የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጀነራል ታደሰ
የምስሉ መግለጫ,የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጀነራል ታደሰ ወረደ

ከ 5 ሰአት በፊት

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሹም ሽር እንዳያደርግ ከለከሉ።

ጄነራል ታደሰ ትናንት ማክሰኞ ጳጉሜ 4/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችን “መሾምም ሆነ መሻር ማቆም አለበት” ብለዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጄነራል ታደሰ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት መሾም እና መሻር አይችልም በሚል የመከልከል ስልጣን እንዳላቸው ግልጽ አይደለም።

ጄነራል ታደሰ ይህን መግለጫቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለበርካታ አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህወሓት መሪዎች መካከል ክፍፍል ተፈጥሮ በትግራይ ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።

በአሁኑ ወቅት በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) ፓርቲው ውስጥ በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ሁለት ቡድን ተፈጥሯል።

በአመራሮች መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እና እንዲሁም ፓርቲው በቅርቡ ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው።

እነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በቅርቡ የጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች በጉባኤው ላይ ያልተሳተፉ ከፍተኛ አመራሮችን ወደ ተራ አባልነት ዝቅ አድርጎ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን የፓርቲው ሊቀ መንበር አድርጎ መልሶ ሾሟል።

ይህ ጠቅላላ ጉባኤ እየተደረገ በነበረበት ወቅት ደግሞ በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን “ህወሓትን ማዳን” ያለውን ስብሰባ አደርጎ በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንደማይሆኑ አስታውቆ ነበር።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ የደረሰበት ክልል ገና ሳያገግም በፓርቲው አመራሮች መካከል ልዩነት መፈጠሩ ሌላ የደኅንነት ስጋት ፈጥሯል።

“ልዩነቱ በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ ይፈታ”

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የትግራይ ኃይሎችን ሲመሩ የነበሩት ጄነራል ታደሰ ወረደ ትናንት በሰጡት መግለጫ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ መፈታት ይኖርበታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ጄነራሉ “በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያሉ አመራሮች ስልጣናቸውን ተጠቅመው አንዳንዶችን ከስልጣን የማውረድና አዲስ የመሾም ተግባር እየታየ ነው” ሲሉ በክልሉ ስላለው ሁኔታ አስረድተዋል።

“የኛ [የጸጥታ አካላት] ጥያቄ አስተዳደሩን ለመለወጥ እየተደረገ ያለ መሾምና ማውረድ እንዲቆም ነው” ሲሉ በመግለጫቸው አክለዋል።

ጄነራሉ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹም ሽር ማካሄዱ በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ባሰ ደረጃ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

“ተባብሶ በመቀጥል እየፈነዳ ነው ያለው። ገንፍሎ የሚፈስ የፖለቲካ ቀውስ ነው የሚታየው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን “በጊዜያዊ አስተዳደሩ 50+1 ድርሻ የህወሓት ነው በማለት” ስልጣን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ሙከራም መካረሩን ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ጄነራል ታደሰ የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች ክልሉን እያስተዳደረ ባለው ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ቢፈጠርም የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቦ ነበር።