቡድንም አርዶ መብላት የተለመደ ነው። አንዱ አራጆች ለሌላ ጠንቃቃ ሰው አሳልፈው የሚሰጡት ሥራ የከብቱን ሆድ ዕቃ በተለምዶ ሽንፍላውን ማጠብ ነው። ይህ የከብቱ አካል የማያቋርጥ የምግብ መፍጨት፣ መዋሀድና በተለያዩ ኬሚካሎች የሚደረግ ጠቃሚ ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች በተለየ መልኩ መጥፎ ጠረን አለው። በተደጋጋሚ ታጥቦ አይጠራም፡፡ በጥንቃቄና በትዕግሥት ከፀዳ በኋላ ግን ጠረዼዛ ላይ ሲቀርብ ጣዕሙና ስናኝከው አፋችን ውስጥ የሚፈጥረው ስሜት የተለየ ነው። እኔ ትሪፓ የሚባለውን ምግብ ከዚህ የተነሳ እወደዋለሁ:: አዘገጃጀቱ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄና ትዕግሥት ይፈልጋል።

ታዲያ የሰላም ሥራ ሽንፍላ እንደማጠብና ትሪፓ እንደማዘጋጀት ይመስለኛል። በፅዳቱ ወቅት ጨረስኩ ስንል እንደገና የምንጀምርበት፣ አለቀ ስንል ደጋግመን የምናጥብበት፣ ደግሞ ወደ እሳት ከመጨመራችን በፊት ወደ አፍንጫችን እያስጠጋን ደጋግመን እያሸተትን ንፅህናውን የምናጣራበት ሥራ ነው። የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ነፍስ ኄር ኮፊ አናን እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹ሰላም የማያቋርጥና የማያልቅ ሒደት ነው›፡፡ ማህተመ ጋንዲ ደግሞ ‹የሰላም መንገድ የሚባል ነገር የለም፣ እንዲያውም ሰላም ራሱ የማያልቅ መንገድ ነው› ይሉናል። ሌላው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ነፍስ ኄር ሊቀዻዻስ ዴዝሞንድ ቱቱ ደግሞ፣ ‹እውነተኛ እርቅ ከንቱነታችንን፣ ክፋታችንን፣ ያስከተልናቸውን ጉዳቶችና እውነትን ስለሚገልጥ ለጊዜው ነገሮችን የበለጠ ሊያባብስብን ይችላል። ይሁንና ምንም ሥጋት ያጠላበት ሒደት ቢሆንም እንኳን በመጨረሻ ግን ጥቅሙ የጎላ ነው› ሲሉ ይመክሩናል።

ለምሳሌ ዝነኛው የሰሜን አየርላንድ የዕለተ ስቅለት ስምምነት (Good Friday Agreement) እ.ኤ.አ. በ1998 ከመፈረሙ በፊት 13 ዓመታት ገደማ የፈጀ እልህ አስጨራሽ ውይይት ተደርጓል። እ.ኤ.አ. በ1985 ለውይይቱ መሠረት ከተጣለ ቀን ጀምሮ በመካከል ሲቋረጥና ሲቀጥል ቆይቷል። በተለይም እ.ኤ.አ. ከ1997 ጀምሮ በተደረገው የመጨረሻውን ዙር የተፋፋመ ውይይት በአደራዳሪነት ተሳትፈው የነበሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ልዑክ ጆርጅ ሚሼል ስለ ስምምነቱ ሲናገሩ ‘ከሰባት መቶ ክፉ ቀናት በኋላ አንድ ታሪክን የቀየረች መልካም ዕለት ላይ ደረስን› ይላሉ። በውነቱ ግን ድርድሩ ተጀምሮ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የነበሩት ‹ክፉዎቹ› ቀናት ወደ 5,000 የሚጠጉ ነበሩ።

ዛሬም ለእኛ ያቺን የምንናፍቃት መልካም የሰላማችን ዕለት ላይ ለመድረስ እነዚህን ‹አስቸጋ›’ ቀናት በውይይት ማለፍ ግድ ነው። በሰሜን አየርላንድ ጉዳይ ለ30 ዓመታት የቀጠለው እርስ በርስ ፍጅት ሲካሄድ በተፋፋመው ግጭት መካከል የሰላምን ዘር ለመዝራት የአንግሎ-አይሪሽ ስምምነት ተብሎ የሚጠራው በሁለቱ አገሮች መሪዎች ማርጋሬት ታቸርና ጋሬዝ ፊትዝጌራልድ የተፈረመው ሰነድ ወሳኝ ሚና ነበረው። ከዚያም በመቀጠል የተለያዩ ሌሎች ስምምነቶችና ፖሊሲዎች እየተቀረፁ ቆይተዋል። ለአብነት እ.ኤ.አ. የ1993 የዳውኒንግ ስትሪት መግለጫ፣ እ.ኤ.አ. የ1996 የጆርጅ ሚሼል መርሆች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ይህ በአገሮቹ መሪዎች ዘንድ የተደረሰው መግባባት ለተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች መተማመንን በመፍጠር ተኩስ አቁም እንዲደረግና መላ ማፈላለግ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መልካም ዘርና ትልቅ ማበረታቻ ነበር።

የመሪዎች ቁርጠኝነትና ቅን ፍላጎት ወደ ሌሎች በቀላሉ ይጋባል። ለምሳሌ ሰላምና ደኅንነትን ለአገራችን ሁሉ በምንፈልግበት ሁኔታ ውስጥ አንዳንድ የተጣሉ መሠረቶች አሉ። በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ለማስቆምና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በፕሪቶሪያ የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነትና ያንን ተከትሎ የተቀረፀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እጅግ መልካም ጅማሮ ነው። በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሚያ ነፃ አውጭ ሠራዊት ጋር የተጀመረው ድርድርም ይበል የሚያሰኝ ነው። በአገራችን ያሉትን ሥር ሰደድ ችግሮች ከመሠረታቸው ለመቅረፍ ታስቦ የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በጣም መልካም ውጥን ነው። ሌሎችም እኔ የማላውቃቸው መልካም የሰላም ውጥኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ።

