አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ስላሴ

9 መስከረም 2024, 12:44 EAT

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰውን “ተደጋጋሚ የኃይል እርምጃ ዛቻ እንዲያጤን” ኢትዮጵያ ጠየቀች።

የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ የተመድን ቻርተር በሚጻረር መልኩ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰች ያለችውን ተደጋጋሚ ዛቻ ምክር ቤቱ እንዲያጤን ጠይቋል።

ቢቢሲ የተመለከተው በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ስላሴ የተጻፈው ደብዳቤ፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ኦፕሬሽንን በተመለከተ ግብጽ እያራመደች ያለችውን ግትር አቋም እና ምክንያታዊ ያልሆነ ጥያቄን በመተው አገሪቱ ለዓለም አቀፍ መርሆች እንድትገዛ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤት የላከው ግብጽ ከቀናት በፊት ለጻፈችው ደብደቤ ምላሽ ለመስጠት ነው።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ባዳረ አብዱላቲ እሁድ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም. ለጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ፤ ግብጽ የውሃ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብት አላት ብለው ነበር።

ሚኒስትሩ በዚሁ ደብዳቤያቸው ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን የተናጠል ፖሊሲ ግብጽ ሙሉ በሙሉ አትቀበልም ካሉ በኋላ፤“ግብጽ ሕልውናዋን ለመከላከል እና የሕዝቦቿን ጥቅም ለማስከበር በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት ሁሉንም እርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ ናት” ብለዋል።

ግብጽ እና ኢትዮጵያ አንዳቸው ሌላኛቸውን በመውቀስ ለጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ የጻፉት የካይሮ ጦር በሞቃዲሾ ተሰማርቶ በቀጠናው ውጥረት ካየለ በኋላ ነው።

በቅርቡ ካይሮ እና ሞቃዲሹ የደረሱትን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ግብጽ በሶማሊያ ወታደሮቿን ማሰማራቷ ይታወሳል።

አምባሳደር ታዬ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም. ለጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ያቀረበችውን ክስ ሙሉ በሙሉ አንቀበለውም ብለዋል።

በዚህ ደብዳቤ ላይ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ውሳኔ በአገራት ሥልጣን ስር የሚወሰን መሆኑን እና የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በሁለትዮሽ ግንኙነት ወይም በቀጠናዊ ድርጅቶች አማካይነት መፍታት እንደሚገባ ኢትዮጵያ አቋሟን አንጸባርቃለች።

“ኢትዮጵያ፤ ማንኛውም የግብጽ የውሃ አጠቃቀም ወይም ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ፍትሐዊ፣ ሕጋዊ እና ተገቢ የአባይ ውሃ ድርሻ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንደሌለው በማያሻማ መልኩ ማረጋገጥ ትፈልጋለች”።

እየተጠናቀቀ ያለው የሕዳሴ ግድብ ባለፉት 13 ዓመታት በግንባታ ላይ መቆየቱ ይታወቃል።
የምስሉ መግለጫ,እየተጠናቀቀ ያለው የሕዳሴ ግድብ ባለፉት 13 ዓመታት በግንባታ ላይ መቆየቱ ይታወቃል።

አምባሳደር ታዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ 2015 ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ባቀኑ ወቅት ከፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ጋር የግድቡን ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን በተመለከተ የሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲደረግ ከስምምነት ደርሰው እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ “ኢትዮጵያ ድርድሩን ለመቀጠል በሙሉ ዝግጅት ላይ የነበረች ቢሆንም፤ ግብጽ ከሦስትዮሽ ድርድሩ እራሷን ማግለሏን ይፋ አደረገች” ብለዋል።

ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድሩን ጥላ መውጣቷ እና ተደጋጋሚ ደብዳቤዎችን ለጸጥታው ምክር ቤት መላኳ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት በሚደረገውን ጥረት ላይ የምትፈጥረው ሌላኛው እንቅፋት ነው ብለዋል።

ግብጽ የአባይ ውሃን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ፤ በቅርቡ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘በየትኛው አገር የሚከናወን የልማት ፕሮጀክት የግብጽን ታሪካዊ የአባይ ወንዝ የውሃ ድርሻ ጥያቄ ውስጥ በማይከት ወይም የውሃ ድርሻ በማይቀንስ ሁኔታ መካሄድ አለበት’ ማለታቸው ግብጽ አሁንም ሌሎች የተፋሰሱ አገራት ያልተካተቱበት ወይም የማይስማሙበት የቅኝ ግዛት ሕግጋቶች የመመራት አቋም እንዳላት ያሳያል ብለዋል አምባሳደር ታዬ ለጸጥታው ምክር ቤት የላኩት ደብዳቤ።

አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ በበኩሏ ሁሉን ሊያግባባ የሚችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ነው በማለት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ወይም በአጠቃላይ የትብብር ሕግ ማዕቀፍ ስር የሦስትዮሽ ድርድሩን ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ ድርድር

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት በሕዳሴ ግንባታ እና ኦፕሬሽን ዙሪያ ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ያለ ስምምነት መበተኑ ይታወሳል።

በግድቡ ዙሪያ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ባላቸው መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት ከስምምነት መድረስ አልቻሉም። ሁለቱ አገራት ለድርድሩ አለመሳካት አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ግንባታው ከተጀመረ 13 ዓመታት ያስቆጠረውን ግዙፍ ግድብን ውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ግብጽ እና ሱዳን ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከአባይ ውሃ ፍትሐዊ የሆነ ድርሻዬን መጠቀም አለብኝ በማለት አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ስታደርግ ቆይታለች።