ከግራ ወደ ቀኝ፡ ዳዊት አብደታ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር)፣ ገዳ ገቢሳ (ዶ/ር)፣ ኬነሳ አያና እና አብዲ ረጋሳ።
የምስሉ መግለጫ,ከግራ ወደ ቀኝ፡ ዳዊት አብደታ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር)፣ ገዳ ገቢሳ (ዶ/ር)፣ ኬነሳ አያና እና አብዲ ረጋሳ።

ከ 5 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ መንግሥት “በህገ ወጥ መንገድ” በእስር ላይ የቆዩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን “ይቅርታ እንዲጠይቅ እና የጉዳት ካሳ እንዲከፍል” ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ጠየቀ።

የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር በኤክስ ገጻቸው መንግሥት “በሕገ-ወጥ መንገድ” ለአራት ዓመታት አስሮ ላቆያቸው ፖለቲከኞች ይቅርታ የሚጠይቅበት እና ካሳ የሚከፍልበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ሰኞ ጷጉሜ 4፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ከእስር የተፈቱት የኦነግ አመራሮች “መታሰር ይቅርና እና በቁጥጥር ስር መዋል አልነበረባቸውም” ብሏል።

ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ክስ ሳይመሰረትባቸው ለአራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት ኦነግ አመራሮች አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ኬነሳ አያና፣ ለሚ ቤኛ። ዶ/ር ገዳ ኦልጅራ፣ ገዳ ገቢሳ እና ዳዊት አብደታ ናቸው።

እነዚህ ከፍተኛ የኦነግ አመራሮች የፖሊስ አባልን በመግደል እንዲሁም ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

እነዚህ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ከእስር እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በእስር ቤት እንዲቆዩ ስለመደረጋቸው ጠበቆቻቸው እና ፓርቲው ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያለ ክስ በእስር የቆዩ የኦነግ ፓርቲ ፖለቲከኞች ከእስር እንዲለቀቁ ሲጠይቁ ነበር።

እነዚህ ሰባት አመራሮች ከእስር የተፈቱት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 30፤ 2016 ዓ.ም ነበር።

ክስ ሳይመሰረትባቸው አራት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በእስር የቆዩት ፖለቲከኞቹ “ቡራዩ ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በዋስ መለቀቃቸውን” የፓርቲው ቃል አቀባይ አስታውቀው ነበር።

ሂውማን ራይትስ ዋች በመግለጫው “መንግሥት ፖለቲከኞቹ ከእስር እንዲፈቱ የተላለፉ በርካታ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን ችላ ብሏል” ሲል ወቅሷል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በጥናቱ የፖለቲከኞቹ መብቶች በመንግሥት ኃላፊዎች “በተደጋጋሚ መጣሳቸውን” ገልጿል።

ተቋሙ ከጠቀሳቸው የመብት ጥሰቶች መካከል፤ ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቆቻቸው ያሉበትን ሳያውቁ “በግዳጅ ተሰውረዋል” የሚለው አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባለስልጣናት ፖለቲከኞቹን በየወቅቱ በጊዜያዊ እና ይፋዊ የእስር ቦታዎች ያዘዋውሯቸው እንደነበር የመብት ድርጅቱ ጠቁሟል።

ፖለቲከኞቹ ያለ መብራት እና ውሃ አቅርቦት በፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ እና ዶሮ እርባታ መጋዘኖች ውስጥ በመታሰራቸው ኬነሳ አያና እና ገዳ አብዲሳ “በእስር ላይ እያሉ ከባድ የጤና ችግር አጋጥሟቸው” እንደነበር መግለጫው አውስቷል።

“ቤተሰቦቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው [ፖለቲከኞቹ] መፈታታቸውን በደስታ ተቀብለዋል” ያለው ተቋሙ፤ “ነገር ግን ለዘፈቀደ እና ለረዥም ጊዜ እስራት የመዳረጋቸው ምክንያት አሁንም ድረስ ሁሉንም ፖለቲከኞች አደጋ ላይ ጥሏል” ሲል አትቷል።

ሂውማን ራይትስ ዋች አክሎም፤ “በሰለማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ሕይወታቸው እና ነጻነታቸው ለአደጋ እንደተጋለጠ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ጉዳዮችን መፍታት አለበት” ሲል አሳስቧል።

አሜሪካን ጨምሮ የኢትዮጵያ አጋሮች “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተቃዋሚዎችን ያለ ክስ ማሰር እንዲያቆሙ ጫና ማድረግ አለባቸው” ሲል ተቋሙ በአጽንኦት ገልጿል።

የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተሯ ላቲሽያ ባደርም በተመሳሳይ “የኢትዮጵያ አጋሮች እየተካሄደ ያለውን ዘፈቀደ እስራት እንዲቆም ግፊት እንዲያደርጉ” ጥያቄ አቅርበዋል።