የበግ፣ የዶሮ እና የሽንኩርት ዋጋ ጭማሪን የሚያሳይ ምስል

ከ 9 ሰአት በፊት

በዓል ሲቃረብ ሸማች የሚለው ብዙ ነው።

‘የዘንደሮ ገበያ አይቀመስም’ ቀዳሚው ነው።

‘በዓል እንዴት ሊያልፍ ነው?’ ‘ኑሮ ጣራ ነካ!’ ሌላም ሌላም. . .

ነጋዴ ደግሞ በተራው ‘አቅርቦት የለም’ ከሚለው ጀምሮ ‘ከቦታው ጨመረ’፣ ‘ምርት አልገባም’ የሚሉ ሰበቦችን ይደረድራል።

መንግሥት በበኩሉ ‘በስግብግብ ነጋዴዎች የተፈጠረ ጭማሪ’ አልያም ‘የኢኮኖሚ አሻጠር’ ነው ይላል። አንዳንዴም በቂ አቅርቦት እንዳለ ይጠቅሳል።

የጭማሪው ምክንያት ላይ ክርክር አለ። አንድ ነገር ግን ሁሉንም ያስማማል – የዋጋው መጨመር።

ታዲያ ዋጋው ምን ያህል ጨመረ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዓለት ሲመጡ ‘ገበያው እንዴት ነው?’ በሚል የዘገባ ሸፋን ይሰጣል። ሽማቾችን እና ነጋዴዎችን እያነጋገረ አልያም ዘገቢዎቹን ገበያው ድረስ እየላከ የገበያውን ዋጋ ያቀርባል።

ይህ ዘገባ በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይም ያለ ነው።

የዶሮ፣ የዕንቁላል፣ የሽንኩርት እና የቁም ከብቶችን ዋጋ ከሸማቾችና ነጋዴዎች አስተያየት ጋር ያቀርባል።

በእነዚህ ዘገባ የሚነሱ ዋጋዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ ምን ያህል ያንጸባርቃሉ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።

ሆኖም ዘገባዎቹ ላይ ያሉትን ዋጋዎች እንኳን ብንወስድ በዓመታት ውስጥ የበዓል ገበያ እያሻቀበ መሄዱን አይደብቁም።

ከ2012 እስከ 2016 ባሉት 5 ዓመታት የአዲስ ዓመት ገበያ ምን ያህል ጨመረ?

የአዲስ ዓመት ገበያ ከ2012 እስከ 2015 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጳግሜ 5/2012 ዓ.ም. ማለዳ ላይ ባስተላለፈው የቢዝነስ ዘገባ የአዲስ ዓመት ገበያን ቃኝቶ ነበር።

የ‘ሀበሻ’ እና ‘የፈረንጅ’ ዶሮዎች ከ400 እስከ 500 ብር ሲሸጡ እንደነበር የሚያመለክተው ዘገባው ሽንኩርት በኪሎ ከ17 እስከ 20 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ነጋዴዎች እና ሸማቾችን አነጋግሮ ጠቅሷል።

በዚሁ ዓመት ጷግሜ ወር ላይ የተሰራ ሌላ ዘገባ የበግ ዋጋ ከ2 ሺህ 500 እስ 7 ሺህ ብር እንደሆነ የሚያመለክት ሲሆን ሠንጋ ከ13 ሺህ እስከ 35 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እንደሚሸጥ ያሳያል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖ እንዳሳረፈበት በተገለጸው በዚህ ገበያ ቅቤ በኪሎ ከ280 እስከ 350 ብር ተሸጦ እንደነበር ከዘገባው መረዳት ይቻላል።

በኢቢሲ ዘገባ መሠረት በ2012 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ገበያ በአማካኝ ዶሮ 450 ብር፣ ሽንኩርት 18 ብር፣ ቅቤ 315 ብር፣ በግ 4 ሺህ 800 ብር እና ሠንጋ 24 ሺህ ብር ሲሸጥ እንደነበር አመልክቷል።

