September 9, 2024 

“በ1000 ብር ደመወዝ ኑሮን መምራት ዳገት ሆኖብን ለረሀብ ተጋልጠናል” የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ሰራተኞች

እሁድ ጳጉሜ 03 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በ1000 ብር ደሞዝ ኑሮን መቋቋም አቃተን ”  ያሉ የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ሰራተኞች የሚከፈለን ገንዘብ ከቤት ኪራይ የማያልፍ በመሆኑ በረሀብ እየተሰቃየን ነው ብለዋል።

የረከሰ ቤት ፍለጋ ከከተማ ወጣ ያሉ ሰፈሮች በመምረጥ ሶስት አራት ሆነዉ እንደሚከራዩና ጠዋት አንድ ሰአት ለመድረስ ከአስራ ሁለት ሰአት በፊት ተነስተዉ ያውም በባዶ ሆድና በእግር ተጉዘው እንደሚመጡ የሚናገሩት ሰራተኞቹ ” አሁን ግን ኑሮ ጣሪያ በመንካቱ በዚህ መልክ እንኳን መቀጠል አልቻልንም ” ብለዋል።

” ምንም እንኳን የምሳ ድጋፍ ቢደረግልንም በአንድ ከተማ በአንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያለዉ ልዩነት ያሳዝናል ” በማለት በኢንደስትሪ በፓርኩ ውስጥ እንኳን የአከፋፈል ልዩነት መኖሩን ይገልጻሉ።

አንዳንድ ሼዶች የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የትርፍ ሰአት ስራ የሚያመቻቹ ቢሆንም ሌሎች ደግሞ ከአንድ ሽህ ብር ደሞዝ ውጭ ምንም ትርፍ ነገር አይሰጡም።

” በዚህም ኑሮን መግፋት ተራራ ሆኖብናል ለረሃብም ተጋልጠናል” በማለት ያሉበትን የስቃይ ህይወት አስረድተዋል።