By  አማኑኤል ጀንበሩ

 –

09/09/2024

 አገልግሎቱ የበጀት እጥረት ፈተና እንደሆነበትም ጠቅሷል

ሰኞ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የመንግስትና የግል ድርጅት ሰራተኞችን ተሳታፊ የሚያደርገው የጤና መድህን ዘርፍ በበጀት እጥረት ሳቢያ ላለፉት 3 ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑ ገልቷል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እዮብ ገላየ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣አገልግሎቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ የጤና መድህን ዘርፍ ተግባራዊና በስራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ ቢገኝም የበጀት እጥረት ፈተና እንደሆነበት ጠቁሟል፡፡

የመንግስት ፣የግል እንዲሁም በሌላ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞችን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርገው የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት በ 2010 ዓ.ም አገልግሎቱን ለማስጀመር ታቅዶ የዝግጅት ስራዎችን ጨምሮ ወደ ስራ ተገብቶ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው ካፉት 3 ዓመታት ወዲህ ግን የበጀት እጥረት ማነቆ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱን በተያዘው በጀት ዓመት ወይንም በ 2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ የሚጀምርበት ሁኔታ ያለ ሲሆን የከተማ አስተዳድሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ በሚገኙ በሁሉም ክልሎች እንደሚጀመር እና ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ ኢዮብ አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱ ሲጀምር የዘርፉ ተጠቃሚ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚያስመዘግቡት የቤተሰብ ብዛት ልክ ከደመወዛቸው ላይ በሚቆረጥ አመታዊ ክፍያ የህክምና አገልግሎት በማንኛውም ጤና ተቋማት የሚያገኙበት ሁኔታ ይኖራል ነው የተባለው፡፡