ሔለን ተስፋዬ

September 8, 2024

በአዲስ አበባ የገበያ ሥፍራዎች በአዘቦት ቀንም ቢሆን የሸማቾች ትርምስ፣ ጫጫታና ግፊያ አያጣቸውም፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በመገናኛ አካባቢ የሚገኘውና በተለምዶ ‹‹ሾላ ገበያ›› በመባል የሚታወቀው የገበያ ሥፍራ ተጠቃሽ ነው፡፡ በበዓል መዳረሻ ወቅት ይቅርና በአዘቦት ቀንም ቢሆን በሰው ግፊያ የሚጨናነቀው ሾላ ገበያ፣ በአዲሱ የ2017 ዓ.ም. የዘመን መቀበያ ዋዜማ ወትሮ በሚታወቅበት የገበያ ድባብና የሸማቾች ትርምስ ቀዝቅዞ ይስተዋላል። የሚደረገው ሽርጉድ እምብዛም መሆኑን ሪፖርተር ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ ሪፖርተር የዘመን መለወጫ በዓል የገበያ ሁኔታን ለመቃኘት በሾላ ገበያ በተገኘበት ወቅት ያስተዋለው የተቀዛቀዘ የገበያ ድባብን ሲሆን፣ በሥፍራው ያነጋገራቸው ነጋዴዎችም ይህንኑ ዕውነታ ያረጋግጣሉ።

በዋጋ መወደድ ገዥ የራቃቸው የዓውደ ዓመት ገበያዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የበርበሬ ነጋዴ የሆኑት አቶ ይሁኔ ተስፋ፣ እንደቀደሙት ዓመታት ቢሆን፣ በበዓላት መዳረሻ ቀናት ሾላ ገበያ ሸማቾች የሚጎርፉበት እንደነበር፣ በዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ የሚታየው የገበያ ድባብ ግን ቀዝቀዝ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

‹‹ሾላ ገበያ ለወትሮውም ቢሆን ገዥ አይጠፋበትም፤›› የሚሉት አቶ ይሁኔ፣ ዘንድሮ በርበሬ ገዥ ባይኖርም እንኳን ቅመማ ቅመም ለመግዛት የሚጎርፈው ደንበኛ እንደቀነሰባቸው አስረድተዋል፡፡ 

በገበያው አንደኛ ደረጃ በርበሬ ከ450 እስከ 480 ብር በኪሎ ሲሸጥ፣ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከ420 እስከ 380 ብር ድረስ እንደሚሸጥ አቶ ይሁኔ ነግረውናል፡፡ ከ2016 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በኪሎ 380 ብር ድረስ በርበሬ መሸጡን፣ ካለው የአቅርቦትና ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ ዋጋው ከፍ ማለቱን ይገልጻሉ፡፡

እንደ ወግ ባህሉ በዓል ሲቀርብ ለቅቤ መዓዛ፣ ለዶሮ ወጥ ልዩ ሽታን ከሚያጎናጽፉ ቅመማ ቅመሞች መካከል ኮረሪማ በዘንድሮው አዲስ ዓመት ዋዜማ በኪሎ እስከ 1,200 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዋዜማው ኮረሪማ ከ400 እስከ 1,200 ብር በተለያዩ የገበያ ማዕከላት እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ይህ የቅመም ዓይነት በ2013 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓል በኪሎ ከ160 እስከ 170 ብር በተሸጠበት ወቅት ‹‹ተወዷል፣ ኑሮ ወዴት እየሄደ ነው?›› ተብሎ ነበር።

የባሰ አታምጣ እንደሚባለው የሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች የዋጋ ልዩነት አይቀመስ አድርጎታል፡፡ 

በ2013 ዘመን መለወጫ በዓል ወቅት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 40 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ ከ90 ብር እስከ 120 ብር፣ በርበሬ በኪሎ 250 ብርና ቅቤ በየደረጃው ከ420 እስከ 450 ድረስ መሸጡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ 

ይህንን ለመግዛት ሾላ ገበያ ብቅ ያሉ ባልቴቶችን ያስደነገጠ የዋጋ ጭማሪ ካመጡ ቅመማ ቅመሞች መካከል ኮረሪማ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት በኪሎ 350 ብር ተሸጧል፡፡

የሁለቱ ተመሳሳይ ወቅት ልዩነት ሲታይ የ850 ብር ጭማሪ ወይም ብልጫ አሳይቷል፡፡ ለወትሮው ቢሆን በአቅማቸው ዘንቢላቸውን ለመሙላት የሚርመሰመሱ ባልቴቶች፣ ከፍተኛ ገንዘብ ይዘው ወደ ገበያ ቢወጡም በዋጋ ንረቱ ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ ዘንቢላቸውን መሙላት ሳይችሉ፣ ጥቂት ሸምተው ለመግባት መገደባቸውን ነግረውናል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከሚጠቀሱ የገበያ ቦታዎች መሪ ገበያ ይገኝበታል፡፡ ለዚሁ ገበያ የኮረሪማ ዋጋ ከሾላ ገበያ ጋር የተቀራረበ ሲሆን በኪሎ 1,300 ብርና ከዚያ አነስ ያለ ዋጋም ይጠራበታል።

በሁለቱም የገበያ ማዕከላት ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች የዜጎች የመግዛት አቅም ከቀን ወደ ቀን መቀነሱን ጠቁመው፣ ከበዓል ቀደም ብሎ ለሸመታ የሚመጡት የሚሸምቱት መጠን በእጅጉ መቀነሱን ይጠቅሳሉ፡፡    

በሾላ ገበያ የፈረንጅ፣ ድቅልና የሐበሻ ዶሮ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ የፈረንጅ ከ350 እስከ 500 ብር፣ ድቅል ከ850 እስከ 1,200 እና የሐበሻ ዶሮ ደግሞ 550 እና ከዚያ በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተመልክተናል፡፡ 

