በ 2016 ዓ.ም. ዐበይት የነበሩ ጉዳዮች የሚያሳይ ምስል

ከ 9 ሰአት በፊት

እየተሸኘ ያለው 2016 ዓ.ም. ሲገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በአጭር ፅሁፍ ነበር። ቀደም ባሉት ዓመታት ከ600 ባላነሱ ቃላት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ የነበሩት ዐቢይ፤ በ2016 ሀሳባቸውን በ100 ቃላት በቅቷቸው ታይተዋል።

የዐቢይ መልዕክት አስኳል፤ “በቀጣዩ ዓመት ፈተናዎቻችን እጅግ ቀንሰው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ከአልማዝ ጠንክሮ፤ የኢትዮጵያን ሰላም እና ደህንነት በጽኑ መሠረት ላይ እናጸናዋለን” የሚል ነበር። በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ ያለፈውን ዓመት ክራሞት መለስ ተብሎ ሲቃኝ፤ ሊሸኝ የአንድ ለሊት ዕድሜ የቀረው ይህ ዓመትም አወዛጋቢ ርዕሰ ጉዳዮች ያልታጡበት ነው።

በ2016 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ጎዳናዎች 32 ቢሊዮን ብር በፈሰሰበት የኮሪደር ልማት በኩል በቀለም እና መብራት ቢያሸበርቁም፤ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ውስጥ ቀጥለዋል። ላለፉት ዓመታት የነዋሪዎችን የመኖር እና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ያሳጠው የእገታ ወንጀል በ2016ትም ቀጥሎ፤ ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እስከ የሕዳሴው ግድብ ጫካ መንጣሪዎችን ተጠቂ አድርጓል።

ከጦርነት “አረፍ” ያለው የትግራይ ክልልም በአመራሮቹ መካከል በተፈጠረ ፖለቲካዊ ትኩሳት እየታመሰ ነው።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ፋኖ ታጣቂ ቡድን እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ያደረጉት የተኩስ ልውውጥ እና የታጣቂዎቹ አባላት ሞት የመዲናዋን የጸጥታ ጉዳይ በተመለከተ ድንጋጤን የፈጠረ የዚህ ዓመት አንድ ክስተት ነበር።

በሌላ መልኩ መንግሥት አገሪቱ ውስጥ ላሉ ስር የሰደዱ አለመግባባቶች እንደ መፍትሔ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ለሁለት ዓመት ገደማ የቆየበትን የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቅቆ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ተሸጋግሯል።

ይህ ዓመት አስፈጻሚው የመንግሥት አካል አዲስ ሕግ እና አሰራሮችን በተከታታይ ያስተዋወቀበትም ነበር። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት በይዘታቸው ጠንካራ የሆኑ እና ጉልህ ለውጥ የሚያስከትሉ በርካታ አዋጆችን በዚህ ዓመት ቀርበውለት፤ የተወሰኑትን ለቀጣዩ ዓመት አስተላልፎ አብዛኛዎቹን አጽድቋል።

በዜጎች እንቅስቃሴ እና ንብረት ላይ የሚጣሉ ገደቦችን በተመለከተ የፍርድ ቤቶችን ሚና የሚገድቡ አዋጆችን ያስተናገደው ምክር ቤቱ፤ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አካሄድ “አገር ያፈርሳል” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግርም ተሰምቶበታል።

በርከት ካሉት የ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፖለቲካ ክስተቶች መካከል ዋነኛ ያልናቸውን እንዲህ መርጠናቸዋል፦

በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት የፈጠረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሄ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ሲጨባበጡ
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመበትን ዕለት የገለጹት “የኢትዮጵያ ስብራት ጥገና ቀን” በማለት ነበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በጭምጭምታ ሲሰማ የነበረው የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመጠጋት እና የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት፤ በይፋ የተነገረው በጥቅምት መጀመሪያ በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ነበር። ዐቢይ፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ንግግራቸው፤ ወደብ ማግኘት ለኢትዮጵያ “የህልውና ጉዳይ” እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።

ስለ ቀይ ባሕር ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠበትን ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር የተከታተሉ ተንታኞች ትኩረታቸውን ያደረጉት ኤርትራ ላይ ነበር። ታህሳስ 22/2016 ዓ.ም. የሆነው ግን በብዙዎች ያልተገመተው ነበር።

ኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ለአዲስ አበባ ወደብ እና የጦር ሰፈር የሚያስገኘውን የመግባቢያ ስምምነት የመፈራረማቸው ዜና በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ስለ ጉዳዩ የተነገረ ነገር አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በአዲስ አበባ ያደረጉት ፊርማ፤ ኢትዮጵያ ለጦር ሰፈር እና ለወደብ ግንባታ 20 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የባሕር ጠረፍ ቦታን በሊዝ እንደሚያስገኝላት ተገልጿል።

በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ስለ ስምምነቱ ማብራሪያ የሰጡ የመንግሥት ባለስልጣን ኢትዮጵያ በምላሹ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ እንደምገኝ የሚጠቁም ነበር። ስምምነቱ፤ ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እንደ አገር ቆጥራ እውቅና እንድትሰጥ የሚያደርግ እንደሆነ ሕዝብ ጆሮ የደረሰው የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ በፊርማው ስምምነት ላይ በሶማሊኛ ያደረጉት ንግግር ሲተረጎም ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ከቀናት ዝምታ በኋላ እውቅናን በተመለከተ ስምምነት ላይ የተደረሰው ጉዳዩን “አጢኖ አቋም ለመውሰድ” እንደሆነ አስታውቋል።

በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ወደሚሆን ስምምነት ይቀየራል የተባለው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ፊርማ፤ ዘጠኝ ወራትን ቢያስቆጥርም በይፋ የተገለጸ እድገት አላሳየም። በእነዚህ ወራት ውስጥ እያደገ የመጣው ስምምነቱን ተከትሎ ቀጠናው ላይ የተፈጠረው ውጥረት ነው።

የግዛቷ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት እጅጉን ያስቆጣት ሶማሊያ፤ የኢትዮጵያን እርምጃ የቆጠረችው “የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጥሰት” አድርጋ ነው። በሞቃዲሾ የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደር እና ዲፕሎማቶችን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ያዘዘችው ሶማሊያ፤ ለዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ተቋማት አቤት ብላለች።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ
የምስሉ መግለጫ,ሶማሊያ እና ግብፅ ያደረጉት ወታደራዊ ስምምነት በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል ያለውን ውጥረት ጨምሮታል

የሶማሊያ ቅሬታ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት ምክር ቤቶች እንዲሁም በየምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በአረብ ሊግ ስብሰባዎች ላይ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል። የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወዳጅ የሆችው ቱርክ፤ የአገራቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጠርታ በሁለት ዙር ያደረገቻቸው ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮች እስካሁን ስምምነት ላይ አላደረሱም።

በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሶስተኛ ሀገር ተሳትፎ የታየው በንግግር አመቻቺነት ብቻ አይደለም። ሶማሊያ፤ በህዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ወስጥ ካለችው ግብፅ ጋር ወታደራዊ ትብብር ስምምነት በመፈጸም ካይሮን ወደ ቀጣናው አምጥታለች።

ከሳምንት በፊት ግብፅ የጦር መሳሪያ የጫኑ ሁለት የጦር አውሮፕላኖች ወደ ሶማሊያ የላከች ሲሆን በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካ አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ሲቋቋም ወታደሮቿን ለማሰማራት አቅዳለች።

ከስምምነቱ መፈጸም ጀምሮ በሶማሊያ በኩል ለሚሰነዘሩ ንግግር እና መግለጫዎች እምብዛም ምላሽ ሲሰጥ ያልታየው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የግብፅን ወደ ቀጣናው መምጣት በዝምታ አላለፈውም። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሶማሊያ መንግሥት “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል በጠንካራ ቃላት በተሞላው መግለጫው ከስሷል። “ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ሲልም የኢትዮጵያን አቋም አሳውቋል።

ይህ ዓይነቱ ሀሳብ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኩልም ተሰምቶ ነበር። ኢታማዦር ሹሙ ነሐሴ 10 በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ተሰማርተው የተመለሱ የሠራዊቱን አባላት በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በሶማሊያ አልሸባብን ለመቆጣጠር በተደረገው “ትግል” ያልነበሩ “ወገኖች” በአሁኑ ወቅት “ሞታችንን ከሶማሊያ ጋር ያድርገው እያሉን ነው” ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “ከተሳካላቸው አብረን እናያለን። ቀጠናው ላይ ሌላ ችግር ይዘው እንዳይመጡ እኛ የቀጠናው ባለቤቶች ከማንም በላይ የሚያገባን ስለሆነ ዝም ብለን የምንመለከተው ጉዳይ አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።

