ዳዊት ታዬ

September 8, 2024

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዙሪያ የፖሊሲ ለውጦችና በርካታ የሚባሉ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገውባቸዋል ተብሎ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ወቅቶች ውስጥ የ2016 በጀት ዓመት በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በተለይ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንፃር ሥር ነቀል የሚባሉ ለውጦች ተካሂደዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ እንግዳ የሚባሉ የኢኮኖሚ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ሕግጋቶች ወጥተዋል፡፡ ከዓመታት እልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አዳዲስ ብድሮችና የገንዘብ ድጋፎች ለማግኘት የተቻለበትም ዓመት ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ በጀት እንዲጨምር ያስቻለ ሆኗል፡፡  

ከሁሉም በላይ ግን ለዓመታት ፈራ ተባ ሲባልበት የነበረውና በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጭምር የተለያየ አመለካከት የተንፀባረቀበት የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲገበያይ መወሰኑ፣ በ2016 በጀት ዓመት ከኢኮኖሚ አንፃር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ክንውን በመሆን በቀዳሚነት የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ሊባል የሚችለው ውሳኔ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ገበያን መሠረት ባደረገ መልኩ ብቻ እንዲስተናገድ አድርጓል፡፡ ይህንን ለውጥ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት ሲሆን፣ ጠቀሜታውን አመላተዋል፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ በዓመቱ የመጨረሻ ሳምንት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ እንደገለጹትም፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተቀናጀና በተሟላ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገጽታና የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ከመሠረቱ በሚለውጥ ታሪካዊ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡ ሁለተኛውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች የተሠሩ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ይህ የሪፎም ሥራ አሁንም ቀጣይ ስለመሆኑ የሚጠቁመው የገዥው ንግግር በተለይ በአብዛኛዎቹ ቁልፍ በሆኑ ማክሮ ተቋማት በኩል በመካሄድ ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም እንደ ማዕከላዊ ባንክነቱ፣ የተወለበትን ሕዝባዊ፣ መንግሥታዊና ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በርካታ ሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ ከእነዚህም ሪፎርም ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መዘርጋት ሥራ ላይ ማዋል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት ሳይለወጥ የቆየውንና በርካታ ክፍተቶችና እጥረቶች የነበሩበትን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻልና የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነትን፣ እንዲሁም ዕድገት የሚያሰፉ፣ የክፍያ ሥርዓቱንና ዲጂታል ፋይናንስ አጠቃቀም የሚደግፉ የፖሊሲ ዕርምጃዎችንና አሠራሮችን ማስተዋወቅና መተግበር እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ መንግሥት የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ እንዲወስን ማደረጉ አደጋ እንዳለው የሚገልጹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ውሳኔውን ተችተዋል፡፡ ከወቅታዊው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር ብርን ማዳከም በፍፁም ተገቢ ስላለመሆኑ የተለያዩ ትንተናዎችን በመስጠት ሥጋታቸውን ሲገልጹ ተሰምቷል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዙሪያ ጥናት በማድረግና ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) ውሳኔው እጅግ ያስደነገጣቸው ስለመሆኑ በመግለጽ ቀዳሚ ነበሩ፡፡

እንደ አቶ ክቡር ገና ያሉ ታዋቂ ሰዎችም የውጭ ምንዛሪ ገበያ ዋጋ ይወሰን መባሉ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ውሳኔ ተገቢ ነው፤›› ከዚህ የተሻለ አማራጭ አለመኖሩን በመግለጽ ሐሳባቸውን ሲገልጹ የነበሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረግ እንዲያውም ዘግይቷል በማለት ሞግተዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ምልከታ ካንፀባረቁ የኢኮኖሚ ምሁራን መካከል ታዋቂው ኢኮኖሚስት ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ ቆስጠንጢኖስ በረሃ (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ የምንዛሪ ዋጋ በገበያ ዋጋ መወሰኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ተመንን በተመለከተ የትኛውም ዕርምጃ ቢወሰድ ሕመም ይኖረዋል የሚል አመለካከት ያላቸው ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ የምንዛሪ ዋጋን በገበያ መወሰን ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚገለጹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በዋናነት የሚጠቅሱት፣ ‹‹የዋጋ ንረትን ያብሳል›› የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዕዳ ክፍያ ያከብዳል በማለት ሲሞግቱም ሰምተናል፡፡

