የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል

ከ 3 ሰአት በፊት

ከአራት ዓመት ገደማ በፊት በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ “በክህደት መንፈስ ጥቃት” ከፍተዋል በሚል እስከ የሞት ቅጣት ድረስ ተላልፎባቸው የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊቱ አባላት በይቅርታ ተለቀቁ።

በእስር ላይ የነበሩት የሠራዊቱ አባላቱ ይቅርታ የተደረገላቸው አዲስ ዓመትን በማስመልከት እንደሆነ የመከላከያ ሠራዊት ዛሬ ጷጉሜ 5/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላቱ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ነበር። በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ የተፈጸመው ጥቃት፤ ቀድሞውኑም የጦርነት ድባብ አጥልቶበት የነበረውን የፌደራል እና የትግራይ ክልል መንግሥታት መካረር ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዲቀየር አድርጓል።

ይህንን ጥቃት ተከትሎ የተከፈተው የእርስ በእርስ ጦርነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. የፕሪቶሪያ ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ ለሁለት ዓመታት ዘልቋል።

የመከላከያ ሠራዊት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች” የሰሜን ዕዝ ላይ “በክህደት መንፈስ ጥቃት መከፈታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ሕገ- መንግሥታዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በሠራዊቱ እና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል” መፈጸማቸውን አስታውሷል።

በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተከስሰው “ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ” በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ጉዳዩን የተመለከተው ወታደራዊ ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ ያሳለፈው ፍርድ እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ እንደሆነ ያስታወሰው መግለጫው፤ ፍርደኞቹ በእስር ቤት ውስጥ መቆየታቸውን ገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊት መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ በእስር ላይ የነበሩት የሠራዊት አባላቱ ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

መግለጫው፤ “በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እስከ ሞት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 178 የሠራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው የይቅርታ ጥያቄያቸውን ለመንግሥት እና ለመከላከያ ሚኒስቴር አስገብተዋል” ሲል ጥያቄው የቀረበላቸውን አካላት ጠቅሷል።

ፍርደኞቹ ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ በ2006 ዓ.ም. በወጣው የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ስርዓት አዋጅ መሰረት እንደታየ መግለጫው አስታውቋል። የሠራዊት አባላቱን የይቅርታ ጥያቄ የተመለከተው ቦርዱ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን “ይቅርታ ማድረግ የሚያሳካቸውን አላማዎች” ከግምት ውስጥ እንዳስገባ ተጠቅሷል።

በመከላከያ ሠራዊት መግለጫ ላይ የተጠቀሰው የአዋጅ ክፍል፤ ምን ዓላማን ለማሳካት ይቅርታ እንደሚደረግ የሚገልጽ ነው። በአዋጁ መሰረት ይቅርታ ከሚደረግባቸው ዓላማዎች መካከል፤ “የሕዝብ፣ የመንግሥት እና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ” የሚለው ይገኝበታል።

ይቅርታው የሚደረገው ግለሰቦቹ፤ “ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ” እንደሆነም በአዋጁ ላይ ተደንግጓል።

አዋጁ እንደሚያስረዳው ለእነዚህ ዓላማዎች ሲባል ይቅርታ የሚሰጠው “መንግሥት የወንጀል ጥፋተኞች በጥፋታቸው የተፀፀቱ እና የታረሙ መሆኑን” ሲያረጋግጥ ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ የይቅርታ ጥያቄውን የተመለከተው ቦርዱ፤ የሠራዊት አባላቱ “በፈፀሙት ወንጀል መፀፀታቸውንም” እንደተመለከተ አስታውቋል።

“የመከላከያ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርዱን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአዲሱ ዓመት በመታረም ላይ የነበሩ 178 የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላት ከዛሬ ጷጉሜ 5/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከእስር በይቅርታ እንዲለቀቁ” መወሰኑን በመግለጫው አስታውቋል።

ይህ ውሳኔ የተላለፈውም፤ “መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ይበልጥ ለማፅናት ቁርጠኛ በመሆኑ” እንደሆነ ተጠቅሷል።