በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ

9 መስከረም 2024, 16:32 EAT

የአውስትራሊያ ፖሊስ ሕጻን ልጅ ላይ ትኩስ ቡና አፍስሶ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ ለመያዝ ዓለም አቀፍ ክትትል ጀመረ።

የአገሪቱ ፖሊስ እንዳለው በብሪዝበን ከተማ ጥቃቱን ያደረሰው ይህ ግለሰብ ከአገር መውጣቱ በመረጋገጡ ከሌሎች አገራት ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

መላ አውስትራሊያን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ በከተተው ጥቃት፤ ጉዳት የደረሰበት የዘጠኝ ወር ጨቅላ ፊቱ፣ እጆቹ እና እግሮቹ ላይ ከፍተኛ የቃጠሎ ጉዳት ደርሶበታል።

የአውስትራሊያ ፖሊስ የሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እየፈለገው ያለው የ33 ዓመት ግለሰብ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊደርስ የሚችል ቅጣት ይጠብቀዋል።

ይኹን እንጂ የኩዊንስላንድ ፖሊስ በዚህ ወንጀል የሚጠረጠረው ግለሰብ ድርጊቱን ከፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአገር መውጣቱን አረጋግጧል።

ከቤተሰቡ ጋር ምንም አይነት ትውውቅ የሌለው ይህ ግለሰብ፤ በእጁ ይዞ የነበረውን የፔርሙዝ ትኩስ ቡና በህጻኑ ላይ ያፈሰሰበት ቤተሰቡ በአንድ ፓርክ ውስጥ ከወላጆቹ ጋር ሳለ ነበር።

ጥቃቱ እንደተፈጸመ ለታዳጊው አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የተደረገለት ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በርካታ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጎታል። ወላጆቹ እንደሚሉት ልጃቸው በሕይወት ዘመኑ አብሮት የሚኖር ጉዳት ደርሶበታል።

ጥቃት አድራሹ ጨቅላው ላይ ትኩስ ቡና እንዲያፈስ ምን እንዳነሳሳው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የፖሊስ አዛዡ ፖል ዴልተን የጥቃት አድራሹን ማንነት እንዲሁም ወደ የትኛው አገር እንደሸሸ መረጃው እንዳላቸው ተናግረው፣ ይህን ይፋ ማድረግ ምርመራውን ስለሚጎዳ ለሕዝብ ከመግለጽ ተቆጥበናል ብለዋል።

የሕጻኑ ቤተሰቦች ጥቃት አድራሹ ከአገር እንደወጣ መስማታቸው ለልጃቸው ፍትሕ እስኪያገኙ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ስጋታቸው ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በጨቅላው ስም የተከፈተው የጎፈንድ ሚ ገጽ እስካሁን ድረስ ከ100ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ሰብስቧል።