እነዚህ ጅማሮዎች የሰላም አየር እንተነፍስ ዘንድ በዜጎች ልብ ውስጥ የጫሩት ተስፋ ትልቅ ነው። በእነዚህና በሌሎች መሰል ፖሊሲዎችና ተቋማት ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰነዘሩ የአካሄድና የአሠራር ሥጋቶችና ትችቶችን አልዘነጋሁም። መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም በሚገባ አምናለሁ። ይሁንና ‹አንድ አይና በአፈር አይጫወትም› እንዲሉ ለዚህ ሥጋት መፍትሔው ፖሊሲዎቹንና ተቋማቱን ማፍረስና ማሰይጠን ሳይሆን በሰሜን አየርላንድ እንደተደረገው አሠራሩን እየተቹ በየጊዜው እያሻሻሉና እያረሙ መሄድ ነው። እንዲህ መላ በራቀው ፖለቲካችን ባለፈው ጊዜ እንደተደረገው ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አቋቁሞ ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ሳያሳካ ማፍረስ በእኔ አመለካከት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበት የራሱ አሳማኝ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችሉም ተቋማት ሲቋቋሙም ሆነ ሲፈርሱ ቢያንስ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምሥረታ ላይ የተደረገው ዓይነት የባለድርሻ አካላት ውይይት ቢደረግ መልካም ነበር ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ዓይነት ጠቃሚ ምክክር እጣቢውን ውኃ ከእነ ልጁ እንዳንደፋው ይከላከልልናል ብዬ አምናለሁ።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በሰሜን አየርላንድ ጉዳይ የተቋቋሙ ተቋማትና የወጡ ተከታታይ ፖሊሲዎች የተለያዩ ትችቶችና ተቃውሞዎችን እያስተናገዱ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሄድ አስፈልጓቸው ነበር። ይህም በተደራዳሪዎች መካከል በየመሀሉ የሚፈጠሩ ማፈንገጦችና ሽሽቶችን ለማስቀረትና መተማመንን እያጎለበቱ ለመሄድ መልካም ዕድል ፈጥሯል። በዚህ የሰላም ሒደት ወቅት በእንግሊዝና በአየርላንድ መንግሥታት ዘንድ ቢያንስ ሦስት ተከታታይ መንግሥታት ሲፈራረቁ የተገነቡት ተቋማት፣ ተቋማዊ ትውስታን በማስቀጠል የጎደለውን እየሞሉ በመሄድ መልካም ሚና እንዲጫወቱ ረድቷቸዋል። ተቋማት ከፖለቲካ ተዋናዮችና ከመንግሥታት ከሚመሯቸውም መሪዎች በላይ ናቸው። ፓርቲዎች፣ መንግሥታት፣ መሪዎች ሲያልፉና ሲተኩ ተቋማት ግን የተጀመረውን ነገር በቋሚነት ለማስቀጠል ያስችላሉ። ካሁን ቀደም የነበሩ መንግሥታትና መሪዎች እንዲህ ዓይነት የሰላም ግንባታ ተቋማትን መሥርተው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ነገሮችን እጅግ ባቀለሉልን ነበር። ከዚህ አንፃር የአሁኑ መንግሥት ምሥጋና ሊቸረው ይገባል። እነዚህ ተቋማት ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያልፍና ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የሚያመሠግኑበት ጉዳይ ይሆናሉ። የሚያስገርመው ነገር ሰው መታመሙ አይቀርም ብለን ስንት የጤና ተቋማትን ለዘመናት ስንገነባ ቆይተን አገር በማያቆም ሕመም በየጊዜው እየታመሰ፣ ወንድማማቾች እየተጣላን እየተገዳደልንም ከርመን ሳለ ቀደም ብለው ተቋቁመው የወረስናቸው ሰላም ገንቢ ተቋማት አለመኖራቸው እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ጉዳይ ነው።

የመሪዎች ቅን ውጥን እንዴት በቀላሉ ሕዝብን ማንቀሳቀስ እንደሚችል ለማሳየት አንድ ጉልህ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በመገናኛ ብዙኃን እንዳደመጥነው 40 ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እንዲተከሉ አስችሏል። እነዚህ ችግኞች ወደ ዛፎች፣ ዛፎቹ ደግሞ ወደ ደን ሲቀየሩ አገራችንን ለዘመናት ሲፈትኑ የቆዩትን የድርቅ፣ የረሃብ፣ የአካባቢ መጎሳቆልና የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂነትን የመሳሰሉ ችግሮች በእጅጉ እንደሚቀርፉ ይታመናል። ይህም ለመጪው ትውልድ እውነትም ትልቅ አሻራ የምንጥልበት ውለታን የምንውልበት አስተዋጽኦ ነው። የተከልናቸውን ችግኞች ተንከባክበን፣ አብዛኞቹ እንዲፀድቁ አድርገን የአገራችንን የደን ሽፋን በሚገባ መለወጥ ስንችል የተንከባከብናት መሬት ራሷ ልትንከባከበን ትጀምራለች። ይህም የሚመጣው ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት እነዚህ ዛፎች የደን ሥርዓተ ምኅዳር (ኤኮ ሲስተም) መፍጠር ሲችሉ ነው። የደን ሥርዓተ ምኅዳር በሚገባ ሲቋቋም የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳል፣ የውኃ ስርገትን ይጨምራል፣ የአፈር ለምነትን በእጅጉ ያሻሽላል፣ ለተለያዩ ብዝኃ ሕይወት ዓይነቶች አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጥቅማችንን ያጎለብትልናል፣ የሠራናቸውን ኢነርጂ አመንጪ ግድቦች ህልውና ያስረዝምልናል። ይሁንና ችግኞች ራሳቸውን ችለው እስኪቆሙ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ውኃ ማቅረብ፣ ዓረም ማስወገድ፣ ድጋፍ ማበጀት፣ ከእንሰሳት ንክኪና ከሌሎች እሳትን ከመሳሰሉ አደጋዎች መከላከል ያስፈልጋል። አንዴ ራሳቸውን ችለው ሲቆሙ ግን ራሳቸው ሚዛናቸውን ጠብቀው መሄድ ስለሚችሉ እንክብካቤያችን እየቀነሰ ይሄዳል።

ችግኞችን ተክለን መንከባከብ እንዲህ ዓይነት ታላቅና አይተኬ ዋጋ ያለውን ያህል የተቋማት ግንባታም እንዲሁ የማያቋርጥና የማያወላዳ እንክብካቤ ይፈልጋል። የምናደርገው እንክብካቤ ለተቋማቶቻችን አመቺ ሁኔታን እየፈጠረ ሲሄድ ደግሞ እነዚህ ተቋማት የተቋቋሙለትን ዓላማ በሚገባ ለማሳካት መልካም መደላድል ይፈጥርላቸዋል። ያቋቋምናቸው የሰላም ተቋማትም ሲዘልቁና ፍሬ ማፍራት ሲጀምሩ እንዲህ ዓይነት የማይተካ ጥቅም በዘላቂነት ለአገራችን ይሰጡናል።

ይህ ጽሑፌ በዋናነት የሚያጠነጥነው ለሰላም ውጥኖቻችንንና ተቋማቶቻችን አመቺ ሁኔታ የመፍጠር አስፈላጊነትና ልንወስድ የሚገባን አንዳንድ ጠቃሚ ብዬ የማስባቸው ዕርምጃዎች ላይ ነው። በእኔ እምነትና አመለካከት የሰላም ውጥኖቻችንና ተቋማቶቻችን ግባቸውን እንዲመቱ የሚያስፈልገው አመቺ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እንደጎደለ አስባለሁ። ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ችግኞቻችን በአዲሱ ዓመት የሰላም ውጥኖቻችንና ተቋማቶቻችንን የምንንከባከብበትና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ የምንችልባቸውን ስልቶች መንደፍ ያስፈልገናል። የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን እንዲህ ይላሉ፣ ‹ሰላም የግጭቶች አለመኖር አይደለም። ይልቁንም ሰላም ከማንኛውም የልዩነታችን ሰበቦች በላይ የሰዎች ሕይወት  የሚሻሻልበት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነው።› ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ለሰላም ውጥኖችንና ተቋማቶቻችን አመቺ ሁኔታዎችን አልፈጠርንላቸውም ብዬ አስባለሁ።

ለመሆኑ ለሰላም ተቋማቶቻችንና ውጥኖቻችን ስኬት የሚያስፈልጉ እንክብካቤዎች ምንድናቸው? ምን ብናደርግ ነው አመቺ ሁኔታን ደረጃ በደረጃ እየፈጠርንላቸው መሄድ የምንችለው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሦስት ጉዳዮችን አንስቼ የሌሎች አገሮች ልምዶችን እንደ ምሳሌ እያቀረብኩ ለማስረዳት እሞክራለሁ። እነዚህ ሦስቱ የሰላም ኮሪደሮች ብዬ ቀጥዬ የማብራራቸው አመቺ ሁኔታዎች በአስተሳሰብ፣ አንደበትና ድርጊት ላይ ያተኩራሉ።

በነገራችን ላይ በዚህ ጽሑፌ ላይ ደጋግሜ የፖለቲካ መሪዎቻችንን ማንሳቴ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ የተለዩ ፍጡራን ናቸው በሚል ዕሳቤ አይደለም። የፖለቲካ መሪዎቻችን የተቀዱት ከዚህ ኅብረተሰብ ስለሆነ የባህርይ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም። ይልቁንም የፖለቲካ መሪዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ከማናቸውም ሌሎች ክፍሎች የበለጠ ተፅዕኖ ማምጣት ከሚችሉ ጥቂት ቡድኖች ውስጥ አንዱ በመሆናቸው የእነሱ በጎም ሆነ ክፉ ተግባር በአገር ላይ የጎላ ተፅዕኖ ያመጣል ከሚል አመለካከት ተነስቼ ነው። የፖለቲካ መሪዎች ስል በሁሉም ጎራና ሥፍራ ያሉትን ማለቴ እንደሆነም አስቀድሜ አሳውቃለሁ።

በጎ አስተሳሰብ እንደ ሰላም ኮሪደር

አንድ ከኢትዮጵያ ውጭ የሰማሁት አባባል ‹ዛፍ እንድቆርጥ ስድስት ሰዓት ከሰጠኸኝ የመጀመሪያውን አንድ ሰዓት መጥረቢያውን በደንብ ለመሣል እጠቀምበታለሁ› ይላል። ያለ በቂ የአስተሳሰብ ዝግጅት ግጭትን ለማቆምና የሰላምን ሥራ ለመሥራት መሞከር ዛፍን በደነዘ መጥረቢያ ለመቁረጥ በከንቱ እንደመታገል ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የአገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች በዓለም ላይ በፍፁም ተሰምተውና አጋጥመው የማያውቁ፣ መፍትሔም ልናገኝላቸው የማንችላቸው አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንቶኔ የተባለችው አገር እንደፈረሰች ኢትዮጵያ ላለመፍረሷ ምን ዋስትና አለን? ይሉኛል:: እኔ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ሩዋንዳ… የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የነበሩ እጅግ ውስብስብ ችግሮች እንደተፈቱ፣ እኛም ችግሮቻችንን ለመፍታት ምን ያግደናል? ብዬ ምላሽ እሰጣቸዋለሁ። በውነቱ ከዚህ አንፃር አስተሳሰባችን ፈውስ ያስፈልገዋል ብዬም አምናለሁ። ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ካጋጠማቸውና መውጣት ካቃታቸው አገሮች ልንማራቸው የሚገቡን ትምህርቶች እንዳሉ ባምንም፣ ውስብስብ ችግሮችን ተቋቁመውና መፍትሔዎችን ደረጃ በደረጃ ተልመው አገራቸውን የታደጉ ሕዝቦች ይልቁንም ዋነኛ ተምሳሌቶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ ባይ ነኝ።

በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከሰላማዊ አማራጮች ይልቅ የኃይል አማራጮችን መጠቀም ይቀናናል። ይህም አንድ የከረመብን ፅኑ በሽታችን ነው። ምን ያህል ሰው ቢሞት እንደምንደነግጥና ቆም ብለን ማሰብ እንደምንጀምር አላውቅም። ሦስት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሲፈራረቁ በዚሁ አገር ውስጥ እንደተወለደና እንዳደገ አንድ ዜጋ ደፍሬ መመስከር የምችለው ዱለኝነት፣ ማናለብኝነት፣ ግትርነት፣ እኔነትና የእኔ ብቻነት በፅኑ የሚያጠቃን መሆኑን ነው። አንድ የፖለቲካ አመራር ትውልድ አልፎ ሌላው ሲተካ በቃ አሁን የፖለቲካ ባህላችን ሊቀየር ነው ብለን በጉጉት ስንጠብቅ ነገሮች ባሉበት ሲሄዱ አስተውያለሁ። ለአፍታም ቢሆን የተቀየሩ ነገሮች ዓይተን ልባችን ዳንኪራ መርገጥ ስትጀምር በቅጽበት የልብ ድካም የሚያስይዙ ነገሮች ሲከናወኑም ተመልክቼያለሁ።

ይህ ዱለኝነታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትዝብት ላይ እንደጣለን አንድ ምስክር ላንሳ። ጆን ፖል ሌደራክ የተባሉ ታዋቂ የሰላም ምሁርና ጸሐፊ ስለዚህ ደዌያችን የመሰከሩት ምስክርነት አንገት የሚያስደፋ ነው። በኤስዋቲኒ (ስዋዚላንድ) ‹የችግር መፍትሔ ያለው በብርቱ ውይይት ውስጥ ነው› የሚል አባባል አለ። በኢትዮጵያ ደግሞ ‹ጉልበት ሲደክም ምላስ ይረዝማል› የሚል አባባል እንዳለ አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪ ነግሮኝ ነበር ይላሉ። ይህ አስተሳሰብና አባባል ውይይት የብርቱዎች ሳይሆን የደካሞችና የቂሎች መሣሪያ ነው የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ምሁሩ  ያሰምሩበታል። ለካስ በተደጋጋሚ ከጠረዼዛ ወደ ጠብመንጃ የሚመልሰን አንዱ የአስተሳሰብ በሽታችን ይህ ኖሯል?

ዴዝሞንድ ቱቱ በደቡብ አፍሪካ ያለው ውስብስብ ችግር እንዲፈታ ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላ በዓለም ሁሉ እየተዘዋወሩ በርካታ የሰላም ሥራን ማገዝ ችለዋል። በጻፉትም አንድ መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹አምላክ በእውነት ሰዎችን ማሳቅ ይችልበታል፣ በውኑ ደቡብ አፍሪካ የምስቅልቅል፣ የቀውስ፣ የክሽፈት፣ የአገር ውድቀት እንጂ የሰላም ተምሳሌት ሆና ዓለምን ታስተምራለች ብሎ ማን አስቦ ያውቃል? ከሌሎች የተሻልንና የበለጥን ስለሆንን ሳይሆን፣ አምላክ ራሱ ስለረዳን ብቻ ሰላምን ማምጣት ችለናል። ታዲያ እንዲህ በፍፁም በሰዎች ያልታሰብነውን የሰላም ፀሮች አስታርቆን ዛሬ አምላክ ለመላው ዓለም እንዲህ የሚል የምሥራች ያውጃል፣ ‹እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን አፓርታይድ የሚባል ትልቅ ስቃይ ነበረባቸው፣ አሁን ግን ያ ሥርዓት አብቅቶለታል። የእናንተም ስቃይ እንዲሁ ያበቃል። እነሱ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ እጅግ አስቸጋሪ ችግር ነበረባቸው፣ አሁን ግን ችግሩን መፍታት ችለዋል፣ ስለዚህ በዓለም ላይ የትም ቦታ ቢሆን ሰዎች የእኛ ችግር ከቁጥጥራችን ውጪ የሆነ ሊፈታ የማይችል ነው ሊሉ አይገባም።› ይኸው የዴዝሞንድ ቱቱ አምላክ በረከት አድሮብን አስተሳሰባችን ተፈውሶ ሥር የሰደዱና በፍፁም በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ አይችሉም ብለን ደምድመን፣ የምንታኮስባቸውንና የምንገዳደልባቸውን ችግሮቻችንን ተቀራርበን ፈትተን እንደ ደቡብ አፍሪካ ለሌሌች ተምሳሌት የምንሆንበት ቀን ይመጣል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ አንፃር በተለይ የፖለቲካ መሪዎቻችን ደግሞ ይህንን የሰላማዊ መፍትሔ አስተሳሰብ የሙጥኝ ብለው መያዝ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ።