የዶሮ ዋጋ

በተከታዩ ዓመት 2013 ዓ.ም. ደግሞ ተመሳሳይ ዘገባ የሰራው ኢቢሲ፣ የዶሮ አማካኝ ዋጋ 100 ብር ጨምሮ ከ550 እስከ 650 እንደሚሸጥ ገልጿል።

ሽንኩርት ከዓመት በፊት ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ እስከ 19 ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል። በዘገባው መሠረት በ2013 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ገበያ ሸንኩርት በኪሎ ከ38 እስከ 39 ብር ሲሸጥ ነበር።

በ2013 ዓ.ም. ከፍተኛው የሠንጋ ዋጋ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረበት 15 ሺህ ብር ጨምሮ 50 ሺህ ብር ገብቷል። በዚያ ዓመት ሠንጋ ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ሲሸጥ ነበር።

የበግ ዋጋ ደግሞ ከ3 ሺህ እስከ 8 ሺህ 500 ብር እንደሚያወጣ የተዘገበ ሲሆን አንድ ዓመት ቀድሞ ሲሸጥበት ከነበረው አማካኝ ዋጋ የ700 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

የበግ ዋጋ

ቅቤ ደግሞ ከ500 እስከ 580 ወይም በአማካኝ 540 የኢትዮጵያ ብር የነበረ ሲሆን አማካኝ ዋጋው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ከነበረው የ227 ብር ጭማሪን አሳይቷል

በዚያ ዓመት ‘የሀበሻ’ እንቁላል በ8 ብር ሲሸጥ ነበር።

በቀጣዩ ዓመት 2014 ዓ.ም. ከፍተኛ ጭማሪ የታየው በሠንጋ ዋጋ ላይ እንደሆነ ኢቢሲ በሰራው የበዓል የቢዝነስ ዘገባ ላይ ተብራርቷል።

ከዚህ ጊዜ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የነበረው የሠንጋ አማካኝ ዋጋ በ23 ሺህ ብር አሻቅቧል። ዋጋው ከ45ሺህ እስከ 65 ሺህ ብር እንደነበር ኢቢሲ ዘግቦታል።

በግ ከ4 ሺህ እስከ 10 ሺህ ሲሸጥ የነበረ ሲሆን አማካኝ ዋጋው 7 ሺህ ብር ሆኖ አልፏል። ኢቢሲ የ2014 ዓ.ም. አዲስ ዓመት የበዓል ገበያን ሲያስቃኝ ዶሮ ከ650 እስከ 800 የኢትዮጵያ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ዘግቦ ነበር። በዚህ ሂሳብ አማካኙ የዶሮ ዋጋ 725 ብር እንደነበር መረዳት ይቻላል።

በዚሁ ዓመት ‘የሀበሻ’ እንቁላል በ2013 ዓ.ም. ከነበረው 8 ብር የ4 ብር ጭማሪ አሳይቶ 12 ብር ገብቷል። ቅቤ ደግሞ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው አማካኝ ዋጋ 60 ብር ጨምሮ 600 ብር ገብቷል።

የሽንኩርት ዋጋ

እስቲ ወደ 2015 ዓ.ም. እንሻገር።

አቢሲ በዘገበው መሠረት በ2015 ጳግሜ ወር የአዲስ ዓመት ገበያ የሽንኩርት ዋጋ በኪሎ 38 ብር ነበር። ይህ ማለት ከ2 ዓመት በፊት ከነበረው ዋጋ ተመሳሳይ ወይም በአንድ ብር ዝቅ ያለ ነው።

በወቅቱ ቅቤ ከ520 ብር እስከ 580 ብር የተሸጠ ሲሆን ከ2014 ዓ.ም. ቅናሽ ታይቶበታል። ከዚያ ዓመት በፊት አማካኝ የቅቤ ዋጋ 850 ብር የነበረ ሲሆን በ2015 ዓ.ም. 550 ብር ዝቅ ብሏል።

