ኽን ዩኒስ

ከ 8 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር ሰብዓዊ ቀጣና ተብሎ በተለየ ስፍራ ላይ በፈጸመው የአየር ጥቃት 40 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ የአየር ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በኽን ዩኒስ በሚገኘው የሐማስ ተዋጊዎች ማዕከል ላይ ነው ብሏል።

በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ግን ሰብዓዊ ቀጣና ተብሎ በተከለለው ስፍራ ተፈናቃዮች ተጠልለው የነበሩበት ድንኳኖች ላይ ሦስት የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።

“40 ሰዎች ተገድለዋል። 60 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። አሁንም ደግሞ ከፍርስራሽ ስር ያልወጡ በርካታ ሰዎች አሉ” ሲሉ አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አል-ማዋሲ የተባለው አካባቢ በአየር ጥቃት ሲመታ ከፍታኛ ፍንዳታ ድምጽ ተሰምቶ ነበር።

ጥቃቱ ከተፈጸመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት የሚኖረው ካሊድ መሐሙድ የተባለ በጎ ፍቃደኛ እርሱ እና ሌሎች ሰዎች ለእርዳታ ወደ ስፍራው ባቀኑ ጊዜ የደረሰው ጉዳት እንዳስደነገጣቸው ተናግሯል።

“ጥቃቶቹ 7 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶችን ፈጥረዋል። ከ20 ያላነሱ ድንኳኖችን አውድመዋል” ሲሉ ካሊድ ተናግሯል።

ቢቢሲ ትክክለኛነታቸውን ያላረጋገጣቸው ምስሎች ሰዎች ፍርስራሽ ስር የተቀበሩ ግለሰቦችን በእጆቻቸው ቆፍረው ለማውጣት ሲጥሩ ይታያል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “አሸባሪው ሐማስ ሰብዓዊ ተብሎ በተከለለው ስፍራ ውስጥ ባቋቋመው ማዘዣ ማዕከል ላይ ነው” ብለዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥንቃቄ ተወስዷል።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት የሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ለመቀነስ ጦሩ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።

የእስራኤል ባለስልጣናት ሐማስ እራሱን ለመከላከል ሰላማዊ ሰዎችን እንደ መሸሸጊያ ይጠቀማሉ ሲሉ ይከሳሉ።

ሐማስ በበኩሉ ተዋጊዎቹ ሰላማዊ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ እንደማይንቀሳቀሱ ይገልጻል።

እስራኤል ጥቅምት 2016 ላይ ወታደራዊ ዘመቻዋን በጋዛ ላይ ከከፈተች በኋላ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ወደ ኽን ዩኒስ አካባቢዎች ሸሽተዋል።

እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን የጀመረችው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል።

ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት 1ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎችን ገድሎ እና 251 ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ከገባ በኋላ እስራኤል የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ስታደርግ ቆይታለች።

በሐማስ የሚመራው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው ከሆነ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ 41ሺህ ሰዎች በእስራኤል ጦር ተገድለዋል።