በናይጄርያ "የተጸለየበት" እየተባሉ የሚሸጡ ውሃዎች የቤተ አምነቱን ሰባኪ ስም ይዘው ይታያሉ

ከ 8 ሰአት በፊት

የናይጄርያ መድሀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን “የተፀለየበት” ተብለው የሚሸጡ እና በናይጄርያዊው የቴሌቪዥን ወንጌል ሰባኪ፤ ጀርማያ ፉፌይን ቤተ እምነት በኩል የሚቀርቡ ምርቶችን ከመግዛት እንዲቆጠቡ ዜጎችን አስጠነቀቀ።

ባለሥልጣኑ “የተፀለየበት ውሃ” እና “የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ” እየተባሉ ታሽገው የሚሸጡ ምርቶች መካን የሆኑ ሴቶች እንዲወልዱ ያደርጋሉ በሚል “በሐሰት” አንደሚሸጡ ገልጿል።

መግለጫው አክሎም ምንም እንኳ የባለስልጣኑ ፈቃድ ባያገኝም ወንጌል ሰባኪው ጀርማያ ፋፌይን የሚመራው ‘ክራይስት ሜርሲላንድ ዴሊቨረንስ ሚኒስትሪ’ ምርቶቹን እየሸጠ እንደሚገኝ ገልጧል።

ቤተ እምነቱ በበኩሉ “ሕግን አክብሮ የሚሰራ” መሆኑን በመግለጽ የተቋሙን መግለጫ “መንፈሳዊ ነገሮችን ባላቸው መንፈሳዊ እምነት” ልክ እንደሚጠቀም ገልጿል።

እሁድ እለት በተጋራ መግለጫ፣ ክራይስት ሜርሲላንድ ዴሊቨረንስ ሚኒስትሪ በናይጄርያ ሕግ መሠረት እንደሚንቀሳቀስ ገልጾ፣ ይህም ያለምንም ጣልቃ ገብነት የእምነት ነጻነትን ይፈቅዳል ብሏል።

የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣኑ ምርቶቹ ላይ ምርመራ የጀመረው ከዜጎች ቅሬታ ከደረሰው በኋላ መሆኑን ገልጿል።

አክሎም ምርቶቹ የቁጥጥር ባለስልጣኑን ፈቃድ ያላገኙ እንዲሁም የጀርማያ ቤተ እምነትም “በምርመራው ላይ ለመተባባር ዳተኛ የሆነበት” መሆኑን አስታውቋል።

ቤተ እምነቱ በዩቲዩብ ያሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዩች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የባለስልጣኑን ክስ ያስተባብላሉ።

አክለውም ቤተ እምነቱ ለባለስልጣኑ በደብዳቤ ምላሽ መስጠቱንም ገልጿል።

ጀርማያ በናይጄርያ የተአምራት እና የፈውስ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ተከታዮቸን አፍርቷል።

ቢሊየነር እንደሆነ የሚናገረው ሰባኪው፣ በቅንጡ አኗኗሩ የተነሳ ትችቶች ይቀርቡበታል።

በናይጄርያ የተጸለየባቸው እየተባሉ የሚሸጡ የተለያዩ ምርቶችን ማግኘት የተለመደ ነው።

ከዚህ ቀደም ቲቢ ጆሽዋ የመፈወስ አቅም አላቸው እየተባሉ የሚሸጡ “የተፀለየበት ውሃ” ነበረው።

የቢቢሲ ምርመራ ዘገባ ቲቢ ጆሽዋ ታምመው ወደ ቤተ እምነቱ ይመጡ የነበሩ ምዕመናን መድሃኒታቸውን እንዲያቋርጡ ያበረታታ እንደነበር ይፋ አድርጓል።

በጎን ግን በምስጢር የተደራጁ የፋርማሲ ባለሙያዎች የታዘዘውን መድሃኒት “ይፈውሳሉ” ከተባሉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና ውሃዎች ጋር በመቀላቀል ለተከታዮቹ ይሰጥ ነበር።