የተሽከርካሪ አደጋ በናይጄሪያ

ከ 4 ሰአት በፊት

በናይጄሪያ ማዕከላዊ ግዛት ኒጀር አንድ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ሰዎች እና የቁም እንስሳትን ከጫነ መኪና ጋር ተጋጭቶ ቢያንስ 48 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በሁለቱ መኪኖች ግጭት የተነሳው ከባድ ቃጠሎ ለሰዎች እና እንስሳት ሞት ምክንያት መሆኑን የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል።

ኤጀንሲው ይህ አደጋ ያጋጠመው ትላንት ዕሁድ እንደነበር ገልጾ ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ሲጋጩ ከፍተኛ ፍንዳታ ተከስቶ እንደነበር ጠቅሷል። በዚህም ሳቢያ ተሽከርካሪዎቹ ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን አመልክቷል።

የናይጄሪያ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክትር ጄነራል አቡዱላሂ ባባአራህ ክስተቱ ወዳጋጠመበት ስፍራ የአደጋ መከላከል ሠራተኞች ቡድን እንደተላከ ተናግረዋል።

ሌሎች በርካታ ተሽከርካሪዎችም በአደጋው ምክንያት በተፈጠረው ፍንዳታ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

አደጋው ከተከሰተ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በማኀበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ቪዲዮዎች የተጋጩት ሁለት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወድመው አስመልክተዋል። በተጨማሪም በእሳት ተቃጥለው የሞቱ እንስሳትም ይታያሉ።

ሮይትርስ ያነጋገረው አንድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የሞቱ ሰዎችን አስክሬን እያወጡ እንደሆነ ተናግሯል። ጨምሮ እስካሁን ያልወጡ የሞቱ እንስሳትን ከተሽከርካሪዎች የማውጣቱ ሥራ እንደቀጠለ ገልጿል።

የሞቱ ሰዎች በጅምላ መቃብር ውስጥ መቀበራቸውን የናይጄሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያ ዘግቧል።

በናይጄሪያ የኒጀር ገዢ ኡማር ባጎ በዚህ ክስተት ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸው በአደጋው ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ቤተሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

በናይጄሪያ በተለይም በመንገድ ችግር ምክንያት የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ፍናዳታ እና የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው።