ማኅበራዊ ትስስር

ከ 5 ሰአት በፊት

አኪላ ሻኪህ በ19 ዓመቷ ልጅ ከወለደች በኋላ ሰዎችን የመንከባከብ ሙያ ውስጥ ገባች። በየቤቱ ለሰዎች እንክብካቤ መስጠት “ለኔ የተሰጠ ሙያ እንደሆነ አወቅኩ” ትላለች።

ሥራው ግን አድካሚ ነው። ሕሙማንን ማንቀሳቀስ፣ አልጋ መግፋት፣ ቀኑን ሙሉ መቆም ይጠይቃል።

ጀርባዋን መታመም የጀመረችው በሥራዋ ምክንያት ነው።

ሕመሙ ሲበረታባት የሐኪሞችን ምክር ሰምታ ሥራውን አቆመች።

ሆኖም እረፍት ማድረጓ ሕመሟን አላስታገሰም። ከአልጋ መውረድ የማትችልበት ደረጃ ደረሰች።

“በጣም የሚያስጠላ ስሜት ነው። እኔም የማስጠላ ሰው ሆንኩ” ትላለች።

መንከባከብን እንደ ሙያዋ ይዛ ቆይታ ለሷ እንክብካቤ ሲደረግላት ማየት አላስደሰታትም።

ባለቤቷና ልጆቿ ሐኪም ሲጠሩ የበለጠ ተበሳጨች።

እናቷና አማቷ በተመሳሳይ ወቅት ታመሙ። እነሱን መንከባከብ አለመቻሏ የበለጠ ይጎዳት ጀመር።

“ምንም የቀረኝ ነገር የለም። ከዚህ በኋላ መቀጠል አልችልም። ሁሉንም ነገር ሰው እንዲያደርግልኝ አልፈልግም” ብላ ማሰብ ጀመረች። ራሷን ስለማጥፋትም ታስብ ነበር።

እናቷ በጠና ሲታመሙ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት ጀመረች።

“እናቴ በጣም ብዙ ትሠራ ነበር። በጣም እስክትታመም ድረስ ማንንም አትሰማም ነበር። እኔም ልክ እንደ እናቴ እየሆንኩ መሆኑ ታወቀኝ። ያንን ልጆቼና ባለቤቴ ላይ ማድረጌ ደግሞ ትክክል አይደለም” ትላለች።

አኪላ ለድባቴ የሚሆን መድኃኒት መውሰድ ጀመረች። ባለሙያ ታማክርም ጀመር። ሁለቱም ግን ለውጥ አላሳዩም።

አንድ ነርስ ‘ማኅበራዊ ትስስር’ የሚል ካርድ ስትሰጣት ሁሉም ነገር ተለወጠ።

ወደ ጆአን ጋቪን ደወለች። በዩኬ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ናት።

‘ችግርሽ ምንድን ነው?’ ብለው አይጠይቁም። የበጎ ፈቃደኞቹ ጥያቄ ‘በሕይወትሽ ዋጋ የምትሰጪው ምንድን ነው?’ የሚለው ነው።

ምላሹን ተከትለው ለእያንዳንዱ ሰው የሚሆን ማኅበራዊ ክንውን ያዘጋጃሉ።

አንዳንዶች ከተፈጥሮ ጋር መሆን ሕመማቸውን ያስታግስላቸዋል። ሌሎች በሥነ ጥበብ ይታከማሉ።

አኪላ የሚያስደስታት ሰዎችን መንከባከብ እንደሆነ ጆአን አወቀች።

በ2018 ቦልተን ውስጥ የሚገኝ ሆስፒታል ጆአን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንድትሰጥ ጠይቋት ነበር።

ሥራዋ ሕሙማን የሚናገሩትን አዳምጦ ዋጋ ወደሚሰጡት ነገር ፊታቸውን እንዲያዞሩ ማስቻል ነው።

በእንግሊዘኛው social prescribing የሚባለው ይህ ሐሳብ አዲስ ነው።

“የሰዎችን ታሪክ እሰማለሁ። ድባቴ ወይም ጭንቀት ውስጥ ሳይገቡ በፊት ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ ለመረዳት እሞክራለሁ። ከዚያ ወደዛ ስሜት የሚመለሱበትን መንገድ መፈለግ ነው” ትላለች ጆአን

ሕሙማን ማኅበረሰባዊ ትስስር እንዲፈጥሩ በማስቻል፣ የሚወዱትን ነገር እንዲያደርጉ ዕድል በመስጠት የሚከናወን ሕክምና ነው።

ሳይንስም ይደግፈዋል።

የሥነ ጥበብ ትምህርት፣ ሳይክል መንዳት፣ ምግብ መሥራትና ሌሎችም ክንውኖችን በውስጡ ይዟል።

ማኅበራዊ ትስስር

በአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከሚደረግላቸው እንክብካቤ ባሻገር እነሱም ከራሳቸው ውጪ ለሌላ ነገር እንክብካቤ ሲያደርጉ የተሻለ ጤና እንደሚያገኙ ጥናት ይጠቁማል።

ለምሳሌ አትክልት ሊያሳድጉ ይችላሉ።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ኤለን ላንገር “ሰዎችን መርዳት እርዳታ ለሚሰጠው ሰው ያስደስታል። እርዳታ የሚሰጠው ሰው ግን የጎደለው ነገር እንዳለ ሊሰማው ይችላል” ትላለች።

ማኅበራዊ ትስስር

እንስሳትን መንከባከብ ጤናን እንደሚያሻሽል የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ።