በዓመቱ ማጠናቀቂያ ቀናት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የተደረጉ ንግግሮች በቀጣናው የተፈጠረውን ውጥረት ወታደራዊ ገፅታ የሰጡ ናቸው።

ጠመንጃ የታጠቀ ሰው

የ2016ን ዘጠኝ ወራት በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ያሳለፈው አማራ ክልል

“ባሕር ዳር፣ አዴት፣ ደብረማረቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መርዓዊ፣ ቢኮሎ፣ መርጦ ለማርያም፣ ሸዋ ሮቢት እና የዕድውኃ” በ2016 ዓ.ም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጭ ግድያዎችን የተፈጸመባቸው ከተሞች መሆናቸውን ይናገራል፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች (ኢሰመኮ) ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት።

እነዚህ በግጭት አውድ ውስጥ የተፈጸሙ ግድያዎች የተመዘገቡበት የአማራ ክልል፤ 2016ን የጀመረው ባለፈው ዓመት መጨረሻ የገነፈለውን የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ግጭት በማስተናገድ ነበር። ሐምሌ 2015 ዓ.ም. በዋነኛነት በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በጥር ላይ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሞ ነበር።

በዚህም ምክንያት ክልሉ የዓመቱ አብዛኛዎቹን ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር አሳልፏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጣሉን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች “የጅምላ እስር” መፈጸሙን ኢሰመኮ አስታውቋል። ሐምሌ ላይ በተወሰነ መልኩ በተለይም በዋና ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት በድጋሚ እስከሚለቀቅ ድረስም ክልሉ፤ በግንኙነት እቀባ ውስጥ ቆይቷል።

እንደ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልዲያ ባሉ በክልሉ ዋና ከተሞች ውስጥ ጭምር በተደረጉ ተደጋጋሚ የተኩስ ልውውጦች ምክንያት ዓመቱን በሰላም እጦት ያሳለፈው አማራ ክልል፤ ጥቂት የማይባሉ የድሮን ጥቃቶችም ተፈጽመውበታል።

በክልሉ ምዕራብ ጎጃም ዞን በደምበጫ ከተማ እና ቋሪት ወረዳ በመስከረም ወር የተፈጸሙ ሁለት የድሮን ጥቃቶች 40 ገደማ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር። በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው መሀል ሳይንት ወረዳ በህዳር ወር የተፈጸሙ ሁለት የድሮን ጥቃቶች ደግሞ ቢያንስ “ለ30 የአካባቢው ወጣቶች” ሕልፈት ምክንያት እንደሆኑ ነዋሪዎች ገልጸው ነበር።

በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት አውድ ውስጥ ንጹሃን የተገደሉት በድሮን ጥቃት ብቻ አልነበረም። በመርዓዊ እና ጅጋ ባሉ ከተሞች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የፈጸሟቸው ግድያዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ጥር 20/2016 ዓ.ም. በመርዓዊ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመው ከፍርድ ውጪ የሆነ ግድያ “ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎች” እንደተገደሉ ኢሰመኮ አስታውቋል። በዕለቱ ሲቪል ሰዎች የተገደሉት “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል እንደሆነ በሰብዓዊ መብቶች ተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።

የፋኖ ታጣቂዎች

የመርዓዊውን ክስተት ጨምሮ በጥር ወር ብቻ በክልሉ ሰሜን ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ቢያንስ 66 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቆ ነበር።

