ኡጋንዳዊቷ ኦሊምፒክ አትሌቷ ሬቤካ ቺፕቴጌ

ከ 1 ሰአት በፊት

የኡጋንዳዊቷ ኦሊምፒክ አትሌቷ ሬቤካ ቺፕቴጌ የቀድሞ ፍቅረኛ የነበረው እና በእሳት አቃጥሎ የገደላት ግለሰብ መሞቱን የኬንያው ሆስፒታል ኃላፊዎች አሳወቁ።

ግለሰቡ በደረሰበት ቃጠሎ ምክንያት ሆስፒታል ውስጥ የሕክምና እርዳታ ሲያገኝ እንደነበር ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር ዲክሰን ንዲየማ የተባለው ግለሰብ የማራቶን ሯጯ ከቤተ-እምነት ስትመለስ ጠብቆ ነዳጅ በማርከፍከፍ በእሳት ያቃጠላት።

የሰሜን ምዕራብ ኬንያ ባለሥልጣናት እንደገለፁት ጥንዶቹ በአንድ አነስተኛ መሬት ጉዳይ አለመግባባት በመካከላቸው የነበረ ሲሆን ሬቤካ በሥፍራው ትኖር ነበር።

ግለሰቡ ከሰውነቱ ክፍሉ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው በእሳት በመቃጠሉ ምክንያት የፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ሕክምና ሲደረግለት ነበር።

“አዎ፤ በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ነው የሞተው” ሲሉ ኤልዶሬት በተሰኘችው የኬንያ ከተማ የሚገኘው የሞይ ሪፈራል ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኦዌን ሜናች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አትሌት ሬቤካ ባለፈው ሳምንት ከ80 በመቶ የሰውነት ክፍሏ በእሳት በመቃጠሉ ምክንያት ጥቃቱ ከደረሰባት ከአራት ቀናት በኋላ መሞቷ ይታወሳል።

የአካባቢው ሰዎች ጭቅጭቅ መስማታቸውን እና አትሌቷ የድረሱልኝ ድምፅ እያሰማች ለእርዳታ ወደ ጎረቤቶቿ እንደመጣች ተናግረዋል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ አምስት ሊትር ነዳጅ በጄሪካን ይዞ መጥቶ ጥቃቱን ካደረሰባት በኋላ እሱም በእሳት በመያዙ ቃጠሎ ሊደርስበት ችሏል።

ንዲዬማ አትሌቷ ላይ ያደረሰው ጥቃት በግድያ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ግለሰቡ ዋነኛ ተጠርጣሪ ተብሎ በፖሊስ ክትትል እየተደረገበት ነበር።

አትሌቷ እና ጥቃት ያደረሰባት ግለሰብ ከአደጋው በኋላ ወደ ሞይ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና ሲደርግላቸው ቆይተዋል።

የ33 ዓመቷ ኡጋንዳዊት አትሌት ባለፉት ሁለት ዓመታት ኬንያ ውስጥ የተገደለች ሶስተኛዋ ሴት አትሌት ስትሆን በሁሉም ግድያዎች የአትሌቶቹ ፍቅረኛዎች ተጠርጣሪዎች ሆነው ቀርበዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት አግነስ ቲሮፕ እና ዳማሪስ ሙቱዋ የተባሉ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የተገደሉ ሲሆን በሁሉቱም ግድያዎች የፍቅር ጓደኞቻቸው ቀንደኛ ተጠርጣሪዎች ናቸው።

የቲሮፕ ባል በአሁኑ ወቅት በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ሲገኝ የሙቱዋ ፍቅረኛ ደግሞ አሁንም አድራሻው አይታወቅም።

ኬንያ እና ኡጋንዳ ከሚጋሩት ድንበር አካባቢ የመጣችው ሬቤካ፤ ትራንስ ንዞያ በተባለ አካባቢ መሬት ገዝታ ቤት በመሥራት በአካባቢው ካለ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ቀረብ ባለ ሥፍራ ነበር የምትኖረው።

“ይህ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው። በዚህ ምክንያት አንድ ታላቅ አትሌት አጥተናል። በሥራዋ ስናስታውሳት እንኖራለን” ሲሉ የኡጋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ፕሬዝደንት ዶናልድ ሩካሬ ፅፈዋል።

ቼፕቴጌ በቅርቡ በፓሪስ ኦሊምፒክ በተደረገው የማራቶን ውድድር 44ኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

የአትሌቷ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በሚመጣው ቅዳሜ ቡክዎ በተሰኘው የኡጋንዳ መንደር እንደሚደረግ ይጠበቃል።