September 10, 2024 

ግብፆች ሊሞክሩ የሚችሉት ግድቡ ላይ ጥፋቶችን ማድረስ (sabotage ማድረግ) እንጂ በአየር መምታት ሊሆን እንደማይችል ተጠቆመ

(መሠረት ሚድያ) – ግብፅ የህዳሴ ግድብን በአየር ልትመታ ትችላለች በሚል በአንዳንድ ወገኖች የሚነሳው ግምት ‘ሊሆን የማይችል’ እንደሆነ አንድ የወታደራዊ ትንታኔ የሰጡን ግለሰብ ጠቁመዋል።

“አንዳንዱ ግብጽ ግድቡን በአየር ትመታለች ብሎ ይሰጋል፣ ይህ ሊሆን አይችልም። ያን የሚያክል ወፍራም ኮንክሪት ለመደርመስ የሚያስችለው GBU-28 የተባለው ምሽግ ደርማሽ (Bunker Buster) ቦምብ ግብፅ የላትም” የሚሉት ተንታኙ ግምቱ መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ነው ይላሉ።

አክለውም “ግብፅ ይህን ምሽግ ደርማሽ ሚሳኤል ተሸካሚ F-15/16 ጀት ቢኖራትም ቦምቡን ግን አሜሪካኖቹ አልሸጡላትም። በዚህ ላይ ግድቡን ማፍረስ ለራሷ ደህንነት አደጋ ስለሆነ የምታስበው አይሆንም” ብለው ያስረዳሉ።

እንደ ተንታኙ አባባል በነዚህ ምክንያቶች ግብፆች ሊሞክሩ የሚችሉት ግድቡ ላይ የተለያዩ ጥፋቶችን (sabotage መፈፀም) ነው።

“በልዩ ኮማንዶዎች (Special Surgical Units) ኦፕሬሽኖችን ሊያስቡ ይችላል። ይህም የግድቡን ስራዎች የሚያበላሹ Sabotaging Operations ማለቴ ነው። አንድነት በሌለው ሃገር ለዚህ ተባባሪ ስለማያጡ አያደርጉትም ማለት አልችልም” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

በቅርቡ የግብጹ ‘አረብ ኒውስ’ ሚድያ ኤዲተር በጻፈው አንድ አስተያየቱ ላይ ይህንን ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል።

“ይህ ጥቃት ከተሰነዘረ መነሻው ምስራቅ አይሆንም። ከሆነ በሱዳን ወይም ኤርትራ ክልል በኩል ነው የሚሆነው፣ ያው የሰሞኑ የሱዳን ድንበር ጉዳይ እንደሚታወቀው ነው” በማለት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ለዚህ በር ከፋች ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል።

ግብጽ ሰሞኑን ከቻይና ጋር FC-31 የተሰኘውን ራዳር የማያየው ጀት ልትገዛ እየተደራደረች መሆኑ ተሰምቷል።

“ወደ ቻይና የዞረችው አሜሪካ F-35 ጀት ልትሸጥላት ባለመፈለጓ ነው። ግብጽ ወደፊትም F-35 ልታገኝ አትችልም፣ ምክንያቱም ከእስራኤል ጋር ያለውን የሀይል ሚዛን ሊያናጋ ስለሚችል” በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።