September 9, 2024 – Konjit Sitotaw 

በ12ኛ ክፍል ፈተና ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 5.4 በመቶ ብቻ ናቸው

የዘንድሮውን 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 674,823 ተፈታኞች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች 5.4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ተማሪዎችን ካስፈተኑ ትምህርቶች ቤቶች መካከል 1,363 የሚሆኑት አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን የገለጸው የዚህን አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት፤ ዛሬ ሰኞ ጷጉሜ 4፤ 2016 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። ለ3ተኛ ጊዜ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ የተደረገውን ይህን ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ፤ 8 በመቶ ያህል የሚሆኑት በይነ መረብን ተጠቅመው የተፈተኑ ናቸው።

የዘንድሮውን ሀገር አቀፍ ፈተናውን ለመውሰድ ከተቀመጡት ተማሪዋች መካከል፤ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ነው። ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ፈተናውን ከወሰዱ 321,536 ተማሪዎች መካከል፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 9 በመቶው መሆናቸው ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈተናውን ከወሰዱት 353, 287 ተፈታኞች የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 2 በመቶ ብቻ እንደሆነ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች 1,221 መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የዘንድሮውን ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል1,363 የትምህርት ቤቶች “አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን” የትምህርት ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዛት 3,792 ነው።