 የትኛውም መውጫ አንድ ሕመም ያለው ቢሆንም፣ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ እንዲሆን መወሰኑን ግን የተሻለው አማራጭ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡

ከሞላ ጎደል ውሳኔው እንዲህ ያሉ ሁለት አመለካከቶች ያሉት ቢሆኑም፣ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ያስከትላል የተባለው ተፅዕኖ ብዙም አልታየም፡፡ በጥቁር ገበያውን በመደበኛው የምንዛሪ ጋር ያለው ልዩነት በእጅጉ ከመጥበቡም በላይ የጥቁር ገበያ በእጅጉ ይጨምራል የተባለው ሥጋት ግን እንብዛም አልታየም፡፡ በገበያ ውስጥ ይፈጠራል ተብለው የዋጋ ንረት ቀደም ብሎ ሲነገር እንደነበረው ሊሆን አለመቻሉ በራሱ አነጋጋሪ ቢሆንም፣ ይህ ያልሆነበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ቀደም ብሎ ቢሆን ኢኮኖሚው ሲዘወር የነበረው የጥቁር ገበያን መሠረት አድርጎ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ማሞ ምሕረቱ ከሰሞኑ ከሰጡት ማብራሪያ የጥቁር ገበያ በእጅጉ ይጨምራል የተባሉት ሥጋት አልታየም፡፡ በገበያ ውስጥ ይፈጠራል ተብለው የዋጋ ንረት ቀደም ብሎ ሲነገር እንደነበው ሊሆን አለመቻሉ በራሱ እንደ መልካም የሚታይ ሆኗል፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ መመርያው የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ አከፋፈትና አጠቃቀም ሁኔታዎችን፣ የሐዋላ አላላክ ዘዴዎችን በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን የሚያሳልጥና የፋይናንስ አካታችነትን የሚያጎለብት ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ለውጥ በተካሄደ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በትይዩ ገበያና በባንኮች የውጭ ምንዛሪ ገበያ መካከል ያለው የተመን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃና በፍጥነት ቀንሷል፡፡ በሁለቱ ገበያዎች መካከል ከለውጡ በፊት 100 በመቶ የነበረው የተመን ልዩነት ከሐምሌ 22 እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ወደ አራት በመቶ ወርዷል፡፡ ይህም የትይዩ ገበያ አስፈላጊነትና ጥቅም ትርጉም እያጣና በአንፃራዊነትም እየተዳከመ መምጣቱን ያሳያል በማለት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመርያው በአግበቡ ሥራ ላይ መዋሉንና የውጭ ምንዛሪ ገበያው በጤናማ ውድድር ላይ የተመሠረተና ግልጽነትን የተላበሰ እንዲሆን ክትትልና ቁጥጥር መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም አዲስ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሥርዓት በመጀመሩ በለውጡ የመጀመሪያ ቀናት በባንኮች ዘንድ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ረገድ ይታይ የነበረው መደናገርና የተራራቀ የውጭ ምንዛሪ ተመን አወሳሰን እየተስተካከለና አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መልክ እየያዘ ስለመምጣቱ አቶ ማሞ ምሕረቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግብይትና ተያያዥ አሠራሮች ጋር አሁን ባለው ሁኔታ ይፈጠራሉ የተባሉ ችግሮች እምብዛም አልታዩም ቢባልም፣ ችግሩ ቀስ በቀስ የሚታይበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል አስተያየት ያላቸው አሉ፡፡ በተለይ በባንኮች አካባቢ ትልቅ ችግር የሚሆንበት ሁኔታ መኖሩን የሚጠቆሙ ያነጋገርናቸው ፋይናንስ ባለሙያዎች የምንዛሪ ገበያው መለወጡ ባንኮችን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው ይላሉ፡፡ ከኤልሲ አፈቃቀድ ጋር ተያይዞ በውጭ ባንኮች ማወዳደር የሚገባቸውን ገንዘብ በአዲሱ የምንዛሪ ተመን የማወራረድ ግዴታ ስላለባቸው ይህ ግዴታ ደግሞ ከፍተኛና ያልተጠበቀ ወጪ እንዲያወጡ ያስገድዳቸዋል ይላሉ፡፡