የዶሮ ገበያው በሁለቱም ገበያዎች የሰዎች የመግዛት እንቅስቃሴ እምብዛም እንደነበር ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ የተመለከተ ሲሆን፣ ነጋዴዎች እንደተናገሩት ከሆነ በዓሉ አንድና ሁለት ቀን ሲቀረው ሸማቾች እንደሚጎርፉ ጠቁመዋል፡፡ 

የሐበሻ ዕንቁላል 12 ብር፣ የፈረንጅ ደግሞ 10 ብር ነጋዴዎች እየሸጡ እንደሚገኙ፣ ለጋ ቅቤ በኪሎ 850 መካከለኛ 800 ብር፣ እንዲሁም የበሰለ 750 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ 

ሽንኩርት በኪሎ እንደ ገበያ ማዕከላቱ የሚለያይ ሲሆን፣ በሾላ ገበያ በኪሎ ከ95 እስከ 105 ብር እንደ ጥራቱ ሲሸጥ፣ በመሪ ገበያ ደግሞ በኪሎ 100 እስከ 110 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተመልክተናል፡፡  

ከእነዚህ የገበያ ቦታዎች በተጨማሪ በየአካባቢው በድንኳኖች የተዘረጉ ገበያዎች በአንፃራዊ ከሌሎች ገበያዎች እንደሚቀንሱ ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡  

ለአብነትም ካዛንቺስ በሚገኘው አነስተኛ የሽያጭ ድንኳኖች ሽንኩርት 80 ብር በኪሎ፣ ነጭ ሽንኩርት 250 ብርና ከዚያ በታች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በእነዚህ የሽያጭ ቦታዎች ከቋሚ ገበያዎች አንፃር ከ50 ብር እስከ 100 የሚደርስ የሸቀጦች ዋጋ በቅናሽ ይቀርባሉ፡፡ 

ከላይ በተዘረዘሩት የገበያ ማዕከላት ባለአምስት ሌትር ኦማር ዘይት 1,150 ብር፣ ፎር ኦል የተሰኘው ዘይት 950 ብር የሚሸጡ ሲሆኑ፣ በሚሊኒየም አዳራሽና በኤግዚቢሽን ማዕከል ባለአምስት ሌትር ኦማር ዘይት 1,100 ብርና ሌሎች የምግብ ዘይቶች ከዚያ በታች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ 

በዓሉ ሲቃረብ የተለያዩ ምርቶችን በአንድ ቦታ ይዘው ብቅ የሚሉት የኤግዚቢሽን ማዕከላት ናቸው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የአገር ልብሶች፣ የቤት ዕቃዎች፣ የምግብ ዘይቶች፣ የተለያዩ ዕቃዎችና ሌሎችም ግብዓቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት አመቺ ይሁን እንጂ በሰዎች ግፊያ ይጨናነቁ የነበሩ ባዛሮች እምብዛም እንደነበሩ ተመልክተናል፡፡

እነዚህ ማዕከላት ከዚህ ቀደም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ገብተው ይገበያዩባቸው የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ግን አነስተኛ ገቢ ያላቸው እየሸሹ ጥሩ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚገበያዩበት እየሆነ መምጣቱን ታዝበናል፡፡

በእነዚህ ማዕከላት ቅናሽ የታየው ባለ አምስት ሌትር ኦማር ዘይት ሲሆን፣ 1,100 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ለአብነትም ከሾላና ከመሪ ገበያዎች ጋር ሲነፃፀር የ50 ብር ቅናሽ እንዳለው ለመታዘብ ችለናል፡፡  

በእነዚህ ባዛሮች ያነጋገርናቸው ሸማቾች እንደሚሉት፣ በባዛሩ ለሽያጭ የቀረቡ ሸቀጦችን ከመግዛት ይልቅ መሸት ሲል የሚመጡ ድምፃውያንን ለመስማት እንደሚገቡ ይናገራሉ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሸማቾች እንደተናገሩት፣ ባዛር የገቡት ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት ግብዓቶችን ለመግዛት ቢሆንም፣ ቦርሳና ምሳ ዕቃ ዋጋው እንደማይቀመስ ተናግረዋል፡፡ 50 ገጽ የሚገዛው ደብተር ደርዘኑ  600 ብርና ከዚያ በላይ መሆኑን፣ ይህም ከሾላና ከመርካቶ ጋር ሲነፃፀር ከ50 እስከ 100 ብር ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ 

በሁለቱም ባዛሮች የተማሪዎች ደብተር 12ቱ ከ600 እስከ 700 ብር እንደ ደብሮቹ ስያሜ የሚለያይ ሲሆን፣ ቦርሳዎች ከ1,200 እስከ 3,000 እና ከዚያ በላይ፣ ምሳ ዕቃ ደግሞ ከ1,200 እና ከዚያ በላይ እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ 

በመርካቶ ገበያና በሾላ ገበያ የተማሪዎች ምሳ ዕቃ እንደ ጥራትና የምርት ዓይነት ከ700 እስከ 1,800 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ቦርሳዎች ደግሞ 1,200 እና ከዚያ በላይ ዋጋ ለገበያ ቀርበዋል፡፡

በእነዚህ ቦታዎች የመገበያያ ቅናሻቸው ከ50 ብር እስከ 100 ብር ሲሆን፣ ለአብነትም 50 ገጽ ሲነር ላይንና ባለድርብ ሽፋን ደርዘን ደብተር 500 ብር መርካቶ ሲሸጥ ባዛር ላይ 600 ብር፣ ሾላ ገበያ 550 እየተሸጠ እንደሚገኝ ተመልክተናል፡፡