የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር ጋር በትይዩ

ከ 5 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ርዕዮተ ዓለማዊ ለውጥ የታከለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

ለረዥም ጊዜ የቴሌኮም አግልግሎትን በብቸኝነት ይዞ የቆየው መንግሥታዊው ኢትዮ-ቴሌኮም ተወዳዳሪ መጥቶበታል።

40 በመቶ ድርሻውን ለግል ባለሃብቶች ለመሸጥ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጨረታ ወጥቷል።

መንግሥት ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ይዞ ገበያ ቢወጣም እስካሁን ገዢ አላገኘም።

እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመንግሥታቸው ውሳኔዎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የግል ባለሃብቶች በርከት እንዲሉ ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው።

ዐቢይ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርጓቸው የነበሩት ውሳኔዎች ቀጣይ የሆኑ እና ስር ነቀል የሚባሉ የኢኮኖሚ ለውጦችን በዚህ ዓመት አድርገዋል።

እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ህጎች እና አዋጆች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የተወሰኑት ጸድቀዋል።

ኢኮኖሚው ላይ የተደረጉ ለውጦች ውግዘት እና ውዳሳ እያገኙ ነው። ለመሆኑ የ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አበይት ክስተት ምን ምን ናቸው? ምን አይነት ውጤትስ ያስከትላሉ?

ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል የቅርብ ጊዜው መንግሥት “የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም” ሲል የጠራው የፖሊሲ ለውጥ ነው። በዚህ የፖሊሲ ለውጥ ተግባራዊ ከተካተቱ እርምጃዎች መካከል በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን እና በወለድ ተመን ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ስርዓት ናቸው።

በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን

ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ወደ ትግበራ የገባው “የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም” የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል።

ከዚህ የፖሊሲ ለውጥ ማግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 22፤ 2016 ዓ.ም. የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን አስታውቋል። የፖሊሲ ማሻሻያው ካስተዋወቃቸው ለውጥች መካከል በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን አንደኛው ነው።

ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ሳያግባባት የቆየውን በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ውሳኔ በገበያው ላይ ባለ የግብይት ተመን እንዲወሰን የሚያደርግ ይሆናል።

የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ለውጡ ይፋ በተደረገበት ቀን የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካን ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በ30 በመቶ ቀንሷል። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ የብር የመግዛት አቅም በ57.93 በመቶ ተዳክሟል።

መንግሥት ይህ ውሳኔ፤ “በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን በማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል” ብሎ ነበር።

ማሻሻያውን ተከትሎ በፊት የውጭ ምንዛሪ ተመን ሲወስን የነበረው ብሔራዊ ባንክ ካለፈው ሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ ሚናው “ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ” ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ግዴታ የነበረው የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀሪ ተደርጓል።

መንግሥት ይህ ውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት የወጪ ንግድን ያበረታታል፤ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ያጠናክራል ቢልም ባለሙያዎች ግን ውሳኔውን ሲተቹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባለሙያዎች ያጠኑት ጥናት የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያው፤ የዋጋ ግሽበት እንደሚያስከትል ጠቁመዋል።

ሦስት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በጋራ ባካሄዱት ጥናት መንግሥት እንዳሰበው በአጭር ጊዜ የወጪ ንግድ እንደማይጨምርም አመላክተዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፤ “[ውሳኔው] ብር የመግዛት አቅምን እያዳከመ፤ የዶላርን የመግዛት ዋጋ ከፍ እያደረገው ሲሄድ ድርጅቶችን ይጎዳል። ምክንያቱም የሚያስገቡትን ግብዓት በውጭ ምንዛሪ ስለሚያስመጡ አገር ቤት ገብቶ ከተመረተ በኋላ ለሸማቹ የሚቀርብበት ዋጋ ከፍ ማለቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ የኑሮ ሁኔታውን የበለጠ ያናጋዋል የሚል ፍርሀት አለኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ

በተመሳሳይ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወለድ ተመን ላይ የተመሰረተ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ ማድረጉን ያስታወቀው።

ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያስተዋወቀው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንድ አካል ነው።

ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን ባስተዋወቀበት መግለጫ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ “ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ሲሠራ” መቆየቱን ጠቁሟል።

ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማሸጋጋር ነው።

በአዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ የፖሊሲ አቋሙን ለማሳየት እና የገንዘብ እና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የወለድ ምጣኔ የፖሊሲ ተመን እንደሚጠቀም ተገልጿል።

15 በመቶ እንዲሆን የተወሰነው የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ፤ “እንደ ዋጋ ንረት እና የገንዘብ ሁኔታ እየታየ ከፍ ወይም ዝቅ የሚል” መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

እንደ ኢኮኖሚው ሁኔታ የወለድ ምጣኔ ተመኑ ላይ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው አመላክቶ ነበር።

ይህን የብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ ተመን ባንኮች እርስ በእርስ በሚወዳደሩበት ወቅት እንደ አመላካችነት ይጠቀሙበታል።