በቀውስ አረንቋ ውስጥ በነበሩ ሌሎች አገሮች የሰላም አየር እንዲነፍስ ያስቻሉ የፖለቲካ መሪዎች በመጀመሪያ የተለወጠው አስተሳሰባቸው ነው። ጥቂት ምሳሌዎችን ላንሳ። ለሁለት ተከታታይ መንግሥታት መፈታት ያቃተው የሰሜን አየርላንድ እንቆቅልሽ ሊፈታ እንደሚችል ገና ሥልጣን ሳይይዙ በምርጫው ዋዜማ የተረዱት የእንግሊዙ ቶኒ ብሌርና የአየርላንዱ በርቲ አኸርን አስቀድመው እየተገናኙ ለሰላም ይዶልቱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክሩልናል። ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ ውስብስብ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ በዋነኛ ተዋናዮች ቅርርብ ሊፈታ እንደሚችል አስቀድመው ገና በሮቢን ደሴት ወህኒ ቤት ተረድተው እየተዘጋጁ ቆይተው ነበር። የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ማኑኤል ሳንቶስ መሪነትን ከመጨበጣቸው ከበርካታ ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት የማንዴላን ምክር በመሻት በሰላማዊ አማራጭ መንገድ ላይ እስከ መጨረሻው ፀንተው በመቆየት ሰላምን በአገራቸው እንዲሰፍን ጉልህ ሚናቸውን ተጫውተዋል። እነዚህ የሰላም ፊታውራሪዎች በአገራቸው ምንም የተስፋ ጭላንጭል በጠፋበት ሁኔታ ከኃይል አማራጭ ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን የሙጥኝ ብለው ለመቆየት ሲወስኑ በዙሪያቸው የነበሩ ጠንካራ ተጻራሪ ድምጾችንና የአቻ ጫናዎችን ተቋቁመው መሄድ አስፈልጓቸው ነበር። በተደጋጋሚ አቋም ሊያስለውጡና ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ከባድና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ እየተንገዳገዱም ቢሆን በአመለካከታቸው ፀንተዋል። ዛሬ ዓለምና ትውልድ በሙሉ የሚያጭደው የሰላም ፍሬ የዚህ የፀና ሰላማዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ይህ ለሁላችንም በተለይ ለፖለቲካ መሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ስለዚህ ችግሮቻችን ከእኛ አቅም በላይ እንዳልሆኑ ተቀራርበን በሰላማዊ መንገድ ልንፈታቸው እንደምንችል መረዳት አንዱ ዋነኛ አመቺ ሁኔታ ነው። ይህንን ስል ከግጭት የሚያተርፉ አካላትን ሚና እንዲሁም ሌሎች የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ሊያደርሱ የሚችሉትን ተፅዕኖ ዘንግቼ አይደለም። ለነገሩ በሁሉም አገሮች ታሪክ ውስጥ ግን መጠናቸውና ጥልቀታቸው ይለያይ እንጂ ከእንዲህ አይነት ጫና የፀዳ የለም። ስለዚህ እነዚህን ጫናዎች ለመቆራቆሳችን እንደ ሰበብ አድርገን ልናቀርብ አንችልም።

የመሪዎች ንግግር እንደ ሰላም ኮሪደር

ታሪክም ሆነ ሳይንስ እንደሚያወሳው ሰላም በዋናነት የአንደበታችን ተጠቃሚ ወይም ሰለባ ነው። በተለይም በፖለቲካ መሪዎች የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ንግግሮች ከስሜት የፀዱ ሊሆኑ ይገባል። ማንኛውም ንግግር በአድማጩ ዘንድ ወይ ደስታን አልያም ሕመምን ከሁለት አንዱን ውጤት ይፈጥራል። አስጨናቂ ንግግር በምንሰማ ጊዜ በነርቭ ሥርዓታችን ውስጥ የሚጎርፉ መጥፎ ሆርሞኖች አዕምሮአችንን በመሙላት ለ16 ሰዓታት አካባቢ መቆየት እንደሚችሉ ጥናቶች ይነግሩናል። በዚህ ጊዜ ሰው አዕምሮው ይጠለፍና የማገናዘብና የማስተዋል አቅሙ ተዘግቶ ሙሉ በሙሉ በስሜት የሚነዳ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህም ክፉ ንግግር የሚያመነጫቸው እንደ ኮርቲሶልና አድሬናሊን የመሳሰሉ ሆርሞኖች ሰዎችን ከወትሮው ይልቅ ስሜታዊ በማድረግ በቀላሉ ለግጭትና ለግድያ እንዲሁም ለጦርነት ይጋብዛሉ። አንዳንዴ ሰዎች በእነዚህ ሆርሞኖች ጫና አላስፈላጊና የከፋ አደጋ ካደረሱ በኋላ ‹እንዲያው ብልጭ ብሎብኝ የማደርገውን ሁሉ አላውቅም ነበር› ሲሉ እናደምጣለን። ጥንቃቄ የጎደላቸው፣ አስቆጪና ፍርኃት ጫሪ ቃላት መወራወር በእነዚህ ሆርሞኖች ምክንያት ጫናን በመፍጠር ቀስ በቀስ ወደ ጎጂ ስሜታዊ ውሳኔ ይነዳል። ይህ ክስተት በቤተሰብ ወይም በጓደኞች ደረጃ ሲከሰት ሊያስከትል የሚችለው አደጋ መጠነኛ ሊሆን ይችላል። ፖለቲከኞች ብልጭ ሲልባቸው ግን መዘዙ እጅግ ሰፊና የከፋ ነው።

ለምሳሌ በአንደኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ላይ በ1919 የተፈረመው የቨርሳይል ስምምነት (Treaty of Versailles) የሰላም ስምምነት ተብሎ ይጠራ እንጂ፣ ውጤቱ እጅግ አስከፊ እንደነበር የታሪክ ባለሙያዎች ያወሳሉ። በወቅቱ የነበሩት የፈረንሣይና የእንግሊዝ መሪዎች ጀርመንን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ሲሉ በስሜት ጫና ጠንካራ ውሳኔ በመወሰናቸው ምክንያት በጀርመን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት አስከተለ። ይህ ውሳኔ የመጥፎ ሆርሞን ጎርፍ ካስከተለባቸው ሰዎች አንዱ አዶልፍ ሂትለር በእልህ ተነሳስቶ ጦሩን ሲያደራጅ ከከረመ በኋላ፣ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ የቀጠፈውንንና ከዚህ የማይተናነስ ቁጥር ያለው ሕዝብ ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ያመጣውን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ቆይቶ ሊያስነሳ ችሏል።

በተለይ የፖለቲካ መሪዎቻችን ይህንን ተረድታችሁ በአዲሱ ዓመት አንደበታችሁን ለመግራትና ውሳኔዎቻችሁን በተቻለ መጠን ፍርኃትና ቁጣ ከሚወልደው ስሜት የፀዳ ለማድረግ ጥረት ብታደርጉ መልካም ነው። እነዚህ ክፉ ሆርሞኖች የሚያስከትሉትን አሉታዊ ጫና ለማስቀረት አንደበትን በመግራት የምትናገሩትን ነገር ይዘትና አቀራረብ እየተጠነቀቃችሁ ብትሄዱ ሕዝብና አገርን ከብዙ ጥፋት ትታደጋላችሁ።