በዚያ ጊዜ ዶሮ 850 እስከ 950 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አማካኙ ዋጋ 900 ብር ነበር። በዚህ መሠረት አማካኙ ዋጋ ላይ በ2015 ዓ.ም. ላይ 175 ብር ጭማሪ ይታያል።

የእንቁላል ዋጋ

ኢቢሲ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሰራው የበዓል ገበያ ዘገባ መሠረት ዶሮ ከ750 እስከ 1000 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እንደሚሸጥ የዘገበ ሲሆን፣ በዚህ ዋጋ መሰረት የዶሮ ዋጋ ከ2015 ዓ.ም. በ25 ብር ቀንሶ 875 ብር ተሽጧል።

በግ ከሁለት ዓመት በፊት ሲሸጥበት ከነበረው ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። አማካኙ የበግ ዋጋ እስከ 8 ሺህ ብር ጨምሯል። አማካኝ የበግ ዋጋ በ2016 ዓ.ም.16 ሺህ 500 ብር ሆኗል።

እንደ ኢቢሲ የቀጥታ ዘገባ በ2016 ዓ.ም. መገበደጃ ላይ ዝቅተኛው የበግ ዋጋ 6 ሺህ 500 በር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 20 ሺህ ብር ነው።

ቅቤ በኪሎ ከ800 እስከ 900 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አማካኙ 850 ብር ነው። ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ300 ብር ያሻቀበ ነው።

አማካኝ የቅቤ ዋጋ

ባለፉት 5 ዓመታት የበዓል ገበያ ምን ያህል ጭማሪ አሳየ?

ኢቢሲ በሠራቸው ዘገባዎች ላይ ተመስርተን ጭምሪውን እናስላ።

ከአምስት ዓመታት በፊት በነበረው የአዲስ ዓመት ገበያ የዶሮ አማካኝ ዋጋ 450 ብር የነበረ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዶሮ እጥፍ ያህል አድጎ በአማካኝ 875 ብር እየተሸጠ ነው። ይህ ማለት አማካኝ የዶሮ ዋጋ ላይ በአምስት ዓመታት ውስጥ የ94.5 በመቶ ወይም የ425 ብር ጭማሪ ታይቷል።

በግ ከአምስት ዓመት በፊት አማካኝ ዋጋው 4 ሺህ 500 ብር የነበረ ሲሆን ከአምስት ዓመታት በኋላ ከሁለት እጥፍ በላይ አሻቅቦ በ243 በመቶ (ፐርሰንት) ጨምሯል።

በአምስት ዓመታት ውስጥ በ11 ሺህ 700 ብር ጨምሯል እንደማለት ነው።

ኢቢሲ በዘንድሮ የበዓል ዘገባው እስከ ትናንት ድረስ የሽንኩርት ዋጋን አልዘገበም። የአራት ዓመቱን ቁጥር ስንመለከት ግን ከአራት ዓመት በፊት የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ጷግሜ ወር ላይ በአማካኝ 18 ብር የነበረ ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በፊት ደግሞ 38 ብር ሆኖ ተሽጧል። ይህ ማለት ከእጥፍ በላይ አሻቅቦ በ111 በመቶ ወይም በአንድ ኪሎ ላይ 20 ብር ጨምሯል ማለት ነው።

በተመሳሳይ የሀበሻ እንቁላል ከአራት አመት በፊት ሲሸጥብት ከነበረው 8 ብር 100 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ዘንድሮ 16 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

ቅቤ ከአምስት ዓመታት በፊት በኪሎ በአማካኝ 315 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ከአምሰት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ በአማካኝ 850 ብር ወይም የ170 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል።

አሁንስ በርግጥም ‘ኑሮ ጣርያ ነክቷል’ እንላለን ወይስ ‘የዘንድሮው ገበያ አይቀመስም’?

መልካም በዓል!!