ሰዎች በየዕለቱ የሚከተሉት መርሀ ግብር ሲኖራቸው፣ ለሕይወታቸው ትርጉም ሲያገኙ፣ በአወንታዊ ነገሮች ሲከበቡ፣ በአቅራቢያቸው ሰዎች ሲኖሩና በስሜት የሚደግፋቸው ሲበዛ የተሻለ ጤና ያገኛሉ።

እንስሳት እና አትክልት ከመንከባከብ በተጨማሪ በበጎ ፈቃደኛነት ሌሎችን መርዳትም ሕይወትን የተሻለ ያደርጋል።

ድባቴ እና ጭንቀትን ይቀንሳል።

በ2019 ላይ በ7,000 አሜሪካውያን አዛውንቶች የተሠራ ጥናት በሕይወት ትርጉም ያላቸው ሰዎች ከሌላቸው ሰዎች የላቀ ዕድሜ እንደሚኖሩ ይጠቁማል።

በስቶኒ ብሩክ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምረው ፕ/ር ስቴፈን ፖስት እንደሚለው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከግል ችግሮች ለመራቅ ያግዛል።

“ብዙ ውስጣዊ ጥቅሞች አሉት። ደስተኛ ያደርጋል። ያረጋጋል። ያጠነክራል” ይላል።

በ2017 የተሠራ ጥናት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ሕመምና ድባቴን ማስታገስ እንደቻሉ ያሳያል።

በ2002 የተሠራ ሌላ ጥናት ሕመሙ ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚንከባከቡ ሰዎች ከራሳቸው ሕይወት እንዳገገሙ ጠቁሟል።

“ሰዎች ትርጉም የሚሰጣቸው ማኅበራዊ ትስስር መፍጠር ለውጥ እንደሚያመጣ አያምኑም” ሲል ፕ/ር ስቴፈን ይናገራል።

ከባድ ሕመም ውስጥ ያሉ ሰዎች የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ይወስዳሉ። ግን ለዘለቄታው ሕመምን አይገታም።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሕመም አካላዊ ብቻ አለመሆኑ ነው።

በ1990ዎቹ ጆን ሳርኖ የተባለ ሐኪም ሕመም አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊም ጭምር እንደሆነ ገልጿል።

ይህም ስለ ሕመም ያለውን አስተሳሰብ ገልጿል።

አንዳንዴ ሰዎች እረፍት ላይ ሆነው ሥራ ላይ ሳሉ ከሚሰማቸው የበለጠ ይደክማቸዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሥራ ተወጥረው ሳይሰማቸው የቀረ ድካም ሰውነታቸው ሲያርፍ ተጠራቅሞ ስለሚጫናቸው እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ

አኪላ ከሥራ እረፍት ስትወስድ የበለጠ የታመመችውም ለዚህ ነው።

ማኅበራዊ ትስስር

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ሬቸል ዞፍነስ እንደምትለው ሕመም አካላዊና ሥነ ልቦናዊም ነው።

መጥፎ ስሜት ውስጥ ስንሆን አካላዊ ሕመም የሚበረታብንም በዚህ ምክንያት መሆኑን ታስረዳለች።

ስንናደድ ወይም ስናዝን ሕመም ይበረታል። ሌላ ነገር ላይ ሳናተኩር ስንቀር አካላዊ ሕመም የበለጠ ይሰማናል።

ሬቸል ለዚህ መድኃኒቱ ሕመምን የሚቀንሱ መንገዶች መከተል ነው ትላለች።

ታካሚዎቿን ‘ሌላ አገር ሆናችሁ ሕመማችሁን የረሳችሁበትን ጊዜ እስኪ ንገሩኝ?’ ብላ ትጠይቃለች።

ጆአን ይህንን ጥያቄ አኪላን ጠይቃታለች።

አኪላ ሥራ ማቆሟ ሕመሟን እንዳበረታው አውቃለች።

“የሚያነሳሳት ነገር ስላልነበረ የበለጠ ታመመች” ትላለች።

ለሕጻናት እንክብካቤ የሚሰጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በበጎ ፈቃደኛነት እንድትቀጠር አደረገች።

ጀርባዋን ያሳመማት ዓይነት የሥራ ጫና ሳይኖር፣ በሕይወት ትርጉም የሚሰጣትን ሰዎችን የመንከባከብ ሥራ አገኘች።

አሁን በድርጅቱ ውስጥ ቋሚ ሠራተኛ ሆናለች። ልጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ታስተዛዝናለች። ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ወላጆች የሚያስፈልጋቸውን ታቀርባለች።

አሁን ራሷን እንደሆነች ይሰማታል።

ከቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ጋር ዳግመኛ መተሳሰር ችላለች።

የጀርባ ሕመሟ እንዳለ ቢሆንም “የሕይወት አካል ነው” ብላ ተቀብላዋለች።

ፅኑ ሕመም ውስጥ ወይም ድባቴ ውስጥ ያሉ በሙሉ በበጎ ፈቃድ ሥራ ይድናሉ ማለት አይደለም።

ለአኪላ ግን ከመድኃኒት በተሻለ ሠርቶላታል። የሷን ታሪክ በመስማት ሌሎችም በሕይወታቸው ለውጥ እንደሚያዩ ተስፋ ታደርጋለች።

“ከዚ በኋላ ምንም ማድረግ አትችሉም ብለው ሰዎች ያስቡ ይሆናል። ግን መዳን ይቻላል። ከኔ ተማሩ። ራሴን ለማጥፋት ከማሰብ ጤናማ ሕይወት ወደመምራት ተሻግሬያለሁ” ትላለች።