የሚያስፈራውና ጥንቃቄ የሚሻው ሌላ ጉዳይ ደግሞ ይህ የስሜት ጫና በተቃራኒ አካላት መካከል የማያቋርጥና የሚያገረሽ የሆርሞኖች ጎርፍ በየተራ በዙር እየፈጠረ፣ ጫናው በዑደት እየተዘዋወረ መሥራቱን መቀጠሉ ነው። በሆርሞን የተጠለፉ አዕምሮዎች ልክ በአልኮል ጫና ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሚሆኑት አቅላቸውን ስተው ከባድ ውሳኔ ከወሰኑና ጎጂ መዘዝ ከተከተለ በኋላ ሰዎቹ የሚባንኑት የሆርሞኑ መጠን ሲቀንስ ነው። ይሁንና በዚያን ጊዜ ግን ብዙ የማይቀለበስ ጉዳት ደርሷል። ደግሞም ሌላኛው ካምፕ የሆርሞን ጎርፍ የወለደው ስሜታዊ ምላሽ ተቀስቅሷል:: ይህንንም ቢሆን ግን ማቆም ይቻላል:: አንድ ምሳሌ ላንሳ።

እ.ኤ.አ. በ1993 የትንሳኤ በዓል ዋዜማ የማንዴላ የቀድሞ ምክትልና የፓርቲው ሁለተኛ ሰው፣ እንዲሁም የወታደራዊው ክንፍ መሪ የነበሩት በኋላም የደቡብ አፍሪካ ኮሙዩኒስት ፓርቲ መሪ የነበሩት በወጣት ጥቁሮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት የነበራቸው ፖለቲከኛ ነበሩ። ክሪስ ሀኒ የትንሳዔ በአልን ሊያከብሩ በሄዱበት ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት በገዛ መንደራቸው በአንድ የነጭ አክራሪ የፓርላማ አባል ተባባሪ የሆነ ነፍሰ ገዳይ አማካይነት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። በሟቹ ታጋይ ላይ ከደረሰው ጉዳትና ቤተሰብና ወዳጆቻቸው ከደረሰባቸው ሐዘን ባልተናነሰ የማንዴላ ሐዘን እጅግ ጥልቅ ነበር። ከብቃታቸውና ከተወዳጅነታቸው የተነሳ የማንዴላ ዕድሜ ከሰባዎቹ ስለዘለለ ዕድሜያቸው ሃምሳ ገደማ የሆነው ክሪስ ሀኒ መሪነቱን በብቃት ተረክበው ይሠራሉ የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም ያም በአንዴ ጨለመ።

ክሪስ ሀኒ በግፍ በተገደሉ ዕለት ማንዴላ ሕዝቡን ለማረጋጋት ታስቦ ለአገሪቱ በመንግሥታዊው መገናኛ ብዙኃን ልብን የሚነካ ንግግር ተናግረው ነበር። ከዚህ ንግግራቸው ውስጥ አንዱን ልጥቀስ፣ ‹በጥላቻና በቅድመ ብያኔ የተሞላ አንድ አክራሪ ነጭ አገራችንን በእርስ በርስ ዕልቂት ለማተራመስ አቅዶ ይህን ዘግናኝ ወንጀል በጓዳችን ላይ ፈጸመ፡፡ በሌላ በኩል ግን አንዲት ሌላ ነጭ አፍሪካነር ደግሞ የገዛ ሕይወቷን አደጋ ላይ በመጣል የገዳዩን መኪና ተከታትላ ታርጋ ቁጥሩን በመመዝገብ ለፖሊሶች ደውላ በማሳወቋ ውዲያው ገዳዩ በክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።›

ማንዴላ በዚያች የበዓል ምሽት የተፈጠረባቸው ጥልቅ ሐዘንና የግድያው አረመኔያዊነት ምንም ነገር ሕዝብ ፊት ቆመው ቢናገሩ የሚያስወቅሳቸውም የሚያስፈርድባቸውም አልነበረም። ይሁንና በንግግራቸው በሚፈጠር ቁጣ ሊከተል የሚችለውን አገር አቀፍ ዘርን ያማከለ የርስ በርስ ቀውስ አስቀድመው በመገንዘባቸው፣ የራሳቸውን ቁጣ ተቆጣጥረው በንዴት የጦፈውን ሕዝብ ለማብረድ ከጓዶቻቸው ጋር መልካም አመራር በመስጠት ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላ ተስተጓጉሎ የነበረው የሰላም ውይይት እንዲቀጥልና በመጪው ዓመት ምርጫ እንዲደረግ መሠረትን ጥለዋል። በምርጫውም ፓርቲያቸው አሸንፎ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር መሪ ሆነው እንዲመረጡ አስችሏቸዋል። ታዲያ ማንዴላ እንዲህ ሲሉ ምክራቸውን ይለግሱናል፣ ‹የሰላም ሥራ ለትልቁ መልካም ዓላማ ሲባል የራስን ፍላጎት መግደልን ይፈልጋል፡፡›

ዛሬም አንዱ ዋነኛ የሰላም መደላድልና ማፅኛችን የአንደበት ተኩስ አቁም ነው:: እባካችሁ የፖለቲካ መሪዎቻችን በአዲሱ ዓመት የአንደበት ተኩስ በማቆም የመጥፎ ሆርሞኖች መጫወቻ ላለመሆን ለራሳችሁ ቃል ግቡ።

ትምምንን የሚያጎለብቱ ድርጊቶች እንደ ሰላም ኮሪደር

ትምምን በዋጋ የሚገኝ እንጂ በነፃ የሚሰጥ ችሮታ አይደለም። ለመታመን ዋጋ መክፈልና ተጨባጭ ነገሮችን በተግባር ማሳየት አለብን። ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ1990 መጀመሪያ ላይ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዴክላርክ ጋር በዘዴ በመቀራረብና ትምምንን በመፍጠር ለፓርቲያቸው መሪዎች፣ ‹ይህንን ሰው መታመን የሚችል ሆኖ አግኝቼዋለሁና ከእሱ ጋር የሰላም ውይይት ማድረግ እንችላለን› የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ፓርቲያቸውን ለድርድር እንዲዘጋጅ አድርገዋል። ክሪስ ሀኒ ይህንን ድርድር በመደገፍ ‹አክራሪ አሸባሪ› ብለው ከሚጠሯቸው የገዥው አፓርታይድ መሪዎች አንዳንዶቹ ዘንድ በመሄድና በማነጋገር ትምምንን በመፍጠር ድልድይን በመገንባት ይታወቁም ነበር።