ለዓመታት በውጭ ባንኮች ያላወራረዱት ገንዘብ ያለባቸው ከ10 ያላነሱ ባንኮች እንዳሉ የጠቆሙት እነዚሁ የባንክ ባለሙያዎች፣ ከዚህ ቀደም በነበረ የምንዛሪ ዋጋ ኤልሲ የከፈሉ ባንኮች አሁን ሒሳቡን የሚያወራርዱት በአዲሱ የምንዛሪ ዋጋ በመሆኑ፣ ገንዘቡን ለማወራረድ ወደ ዕጥፍ የተጠጋ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃቸዋል፡፡ ይህም የባንኮቹን ወጪ ስለሚጨምር ትርፋቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ የቀረ መሆኑን ገልጿል። ማሻሻያው ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት በመቻላቸው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያሻሽላል ተብሏል።

ከብሔራዊ ባንክ ይፋዊ መግለጫ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቀደም ብሎ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ላይ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ እንዲወሰን ልታደርግ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ሳያግባባት የቆየውን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ውሳኔ በገበያው ላይ ባለ የግብይት ተመን እንዲወሰን የሚያደርግ ይሆናል በማለት በመግለጫው መጠቀሱ ይታወሳል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ፋይናንስ ነክ ክንውንኖች መካከል የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶች 1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) የካፒታል ማሰባሰቢያውን ማጠቃለያና የገበያውን ደንብ አስመልክተው ከሰጡት ገለጻ መረዳት እንደሚቻለው፣ ለገበያው ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 631 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰበሰበው ካፒታል 1.5 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ከዕቅዱ በ240 በመቶ ብልጫ ያለው አፈጻጸም መመዝገቡን ያሳያል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ 48 በፋይናንስና ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ ባሉ መስኮች የተሠማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች አክሲዮኖችን በመግዛት በመሥራችነት ተሳታፊ ሆነዋል።

ከዚህ ባሻገር በበጀት ዓመቱ ከሚታዩ ኢኮኖሚያዊ ከሆኑ የፖሊሲ ለውጦችና የመንግሥት ውሳኔዎች መካከል ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አንዱ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቀደው ሕግም የቀረበ ሲሆን ተፈጻሚነቱ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህም ውሳኔ ቢሆን ብዙ ሲያከራክር ከሟል፡፡ በውጭ ባንኮች መግባት ዙሪያ በተለያዩ ተቋማት፣ የውይይት መድረኮች ተዘርግተው ሲመከርባቸውም ነበር፡፡ በእነዚህ መድረኮች በአብዛኛው የውጭ ባንኮች መግባት የአገር ውስጥ ባንኮችን ይጫናል የሚሉ አስተያየቶች የጎሉባቸው ቢሆንም፣ ብዙዎች ግን ኢትዮጵያ ራሷን ነጥላ መቆየት የሌለባት በመሆኑ፣ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት እንጂ በፍራቻ ውሳኔውን ማስቀልበስ ተገቢ ያለመሆኑን ያስረዳል፡፡

የፋይናንስ ተቋማትን በተመለከተ 2016 በጀት ዓመት ሳይገለጽ የማያልፍ ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጸመው የማጭበርበር ታሪክ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የማጭበርበር ተግባር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በመሆን የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚህ የማጭበርበር ተግባር በአንድ ሌሊት ከ8180 ሚሊዮን ብር በላይ ተጭበርብሯል፡፡

