አፖሎ ኩይቦሎይ

ከ 3 ሰአት በፊት

ሕጻናትን ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር በፊሊፒንስ እና በአሜሪካ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ተፅዕኖ ፈጣሪው ፓስተር በቁጥጥር ስር ዋለ።

ፖሊስ እራሱን ‘የእግዚአብሔር ልጅ’ እያለ የሚገልጸውን ፊሊፒንሳዊውን አፖሎ ኩይቦሎይን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚሰብክበትን ቤተክርስቲያን ለሁለት ሳምንት ያህል ከቦ ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት በሺዎች በሚቆጠሩ ተከታዮቹ እና በፖሊስ መካከል ውጥረት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን አንድ የቤተክርስቲያኑ አባል በልብ ድካም ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

ሰባት ሚሊዮን ተከታዮች እንዳሉት የሚገልጸው ኩይቦሎይ የቀረቡበትን ሁሉንም ክሶች አጣጥሏል።

ኩይቦሎይን ሕጻናትን በወሲብ ንግድ ዝውውር፣ በማጭበርበር እና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ክስ የቀረበበት እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ነበር።

የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) እንዳለው ፓስተሩ ልጃገረዶችን እና ሴቶች ለገንዘብ ማስገኛ ከፊሊፒንስ ወደ አሜሪካ አዘዋውሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ሴት ረዳቶቹን ከእርሱ ጋር ወሲብ እንዲፈፅሙ መጠየቁን ኤፍቢአይ ገልጿል።

ይህ ሁሉ የሆነው ኩይቦሎይ የቀድሞው የፊሊፒንስ መሪ ሮድሪጎ ዱቴርቴ መንፈሳዊ አማካሪ መሆኑን ተከትሎ እውቅናው እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።

ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 2022 ዱተርቴ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ፓስተሩ የነበረው ዝና ተለውጧል።

በቅርቡ የፊሊፒንስ ባለሥልጣናት በሕጻናት ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ ያቀረበቡበት ሲሆን እንዲታሰር የእስር ማዘዣ አውጥተውበት ነበር።

ኩቦሎይን ለመያዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች በዳቫኦ የሚገኘውን 30 ሔክታር ስፋት ያለውን ቤተክርስቲያኑን ለሁለት ሳምንት ያህል ከብበው ቆይተዋል።

ፖሊሶች ፓስተሩ ለሁለት ሳምንት ያህል ምድር ቤት ውስጥ ተደብቆ እንደነበር በደኅንነት መሳሪያ መለየቱን አስታውቀዋል።

ቅጥር ግቢው ውስጥ ቤተክርስቲያንና ትምህርት ቤትን ጨምሮ 40 ሕንጻዎች አሉት።

የኩይቦሎይ ጠበቃ እንዳሉት ፖስተሩን ለመያዝ ፖሊስ ለሁለት ሳምንት ያደረገው ከበባ ግቢውን [ኬኢጂሲ] ወደ የፖሊስ ሰፈር ለውጦት ነበር በማለት በተፈጠረው ውጥረትም አንድ አማኝ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የብሔራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጂን ፋጃርዶ፣ እሑድ ዕለት ኩይቦሎይ በሰላም እጁን እንዲሰጥ የተሰጠውን የ24 ሰዓት ጊዜ ተከትሎ በሰላም እጁን መስጠቱን ተናግረዋል።

ሆኖም ጠበቃቸው እስራኤሊቶ ቶሬን ደንበኛቸው እጁን የሰጠው አላስፈላጊ ግጭትን ለማስቀረት እንደሆነ ገልጸዋል።

ኩይቦሎይ ከመታሰሩ በፊት ‘ሰይጣን ሕጋዊ ሥራቸውን እየተፈታተነ’ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።በጉዳዩ ላይ ኤፍቢአይ እንዳይገባም ገልጾ ነበር።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ቀደም ሲል በሕጻናት የወሲብ ንግድ፣ በማጭበርበር እና በጅምላ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ኩይቦሎይ ላይ ክስ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ዱቴርቴ ሥልጣናቸውን ለአሁኑ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ከማስረከባቸው ከጥቂት ወራት በፊት እንዲታሰር ይፈልግ ነበር። ሆኖም ባለሥልጣናት ፓስተሩን የመከታተል ሥራ የጀመሩት በማርኮስ የሥልጣን ዘመን ነበር።