በሰሜን አየርላንድ የተጓተተ የሰላም ሒደት እ.ኤ.አ. በ1997 በእንግሊዝና በአየርላንድ አገራዊ ምርጫዎች ወደ መሪነት ያመጧቸው ቶኒ ብሌርና በርቲ አኸርን በዘጋቢዎች ዘንድ ‹ኮከቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ገጠሙ› ያሰኘ መልካም ክስተት ነበሩ። ኮከቦቹ እንዲገጥሙ ያደረገው ክስተት ግን እንዲያው በድንገት የተከሰተ ዕድል አልነበረም። ከምርጫው በፊት ሁለቱም መሪዎች ሊያሸንፉ እንደሚችሉ በመገመት እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ በአገሮቻቸው ዋና ከተሞች ለንደንና ደብሊን በተደጋጋሚ እየተገናኙ መምከርን ያዘወትሩ ነበር። በውይይታቸውም በሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያዎቹ 18 ወራት ሰላምን ለማስፈን እንዲቻል ጠንካራና እውነተኛ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ እርስ በርስ ተስማምተው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በርቲ አኸርን ሰሜን አየርላንድ ከብሪታንያ ተገንጥላ ከአየርላንድ ጋር እንድትዋሀድ የሚዋጋውን የአየርላንድ ታጣቂ ቡድን መሪዎችን በማነጋገር ለተኩስ አቁም እንዲስማማ፣ ቶኒ ብሌር ደግሞ ሰሜን አየርላንድ ከእንግሊዝ ጋር በውህደት እንድትቀጥል ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመነጋገር ሁሉንም ያካተተ ምክክር ለመጀመር እንዲያግባቧቸው ተስማምተው ነበር።

በዚህ አበረታች የመሪዎቹ ጥረት መሀል የሰሜን አየርላንድ ምክክር በተጀመረ በ11 ዓመቱ እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 1996 በለንደን ካናሪ ዋርፍ በተባለ ቦታ የአየርላንድ ታጣቂዎች ያደረሱት የቦምብ ጥቃት ሁለት ሰዎችን ገድሎ ሌሎች መቶ ሰዎችን ቁስለኛ ከማድረጉም በላይ፣ በወቅቱ ግምት 150 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራ አስከትሎ ነበር። ይህ ጥቃት ለጊዜው ሥራ ላይ ውሎ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣሱ ውይይቶች መቋረጣቸው ብቻ ሳይሆን፣ በያለበት የርስ በርስ ግጭት እንደገና እንዲያገረሽ አደረገ። ቶኒ ብሌርና በርቲ አኸርን እየተገናኙ ሲነጋገሩ ይህንን ሳያውቁት ቀርተው አልነበረም። እንዲያውም በዚህ ጥቃት ምክንያት የአየርላንድ መንግሥት እንኳን ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ማናቸውንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ለማቆም በወሰነ ጊዜ ገና በምርጫ ለመወዳደር አስበው የነበሩት በርቲ አኸርን በሩን ጥርቅም አድርገው ከመዝጋት ይልቅ፣ በግላቸው የቡድኑን መሪ ጄሪ አዳምስ በሚስጥር እያገኙ ቡድኑ ተኩስ አቁሞ በሰላም ሒደቱ ውስጥ እንዲቆይ ይጎተጉቱት እንደነበር ይታወቃል።

ብሌርና አኸርን እንደቀደሙት መሪዎቻቸው የርዕዮተ ዓለም ጭነት የተጫናቸው ሳይሆኑ ሐሳባቸውን በመግለጽ ቀጥተኞችና ግልጽ ነበሩ። በተጨማሪም ሁለቱም እግር ኳስ መውደዳቸው ደግሞ ሌላው ያቀራረባቸው ነገር ነበር። ያለ ማንም ሌላ ባለሥልጣን መገኘት በቀጥታ በስልክ በመነጋገር ፈርቀዳጅ መሪዎችም ነበሩ። ሌላው አስገራሚ ነገር ገና እ.ኤ.አ. በ1995 በአየርላንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ሆነው ሳሉ ወደ ሰሜን አየርላንድ ዋና ከተማ ቤልፋስት እየተመላለሱ ታዋቂ ከሆኑት የውህደት ደጋፊ ፓርቲ መሪ ዴቪድ ትሪምብል ጋር ቅርርብ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ነው። አኸርን አባል በሆኑበት ፓርቲ ታሪክ ይህ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አዲስ ክስተት ነበር። ይህ ግንኙነታቸው በቀጣዮቹ ዓመታትም ቀጥሎ አኸርን በመሪነት ሲመረጡም ስለዘለቀ መልካም ትምምንን በሁለቱ መሪዎች መካከል መፍጠሩን ቀጥሎ በአዲስ መንፈስ ለተጀመረው ውይይት መልካም መሠረትን የጣለ ነበረ። ይህንን ቅርርባቸውን ለየት የሚያደርገው መንገድ ሚስጥራዊ ውይይቶቻቸውን ይፋ ባልሆነ መንገድ በሳምንት መጨረሻ ቀናት ውስጥ እያደረጉ ሁለቱም ለሰላሙ ሥራ በየፊናቸው የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች ከልባቸው እየተጨዋወቱ አብረው መላ ማፈላለጋቸው ነበር። ይህ ቅርርብ ግን በተለይ ውህደት አራማጁ ትሪምብል ላይ ከሌሎች ጓዶቻቸው ‹በሌላው ቡድን ተገዝተሃል› እስከመባል ድረስ የገዘፈ ወቀሳና ውግዘትን አስከትሎባቸው ነበር። ይሁንና ከአኸርን ጋር በደኅና ጊዜ የመረቱት መቀራረብ ጠንካራ ስለነበር ትሪምብል በይፋ ያለ ምንም ማወላወል ‘በርቲ አኸርን የማምነው ሰው ነው፣ ወደፊትም አብሬው መራት እንደምችል ይሰማኛል፤› ሲሉ ይደመጡ ነበር።