በዚህ ድፍረት ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ባንኩ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ከዚህ ያላግባብ ከወጣ ገንዘብ ውስጥ ወደ 93 በመቶ የሚሆነውን ማስመለሱን ገልጿል፡፡   

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አነጋጋሪ ከነበሩ አዋጆች መካከል የንብረት አዋጅ ተጠቃሽ ነው፡፡ የንብረት አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተተገበረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ የዋለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ተሻሽሎ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካትቶ በሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ በዚህ አዋጅ ከዚህ ቀደም አዋጁ የማይመለከታቸው የቢዝነስ ዘርፎች በአዲሱ አዋጅ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በተለይ የኢንሹረንስ ዘርፉ አዋጅ እንዲመለከተው መደረጉ አግባብ አይደለም በሚል አሁንም እየተሞገተ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክሱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን እንዲመለከተው መደረጉ የዓረቦን መጠኑን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ምንም እሴት ባልተጨመረበት ሁኔታ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊከፈልበት ይገባል የሚለው አመለካከት አሁንም ጥያቄ እንደሆነ ነው፡፡

ከአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት በርካታ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርገዋል፡፡፡ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ የአገልግሎት ዋጋ፣ የትራፊክ የቅጣት ዋጋ፣ የሦስተኛውን ግን ዓረቦን፣ የፓስፖርትና ተያያዥ አገለግሎቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡

እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ የኢትዮጵያ ባንኮች በአትራፊነት ቀጥለዋል፡፡ በይፋ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸማቸው የኢትዮጵያ ባንክ አንዱ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያተርፍ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛው አትራፊ ባንክ በመሆን የሚጠቀሰው አዋሸ ባንክ ደግሞ ከታክስ በፊት ከ11.6 ቢሊዮን ብር ማትፉን አመልክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ በፓርላማ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ንግድ ኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ በርካታ ሕጎችና መመርያዎች ወጥተዋል፣ ማሻሻያዎች የተደረገባቸው አዋጆች ነበሩ፡፡

ከእነዚህ ሕግጋቶች መካከል የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ መፍቀዱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ባንኮች ተከልክሎ የቆየው ይህ ቢዝነስ ሌሎችንም እንዲሳተፉበት የሚፈቅድ ነው፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡን ከሚመለከቱ ጉዳዮች መካከል አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ንግግ ምክር ቤት ጠቅላለ ጉባዔና ምርጫ ዕልባት ያገኘው በ2016 በጀት ዓመት ማግኘት መቻሉ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከአዋጁና ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ በስድስት ዓመታት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ የቆው ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአስገዳጅነት ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫ ማካሄድ ችሏል፡፡

በዚህም ከኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተወከሉት አቶ ሰብስብ አባፊራ የንግድ ምክር ቤቱ ፐሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቶቹ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ ደግሞ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ ከደንብና ከአሠራር ውጪ ተፈጥሯል በተባለ ችግር ዋና ጸሐፊውና ምክትሎቻቸው እንዲታገዱ መወሰኑ ነው፡፡  

ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ ስድስት የባንክ ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ኃላፊነታቸውን ከለቀቁት መካከል አቶ ሔኖክ አበበ የአማራ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ገነነ ሩጋ የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሙሉጌታ አስማረ የጎህ ቤቶች ባንክ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ግሩም ፀጋዬ የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ከበደ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንትና ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር እስካሁን በባንክ ኢንዱትሪ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 12 የቀድሞ የንብ ኢንተርናሽና ባንክ ዳይሬክተር ቦርድ አባላትን በሙሉ እንዲታገዱና እስከ ስድስት ዓመት በሚደርስ ጊዜ በማንኛውም የፋይናንስ ተቋም እንዳይሠሩ ውሳኔ ማሳለፉም ይታወሳል፡፡