በክልሉ ባለው ግጭት ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ በመፈጸም የሚከሰሱት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ብቻ አይደሉም። በሐምሌ ወር የፋኖ ታጣቂዎች በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ ውስጥ “ለፖለቲካ ሥራ ባሕር ዳር ከተማ ድረስ በመሄድ ስብሰባ ተሳትፋችኋል” በሚል የሃይማኖት አባት እና የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ አራት ሰዎችን መግደላቸውን ብሔራዊው የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ገልጿል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ያላቸው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፤ በዚህ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሱባቸው ጊዜያት የአማራ ክልልም ጉዳይ ከአጀንዳዎቻቸው መካከል ነበሩ። ይሁንና በክልሉ ያለውን ግጭት ከማስቆም አንጻር ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አልተስተዋለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ወር መንግሥታቸው “በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር ከጀመርን ውሎ ማደሩን” ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ንግግር የተገኘው ውጤትም ሆነ በቀጣይ የነበሩ ሂደቶች እስካሁን ይፋ አልሆኑም። የፋኖ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር አቀራርቦ ሰላም ለማምጣት ሰኔ ላይ የተቋቋመው 15 አባላት ያሉት የሰላም ካውንስል እስካሁን ባለው እንቅስቃሴው ተጠቃሽ የሆነ ውጤት አላስገኘም።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባ

ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የታንዛኒያው ሁለተኛ ዙር ድርድር

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ታጣቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሁለት ሳምንት ገደማ የፈጀውን ረጅም ድርድር ያካሄዱት እየተጠናቀቀ ባለው በዚህ ዓመት ነው፤ ምንም እንኳ ያለ ውጤት ቢጠናቀቅም።

በኦሮሚያ ክልል የወለጋ እና ሸዋ ዞኖች በትጥቅ ትግል መንቀሳቀስ ከጀመረ ከአምስት ዓመት በላይ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንግሥት ጋር ድርድር የተቀመጠው ሚያዝያ 2015 ነበር። የመጀመሪያ ንግግር በዛንዚባር ሙዪኒ የባሕር ዳርቻ በተደረገው የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ቢገኙም ተቃራኒውን ወገን ከወከሉት ስምንት ግለሰቦች ውስጥ የሠራዊቱ አባል የነበሩት ሁለቱ ናቸው። ቀሪዎቹ ስድስት ግለሰቦች ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ልዑካን ነበሩ።

ይህ የመጀመሪያው ድርድር ያለ ስምምነት የተጠናቀቀ ቢሆንም ቀጣይ ንግግር እንደሚኖር ፍንጭ የሰጠ ነበር።

ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ዛንዚባር የተጀመረው ድርድር በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ የቀጠለው በጥቅምት መጨረሻ ነበር። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዦች ከፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ፊት ለፊት በተገናኙበት በዚህ ድርድር የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባ በሶስተኛ ወገን አመቻችነት ከኦሮሚያ ክልል ወጥቶ ታንዛንያ የተገኘበት ነበር።

የመከላከያ ሠራዊት አዛዦችም በተሳተፉበት ይህ ድርድር ከተጀመረ ከቀናት በኋላ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ተቀላቅለውታል።

ድርድሩ ለሁለት ሳምንት ገደማ መቆየቱ፤ በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዦች በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸው “ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል” የሚል ተስፋን ጭሮ ነበር። ንግግሩ መቋጨቱ በተነገረበት ኅዳር 11 ምሽት ከሁለቱም ወገኖች የወጡት መግለጫዎች አንዳቸው ሌላኛው የከሰሱበት እና የቀጣይ ንግግር ፍንጭ ያልታየበት ነው።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
የምስሉ መግለጫ,ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚደረግ ሦስተኛ ድርድር “ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ላለመነገጋር” የሚወሰንበት የመጨረሻ ንግግር ሊሆን እንደሚችል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ስለ መግለጫው ባወጣው መግለጫ፤ “በሽብር ቡድኑ ዘንድ በዚህኛው ዙርም ‘መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ’ ከሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርድር ነጥብ ማምጣት አልቻለም” ሲል ስምምነት ላይ ላለመደረሱ ተቃራኒውን ወገን ተጠያቂ አድርጓል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት “የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ከመፍታት” ይልቅ የሠራዊቱን አመራር “መከፋፈል” ላይ ያተኮረ እንደሆነ በመጥቀስ ከስሷል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከድርድሩ መጠናቀቅ ሦስት ሳምንት በኋላ ለመንግሥት ቅርበት ባለው ፋና ቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ስምምነት ላይ ላለመደረሱ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዋነኛነት ያነሷቸው ምክንያቶች ከታጣቂ ቡድኑ ቀርቧል ያሉትን “የስልጣን መካፈል” ጉዳይ ሲሆን የቡድኑ ታጣቂዎች ትጥቅ የመፍታት እና የመበተን ጉዳይም “ተቀባይነት” አለማግኘቱን ገልጸዋል።

ድርድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የታጣቂ ቡድኑ አዛዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉደታ፤ “ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ አመራር ውስጥ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል” በሚል ከቡድኑ የተነሳው ጥያቄ መንግሥትን እንዳላስማማ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አመራሮች ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ያሉ ችግሮች የሚፈቱት በንግግር እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም ሦስተኛ ዙር ድርድርን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሲደረግ በይፋ አልታየም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ መንግሥት ሐምሌ ወር ላይ “ሸኔ” ሲሉ ከጠሩት የታጣቂው “ከተወሰኑ ቡድኖች” ጋር “ቀጣይነት ያለው ንግግር” እያደረገ መሆኑን ተናግረው የነበረ ቢሆንም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጉዳዩን አስተባብሏል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ,የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

የህወሓት ቀውስ

አንጋፋው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ያጋጠመው ክፍፍል፤ ውስጥ ውስጡን ሲፋፋም ቆይቶ በዓመቱ የመጨረሻ ወራት የጋመ የ2016 ዓ.ም. ክስተት ነው።

ደም አፋሳሹን ጦርነት ካስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት በኋላ ከህዳር 2016 ዓ.ም. አንስቶ ለ41 ቀናት ስብሰባ ተቀምጦ የነበረው ህወሓት፤ ስብሰባውን ሲጨርስ ባወጣው መግለጫ የክልሉ ህዝብ ችግር ውስጥ ባለበት ወቅት ለረጅም ጊዜ ግምገማ በመቀመጡ ይቅርታ ጠይቆ ነበር። ከዚህ በኋላም ትኩረቱን የሕዝቡን ችግር መፍታት ላይ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር።

ፓርቲው በቀጣዮቹ ወራት የገባበት የተባባሰ ክፍፍል፤ የገባውን ቃል እንዲያከብር ያስቻለው አይመስልም። በአሁኑ ወቅት በፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሚመራው ቡድን ውስጥ የሚገኙት አቶ አለም ገብረዋህድ፣ አማኑኤል አሰፋ እና ሊያ ካሳ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከነበራቸው ስልጣን የተባረሩት በጥቅምት ወር ነበር።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሆኑትን እነዚህን ፖለቲከኞች ከስልጣን ያነሱበትን ምክንያት በወቅቱ አልገለጹም ነበር።

በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል በክልሉ በሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በኩል ሲገለፅ የነበረ ቢሆንም በተለያየ ጎራ ከቆሙት ከአቶ ጌታቸው ረዳም ሆነ ከዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ቡድን በኩል በይፋ የተባለ ነገር አልነበረም።

በተለያየ ጎራ በቆሙት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ዶ/ር ደብረፅዮን መካከል ያለው ክፍፍል በግልፅ የወጣው የህወሓት 14ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ እየተቃረበ ሲመጣ ነበር። ይህንን ስብሰባ በተመለከተ በቅድሚያ ተቃውሟቸውን ያሰሙት የፓርቲው ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባለት ሲሆኑ አቶ ጌታቸው ደግሞ ሐምሌ ላይ ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ለመጀመሪያ ጊዜ የህወሓት አመራሮች “ፈጠሩብኝ” ያሏቸው ችግሮች ገልጸዋል።

የህወሓት አርማ

አቶ ጌታቸው፤ የፓርቲው አመራሮች “ያጡትን ሥልጣን ለማስመለስ፣ ሥልጣን ቀምቶኛል የሚሉትን ደግሞ ለማስወገድ’”ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ከስሰው ነበር። ከቀናት በኋላ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከጉባኤው ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

ህወሓት በጦርነቱ ምክንያት ያጣውን ህጋዊ እውቅና ፓርቲውን በልዩ ሁኔታ በመመዝገብ የእውቅና የምስክር ወራት የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንን ጉባኤ ተቃውሞት ነበር። ፓርቲዎች ይህንን አይነቱን ጉባኤ ከማድረጋቸው 21 ቀናት በፊት ለቦርዱ ማሳወቅ እንዳለባቸውን የሚደነግገውን ህግ የጠቀሰው ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲው የሚያደርገው ጉባኤም ሆነ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች እውቅና እንደማይኖራቸው አስቀድሞ አስታውቋል።