የባንክ ለባንክ የወለድ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የ15 በመቶ የፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ጋር የማይጣጣም ከሆነ፤ “ብሔራዊ ባንኩ ሁኔታውን ለማስተካከል ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታን ይጠቀማል” ሲል መግለጫው ያትታል።

ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንቱ እንደሚያወጣ በመግለጫ ላይ ሰፍሯል።

በመግለጫው መሠረት እነዚህ ጨረታዎች የሚደረጉት፤ “ብሔራዊ ባንክ ከወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ከባንክ ስርዓት ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲያስችለው ነው”።

የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መሆን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የኢንቨስትመንት ቦርድ የውጭ ባለሃብቶች በወጪ፣ በገቢ፣ በጅምላ እና ችርቻሮ ንግዶች ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ መመሪያ ያወጣው እየተጠናቀቀ ባለው የ2016 ዓ.ም ነበር።

እነዚህ ዘርፎች በርከት ላሉ ዓመታት ከውጭ ባለሃብቶች ተከልለው ነበር። ነገር ግን ዘርፎቹን ለውጭ ተሳታፊዎች የመዝጋት ፖሊሲ “በተገቢው መጠን የሚፈለገውን ዓላማ አሳክቷል ማለት አይቻልም” ሲል መንግሥት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጡት መግለጫ፤ “ከለላ በተሰጣቸው ዘርፎቹ ሰፊ የአገልግሎት ተደራሽነት፥ የጥራት እና የብቃት ችግሮች አጋጥመዋል” ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፊርማቸው ያጸደቁት መመሪያም በተመሳሳይ፤ “እስካሁን የተመዘገቡ ውስን ውጤቶች ቢኖሩም የፖሊሲው ዓላማ [ግን] በተጠበቀው መጠን” አለመሳካቱን ያትታል።

ይህን ምክንያት በማድረግም ፍቃደኛ ለሆኑ እና አቅም ላላቸው የውጭ አገር ባለሃብቶች ዘርፉን መክፈት እንዳስፈለገ ተገልጿል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያ፤ “መከፈቱ ራሱ የሚባለውን ችግር ለመቅረፉ እርግጠኛ መፍትሔ አይደለም” ይላሉ።

ባለሙያው አክለውም “በኢትዮጵያ የሚታየው ገበያን ለውጭ [ባለሀብት] ክፍት ማድርግ የሁሉም ነገር መፍትሔ ነው የሚል አመለካከት በጣም ችግር ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

“ከዕዳ ወደ ምንዳ”?

ኢትዮጵያ እየተጠናቀቀ በሚገኘው የ2016 ዓ.ም. ዕዳቸውን መክፈል ከማይችሉ አገራት ተርታ ተመድባ ነበር። ከሰባት ወራት በኋላ ደግሞ 13.5 ቢሊዮን ዶላር “በድጋፍ” እና ሌሎች አማራጮች አግኝታለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአስር ዓመታት ገደማ በፊት ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ መክፈል የሚጠበቅባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ መክፈል ነበረባት።

6.625 % ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት ይህ የቦንድ ሽያጭ ዕዳ በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ 2017 ዓ.ም. መከፈል ይኖርበታል።

ዋናው ብድር እስከሚከፈል ባሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓመታዊ ወለድ ለአበዳሪዎቹ ይከፍላል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነው ይህንን የወለድ ክፍያ ኢትዮጵያ እንደማትከፍል አስታውቆ ነበር።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ መክፈል የነበረባትን ወለድ ያልከፈለችው ሁሉንም አበዳሪዎች “በእኩል ለማስተናገድ” በሚል እንጂ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኖሮባት አለመሆኑን ገልጾ ነበር።

ገንዘብ ሚኒስቴር በጊዜው ባወጣው መግለጫ፤ “[ሁሉንም አበዳሪዎች] በፍትሐዊነት ለመመልከት አለመቻል በዕዳ ሽግሽግ ላይ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት አደጋ ላይ ይጥለዋል” ሲል አመላክቷል።

ኢትዮጵያ የብድር እፎይታ ለማግኘት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ውይይት ማካሄድ ከጀመረች ሰነባብታለች።

ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በቻይና እና በፈረንሳይ በሚመራው የፓሪስ ክለብ አማካኝነት የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ደርሳለች።

በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለአበዳሪዎቿ መክፈል የሚጠበቅባትን ብድር እና ወለድ ሁለት ዓመት ገደማ አትከፍልም።

ይህ የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ አገሪቱ በየዓመቱ መክፈል የሚጠበቅባትን 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዕዳ በጊዜያዊነት የሚያስቀር ነው።

ከዚህ የዕዳ ሽግሽግ በተጨማሪ 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ወዳጅ አገራት “በድጋፍ” እና ሌሎች አማራጮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ይህ ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሐምሌ ወር መተግበር ለጀመረችው በገበያ ሥርዓት የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ስርዓት እና ሌሎች ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የሚውል ነው።