September 9, 2024 – DW Amharic 

ቄሌም ወለጋ በደረሰ የመሬት ናዳ የሦስት ልጃገረዶች ሕይወት አለፈ

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ጅማ ሆሮ ወረዳ በተከሰተ የመሬት ናዳ የሦስት ልጃገረዶች ህይወት ሲያልፍ በንብረት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡

በዚሁ በወረዳው ሶስት ቀበሌያት ጳጉሜ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. ዓርብ ሌሊቱን ቤተሰቡ በእንቅልፍ ላይ እያለ በጣለ ከባድ ዝናብ በተለይ ከዞኑ ከተማ ደምቢዶሎ በስተምዕራብ 135 ኪ.ሜ. ግድም ርቀት ላይ በሚገኝ በአንድ አባወራ መኖሪያ ቤት ላይ አፈር ተደርምሶ የቤቱ አባወራ እና እማወራ በህይወት ሲተርፉ የሦስቱን ሴቶች ልጆቻቸውን አስከሬን እንኳ ማውጣት የተቻለው ቅዳሜ ጳጉሜን 02 ቀን 2016 ዓ.ም. በማግስቱ መሆኑን ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

የቄለም ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑራ መሃመድ እንደተናገሩት አደጋው በተከሰተባቸው ሦስት ቀበሌያትየቤት እንስሳትና 20 ሄክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

አደጋው ከተከሰተ በኋላ ከዞን እስከ ወረዳ በተሰጠው ትኩረት ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው በአደጋው የተፈናቀሉትና በንብረታቸው ላይ አደጋ የደረሰውን ወገኖች ለማቋቋም እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።