በጠረጴዛ ዙሪያ ተገናኝቶ መነጋገር በጠመንጃ የመሞሻለቅን ያህል ቀላል ውሳኔ አይደለም:: በተወሰነ ደረጃ እርስ በርስ መተማመንን ይፈልጋል። መቀራረብ ደግሞ ራስን ዝቅ ማድረግን፣ የሌሎችን ትችትና ውግዘት መታገስን፣ ማዳመጥን፣ ሚስጥራዊነትንና ስሜታዊ ብስለትን ይጠይቃል። አንዳንዴ ከፖለቲካ መሪዎቻችን የምንሰማው ‹ከእነ እገሌ ጋርማ ምንም ውይይት አያስፈልግም› የሚል ድምፅ ለሰላማችን ትልቅ ደንቃራ ነው። ዴዝሞንድ ቱቱ እንዲህ ይላሉ፣ ‹በእውነት ሰላም የምትፈልግ ከሆነ ከወዳጆችህ ጋር ሳይሆን ከጠላቶችህ ጋር ተነጋገር።›

በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ መሪዎቻችን እርስ በርስ የሚጎበኛኙበት፣ ይፋ ባልሆነ መንገድ እየተገባበዙ የሚጨዋወቱበት፣ አንዱ ሌላውን ተቃዋሚውን ስልክ ደውሎ ቀጠሮ ይዞ ጨዋታን የሚጀምርበት፣ ቀስ በቀስ ወዳጅነትን እየገነባን ለእውነተኛ የሰላም ውይይት አመቺ ሁኔታን የምንፈጥርበት እንዲሆን እመኛለሁ። እንዲያውም ተደጋጋሚ የእራት ግብዣዎች እየተደረጉ ተፅዕኖ አምጪ መሪዎች እርስ በርስ ሐሳብ እየተለዋወጡ ግንኙነትን የሚያጎለብቱበት መድረኮች እየበዙ ቢሄዱ መልካም ነው። ታዲያ በመጪው ዓመት ከምናጠናክራቸው ወዳጅነቶች የተነሳ ‹እንቶኔን አምነዋለሁና ከርሱ ጋር ለሰላም መወያየትና አብሬ መሥራት እችላለሁ› የሚሉ ድምፆች እንዲበረክቱ እመኛለሁ። በተለያዩ ክስተቶች ምክንያት በመካከል መጠራጠርና ቆም ማለት ሊያጋጥም ይችላል። ይሁንና የውይይትን በር ጥርቅም አድርጎ መዝጋትና ከጠረጴዛ ማፈግፈግ ለእኛም ለምንመራቸውም ጓዶቻችንም ለመጪውም ትውልድ ፋይዳ የለውም።

በመጨረሻ ሁለት ነገሮችን በአጭሩ ማንሳት እፈልጋለሁ። በሌሎች አገሮች ታሪክ እንዳየነው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በተለይ የፖለቲካ መሪዎች አንዳንድ የደረሱባቸውን በደሎች ለትልቁ ዓላማ መሳካት ሲሉ መርሳት ይገባቸዋል። በሰላም ግንባታ ሥራ ይህ ስልታዊ መዘንጋት ተብሎ ይጠራል። በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ መሪዎቻችን እባካችሁ እንደ ኔልሰን ማንዴላ አንዳንድ ነገሮችን ሆን ብላችሁ በመዘንጋት እኛም እየረሳን እንድንሄድ አግዙን። ሌላው ጉዳይ በአገራችን ያሉ ቅያሜዎችንና ግጭቶችን ለመፍታት አሁን ያሉን ተቋማትና ውጥኖች በቂ ናቸው ብዬ አላስብም። ይልቁንም አሁን ያሉንን ውጥኖች በእጅጉ ሊያግዝ የሚችል ሆኖ ነገር ግን ገና በቅጡ ያላቋቋምነው አንድ ውጥን ያለ ይመስለኛል። ይህም ዕርቅና ይቅርታን በቋሚነት የሚሠራ ተቋም ነው። አሁን ያሉን ውጥኖች በአሁኑ ጊዜ ያሉብንን አስቸኳይ የማስታረቅ ሥራ ለመሥራት የሚችሉ አይመስለኝም። ለዚህም በአዲሱ ዓመት በአገሪቱ ከሞላ ጎደል የተሻለ ተቀባይነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ተመርጠው የሰላም ልዑካን ተብለው ቢሰየሙና የማቀራረብና የማወዳጀት ኃላፊነት ቢሰጣቸው የሚል ሐሳብ አቀርባለሁ።

አብርሃም ሊንከን በተናገሩት አንድ አባባል ጽሑፌን ልቋጭ፣ ‹የእኔ ዋንኛው ሥጋት በእውኑ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ወይ የሚል ሳይሆን፣ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ነን ወይ የሚለው ነው›፡፡ እኔም እስከ ዛሬ ካየሁትና ከሰማሁት ተነስቼ የጠበቀንና የረዳን አምላክ ከእኛ ጋር እንደነበረ ነገም ከእኛ ጋር እንደሚሆን አልጠራጠርም። ውድ መሪዎቻችንና ወገኖቼ በአዲሱ ዓመት እርሱ በእርግጥ ከእኛ ጋር ነው፣ እኛም ታዲያ ከእርሱ ጋር እንሁን። በፍፁም የሚያቅተን ነገር አይኖርም።

አዲሱ ዓመት በመላው ኢትዮጵያ እነዚህንና ሌሎች የሰላም ኮሪደሮችን የምንገነባበት ይሁንልን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ መሥራችና አስተባባሪ፣ እንዲሁም የሰላም አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው negusumb@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