ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ከ 4 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትኛውም አገር “ኢትዮጵያን መድፈር ሲፈልግ አንዴ ሳይሆን አስር ጊዜ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ጳጉሜ 3/2016 ዓ.ም. በተከበረው “የሉዓላዊነት ቀን” ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላም እና መረጋጋት መሆኑን ገልጸው፣ ይህን አልፈው የሚመጡ ኃይሎችን ግን አገራቸው እንደምትከላከል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው ንግግራቸው “በሩቅም በቅርብም ያሉ፤ በቅጡ ያልተረዱን ዛሬ እንዲገነዘቡ የምፈልገው . . . የሚነካንን እንደልማዳችን አሳፍረን እንመልሳለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሊፈጽም የሚችል አገርን በስም ባይጠቅሱም ይህ ንግግራቸው የተሰማው በቅርቡ ሶማሊያ እና ግብጽ የደረሱትን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ካይሮ ጦሯን ሞቃዲሾ አስገብታ በቀጠናው ውጥረት ካየለ በኋላ ነው።

በተመሳሳይ ከዚህ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ከኢትዮጵያ “ታሪካዊ ጠላት ጋር” በመሆን በቀጠናው ያልተገባ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኤታማዦር ሹሙ በአንድ የመጸሐፍ ምረቃ ሥነ – ስርዓት ላይ “ግብጽ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ናት” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከ9 ወራት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የባሕር በር ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በቀጠናው ውጥረት ተፈጥሯል።

ሶማሊያ ይህ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል አዲስ አጋር ፍለጋ ፊቷን ወደ ካይሮ አዙራለች።

ይህን ተከትሎ ሞቃዲሾ እና ካይሮ ወታደራዊ ስምምነት ደርሰው ግብጽ ጦር ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ ልካለች። ከዚህ በተጨማሪ ግብጽ ለሰላም ማስከበር ሥራ ጦሯን በሶማሊያ ለማሰማራት ያቀረበችው ጥያቄ በአፍሪካ ኅብረት እና በሶማሊያ ተቀባይነት አግኝቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታ የኖረችው ግብጽ፤ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የውሃ ድርሻዬን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ “ሁሉንም እርምጃዎች ከመውሰድ ወደ ኋላ አልልም” ስትል ማሳሰቢያ አዘል ደብዳቤ ለፀጥታው ምክር ቤት ልካለች።

ግብጽ ጦሯን ወደ ሶማሊያ የማስገባት እንቅስቃሴ ታዲያ ኢትዮጵያን እና ሶማሊላንድን አላስደሰተም። አዲስ አበባ እና ሐርጌሳ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ባወጡት መግለጫ የካይሮ ጦር ሞቃዲሾ መግባቱ የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።

“በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር አንደራደርም”

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ሚኒስትር ዐቢይ የሉዓላዊነት ቀን ሲከበር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በተገኙበት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የሰውን በመንካት አትታወቅም ካሉ በኋላ፤ “ከሩቅም ከቅርብም [ሊነኩን የሚመጡትን] አሳፍረን መመለስ ተግባራችን፣ ማንነታችን እና መለያችን ነው” ሰሉ ተደምጠዋል።

“ከመጡብን ከማንም ጋር ቢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር አንደራደርም።”

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ “ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከነጻነት፣ ከክብር፣ ልቆ ከመታየት፣ እራስን ለአገር እና ለሕዝብ መወሰዋት ከማድረግ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው” ካሉ በኋላ የአገራቸው ፍላጎት፤ “ሰላም፣ ብልጽግና እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ” መሆኑን ተናግረዋል።

“ወደ ውጪ የምንሄደው፤ ወንድሞቻችን ሲቸግራቸው፤ ሰላም እና የእኛን የሙያ ድጋፍ ሲፈልጉ ብቻ ነው” ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ ባለፉት 6 ዓመታት በየትኛውም ጎረቤት አገር ላይ አንድም ጥይት ተኩሰን አናውቅም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮቿ ሰላም እና መረጋጋት ሲኖራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ብልጽግና መሠረት እንደሆነ እምነት ስላላት “ከማንም ጋር የመጋጨት ፍላጎት እና ሀሳብ የለንም” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።