እነዚህ ተቃውሞዎች ግን በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓትን ድርጅታዊ ጉባኤ ከማድረግ አልመለሰውም። ጉባኤው ሲጠናቀቅ የአቶ ጌታቸው የህወሓት ምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ ለአቶ አማኑኤል አሰፋ ተሰጥቶ፤ በጉባኤው ላይ ያልተገኙ አባላት ከፓርቲው አግዷል።

ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ከህወሓት አባልነታቸው መታገዳቸውን በማመልከት ፓርቲውን እንደማይወክሉ ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ሌሎች የፓርቲው ተወካዮች መተካት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንድ ጎራ ያለውን የህወሓት አመራር የሚመሩት አቶ ጌታቸው እና በሌላኛው ቡድን የሚገኙት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውይይቶችን በማካሄድ ላይ ናቸው።

የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

የደመቀ መኮንን ስንብት እና የፖለቲከኞች ክራሞት

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለአስራ አንድ ዓመታት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግሥት ኃላፊነታቸው እና ከብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተሰናበቱ በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ነበር።

አቶ ደመቀ ከ31 ዓመት የተሻገረውን የፖለቲካ ጉዟቸውን ሲያጠናቅቁ ባደረጉት ንግግር “በዚህ ረጅም የአመራር ዘመን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ላጎደልኩት ሁሉ ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

አቶ ደመቀ በተደረገላቸው የሽኝት ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር አገሪቱ ያጋጠማትን “የአገረ መንግሥት ግንባታ ፈተና ለመሻገር” መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል። “በሕዝብ ሰፊ ተሳትፎ እና ባለቤትነት ተቋማትን ማጠናከር” እና “ሕገ-መንግሥትን ማሻሻል” የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው ከጠቋሟቸው መፍትሔዎች መካከል ናቸው።

የአቶ ደመቀን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ የተተካ ሲሆን ደርበው ይዘውት የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስልጣንን ደግሞ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተረክበውታል። ይህ ዓይነቱ የከፍተኛ አመራር ለውጥ በጋምቤላ ክልልም ተደርጓል።

የጋምቤላ ክልልን ከስድስት ዓመት በላይ በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ኡመድ ኡጁሉ እና ምክትላቸው አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ከስልጣናቸው የተነሱት በነሐሴ ወር ነው። ከዚህ ቀደም የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው እየሠሩ የነበሩት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ፤ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ክልሉን የመምራት ኃላፊነት ተረክበዋል።

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዋና ኮሚሽነርነት ያገለገሉት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የአምስት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን አጠናቅቀው የተሰናበቱም በዚህ ዓመት ነበር። በዚህ ዓመት የተደረጉ ሹም ሽሮች በሙሉ ግን የተደላደሉ አልነበሩም።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሰልጣን መምጣት በኋላ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ሁለት ምክትል ሚኒስትር ዲኤታዎቹ የተተኩት በአነጋጋሪ ሁኔታ ነበር።

ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላም ሚኒስትር ዲኤታነት ሲሰሩ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን በተነሱበት ዕለት በቁጥጥር ስር ውለዋል። ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የተከሰሱት አቶ ታዬ፤ ባለፉት ስምንት ወራት በእስር ላይ ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ነው።

ሌላኛው የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ስዩም መስፍን ደግሞ ለስብሰባ ከሀገር በወጡበት ኮብልለዋል። በኮበለሉት የሚኒስትር ዲኤታ ምትክ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ የተሾሙ ሲሆን የአቶ ታዬን ቦታ ደግሞ አቶ ቸሩጌታ ገነነ ተረክበዋል።

የታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ በቴ ኡርጌሳ በተፈጸመባቸው ግድያ ህይወታቸው ያለፈው እየተሸኘ ባለው 2016 ዓ.ም. ነበር። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው አቶ በቴ፤ በኦሮሚያ ክልል በትውልድ ከተማቸው መቂ ከተማ ተገድለው የተገኙት፤ ሚያዝያ ላይ ነበር። ከፖለቲከኛውን ግድያ ጋር በተያያዘ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተገልጾ የነበረ ቢሆንም የምርመራ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እስካሁን አልተገለጸም።